>
5:13 pm - Friday April 19, 0278

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ተቋረጠ (ኢሳት)

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2010)

ለሁለት ሳምንት ያህል ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ መቋረጡ ተገለጸ።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም አሜሪካ መግባታቸው ታወቋዋል።

በሌላ በኩል የኦህዴድና የብአዴን የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካላነጋገርናቸው በፓርላማ መደበኛ ሰብሰባ ላይ እንደማይገኙ ማሳሰባቸውን ተከትሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን የፓርላም አባላቱን ማነጋገራቸው ታውቋል።

የኦህዴድና የብአዴን የፓርላማ አባላት በህዝበ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና በሐገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩን ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ጥያቄ ካቀረቡ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

በዚህም ምላሽ ካላገኘን በሚል በፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው የፓርላማው ስራ ሲስተጓጎል ቆይቷል።

ሰኞ ታህሳስ 16/2010 የፓርላማ አባላቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ሳይሆን በኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ያነጋገሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አብረዋቸው የፓርላማ አባላት ያልሆኑ ሌሎች የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በአስረጅነት መግኘታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

የህወሀት ደጋፊ የሆነው አይጋ ፎርም የተባለው ድረ ገጽ ደግሞ ከአቶ ሃይለማርያም ጋር  ማብራሪያ ለመስጠት የተገኙት የኦሮሚያ፣የአማራ፣የደቡብና የትግራይ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች መሆናቸውን ሲዘግብ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ዜና አግልግሎት በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኘውን ይህንንኑ ድረገጽ ጠቅሶ የስብሰባውን ሂደት ዘግቧል።

ሰኞ ሙሉ ቀን የተካሄደውንና ማክሰኞ የቀጠለውን ይህንን ስብሰባ ተከትሎም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ መቋረጡን ዘገባው አመልክቷል።

ውጥረት ነግሶበታል የተባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወደ ስምምነት ማምራት ባለመቻሉ ረዥም ግዜ ሊወስድ እንደሚችልም ለሐገሪቱ ደህንነት መስሪያ ቤት ቅርበት ያላቸው የሕወሃት ደጋፊዎች በመዘገብ ላይ ናቸው።

የኦህዴድና የብአዴን የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋግሯቸው ላቀረቡት ጥያቄ አቶ ሃይለማርያም ከሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ጋር ተገኝተው ምላሽ ለመስጠት የወሰኑት የሃገሪቱ ችግር ከኢሕአዴግ ውስጣዊ ዴሞክራሲ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ምክንያት ለመስጠት እንደሆነም ተመልክቷል።

ሀገሪቱ እዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ገባች? መንግስት ሲወስዳቸው የነበሩት ርምጃዎች ተገቢ ናቸው ወይ? የሚሉ ጉዳዮች በዋናነት የተነሱ መሆናቸውን የስርአቱ ደጋፊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ነገር ግን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እንደተሰማው ከትግራይ የበላይነት ጋር በተያያዘ በሰራዊቱና በደህንነቱ መዋቀር እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ የህወሃት ሚናን የተመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የቆዩት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሜሪካ መግባታቸው ታውቋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ዋሽንግተን ዲሲ የደረሱት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምን አሜሪካ እንደተጓዙ የታወቀ ነገር የለም ፡፡

ሆኖም የመጡበትን ጉዳይ ጨርሰው ነገ ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለሱ ከቅርብ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል።

አንዳንድ ምንጮች ወደ አሜሪካ የተጓዙት ለህክምና እንደሆነ ቢገልጹም ኢሳት የመጡበትን ምክንያት ማወቅ አልቻልም።

አቶ ገዱ አሜሪካ በገቡ ዕለት በፓርላማ በተካሄደው ስብሰባ የህወሃቱ አይጋ ፎርም አቶ ገዱ በስብሰባው ላይ እንደተገኙ ሲገልጽ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ይህንን ጠቅሶ መረጃውን ማሰራጨቱ ይታወሳል።

Filed in: Amharic