>
5:13 pm - Sunday April 19, 9361

በኢትዮጵያ የለውጥ ዋዜማ - አስገራሚ ክስተት (ጥሩነህ ይርጋ)

በኢትዮጵያ ሰማይ የተከሰተው የለውጥ ዳመና የአቶ ለማ መገርሳን ቡድን አስመርቶ፥ በዶክተር አብይ አህመድና በወጣቱ የኦሮሞ ልሳን አቶ አዲሱ አረጋ ታጅቦ፥ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፊታውራሪነት ወደ አዲስ አበባ ቤተ መንግስት እየነጎደ ነው።

ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲጠብቀው የኖረው የስርዓት ለውጥ ለዓመታት እየተንከባለለ የመጣ የትግል ሂደት እና ባልተገመተ አቅጣጫ በመምጣቱ ብዙዎች በጥርጣሬ የሚመለከቱት በአቶ ለማ መገርሳ የታወጀው የአንለያይም አብዮትና ድንገተኛ ክስተት፥ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው መሃንዲስነት ተቀይሶ የተቀየሰ የለውጥ መሰረት ለመሆኑ በቅርብ ጊዜ የታዩት ክንውኖች ጠቋሚ ናቸው።

የዚህ ጽሁፉ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ድንገት የተከሰተው የለውጥ ኃይል ወድቆ መነሳት የማይችል የትግል ሂደት ውስጥ መሆኑን በማስገንዘብ፥ ተጠራጣሪ የሚዲያ ሰዎች፣ ተቃዋሚዎችና የውስጥ አርበኞች ከተባበሩ ግን የወያኔ ትግሬን ገዥ ኃይል እጅ ጠምዝዞ ያለ ጦርነት ስልጣን እንዲያስረክብ የሚያስገድድና፥ ሂደቱ ለድል እንዲበቃ ሁሉም በሚችለው ቢረባረብ በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ ታሪክ ውስጥ ድንቅ የሚባል ክስተት ይዞ ይመጣል በማለት ሃሳቤን ለማካፈል ነው።

የኦሮሞ እና የአማራ ደም የእኔ ነው በማለት ጎንደር ላይ የተጀመረው የአንድነት መንፈስ፥ ጣና ኬኛ በሚል ስብከት ወጣቱን በአንድነት ፍቅር አቆላልፎ፣ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚል የዜግነት ክብር ተጎናጽፎ እየተመመ ያለው የለውጥ ኃይል ለስርዓቱ መናጋት አስከትሏል፥
የኦሮሞና አማራ ህብረት በወያኔ መንደር ከፍተኛ ጭንቀት ፈጥሯል፥ የገዥዎችን ጉልበት አርዷል፥ ወያኔ በበላይነት የሚመራው መንግስት እንዳለቀበት ተረድቶታል።
ስንል እየታየ ያለውን የህዝብ ትብብርና የትግል ሂደት መዝነንና ዱካውን ተከታትለን እንጂ ዝም ብለን በደመነፍስም አይደለም።

በሁለቱ በኦህዴድ/ብአዴን አሽከር ድርጅቶች ማፈንገጥና የከረ አቋም ምክንያት የወያኔ ትግሬ ገዥዎች ተስፋ ቆርጠዋል፥ ለ100 ዓመት አስበው ያሰሩትን ህንጻና ቪላ ቤት በሃራጅ ለሽያጭ እያወጡ መሆኑን የጎንደር፣ የባህርዳር እና የአዲስ አበባ ምንጮች ጠቁመዋል፥

ከዚህ በፊት ያላቸው የፖለቲካ ታሪክ እንዳለ ሆኖ፥ ዛሬ ላይ ሁኔታው አስገድዷቸውም ይሁን በህሊናቸው ተዳኝተው፥ ለህዝብ ሃሳብ ተገዝተው በሆነላቸው ሰዓት ከስርዓቱ ማፈንገጣቸው የህዝብ መሪነታቸውን የሚያረጋግጥ ታላቅ እምርታ ነው። ይሁን እንጂ፥ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ በስኬት ለማከናወን የሚያስችላቸውን ኃይልና ጉልበት ለማግኘት ዋነኛው ምንጭ የሚመሩት ሕዝባቸው መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

እነዚህ ሰዎች በአቶ ለማ መገርሳ የአንድ ነን አዋጅ ተመርተው፥ በገዱ አንዳርጋቸው እና በዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ አራማጅነት በተራቸው ለኢትዮጵያ ታሪክ ለመስራት፥
ድንገት በህዝብ ልብ ውስጥ ስምጥ ብለው ገብተው የአብዮቱ መሪ፥ የለውጡ ፊታውራሪ ሆነው ብቅ ብለዋልና በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ከመቆም ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለውም።

እሄን በተመለከተ ለህዝብ በማስገንዘብ እረገድ የአክቲቪስቶች እና የነጻ ሚዲያው ሚና እጅግ ከፍተኛ ይሆናል፥ የተጀመረው ትግል ወድቆ መነሳት የሚችል የለውጥ እንቅስቃሴ አለመሆኑን አውቀው ህዝብ በአንድ መስመር ላይ እንዲሰለፍ አቅጣጫ ለመጠቆም ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፥
በበኩሌም እሄን እድል ተጠቅሞ ከወያኔ ዘረኛ ስርዓት የተሻለ ነገር ማምጣት ወደ ሚቻልበት አቅጣጫ እንዲሄድ ማገዙ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው በማለት ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

ስለ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትንሽ የምለው አለኝ፥

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ጀኔራል የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም፥ በተለይ የትግራይ ወራሪ ኃይል ከወልቃይት ጠገዴ ወደ ታች አርማጭሆ የመስፋፋት ዘመቻውን በመቀጠል በ2015 ዓ ም የካቲት ወር ላይ ግጨው እና ሰሮቃ አካባቢ ያደረገውን ድንገተኛ ሰፈራ ተከትሎ፥ የጠገዴ እና የአርማጭሆ ገበሬ ከትግራይ ሰራዊት ጋር በተታኮሰበት ጊዜ ነበር፥ በዚህ ጉዳይ ምን እናድርግ ብሎ በአንድ ስብሰባ ላይ ለጠየቀ የአርማጭሆ ገበሬ፥ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፥”እባቡ በእግርህ ላይ ዱላው በእጅህ ነው” ሲል ህዝቡ ከእባቡ ወያኔ ራሱን መከላከል እንዳለበት መናገሩ ይታወሳል።

በወቅቱ፥ ጀግናው ጎቤ መልኬ፣ ሻለቃ ይላቅ አሸነፈ፣ አቶ ኃይሌ ማሞ እና አቶ አዋጁ አቡሃይን ጨምሮ ብዙ የአገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ ንግግር ከትግራይ እና ከብአዴን ባለስልጣናት ጋር ከተደረገ በኋላ፥ የአማራ ገበሬ ፍርሴ ነው በማለት ከግጨው እስከ ቅራቅርና አዴት ድረስ ከትግሬ ሰራዊት ጋር ተዋጋ፥ሁኔታው ወረራ መሆኑን የተረዳው የአማራ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ሰራዊትም ከህዝቡ ጋር ወግኖ ሁለንተናዊ ድጋፍ አድርጎ የትግራይን ወራሪ ሰራዊት አስደንግጦ መለሰ፥ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ግልጽ በሆነ መንገድ ልዩነቱን በስብሰባዎች ላይ ተናግሮ፥ የአማራ ህዝብ እንዲታጠቅና ድንበሩን እንዲያስከብር ከስንቅ እስከ ትጥቅ የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ እንደነበር ይታማል።

በአጠቃላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የትግሬ ተወላጅ የበላይ ባለስልጣናትን ተጽዕኖ፣ የበረከት ስምዖንን መሰሪ ተንኮልና፥ እንደ አላምነው መኮነን የመሰሉ አጋሰሶችን መክቶ፥ ከታች እንደ ከንቲባ ተቀባ እና ንጉሱ ጥላሁን ያሉ የወያኔ ካድሬዎችን አቃጣሪነት ተቋቁሞ፥ ከስልጣን ይልቀቅ ወይም በእስራት ይቀጣ እስከሚል ግምገማ ተደርጎበት ሳይረታ፥ ትግሉን ግን በመቀጠል፥ ውስጥ ለውስጥ መስመሩን ዘርግቶ ትግሉን ከኦሮሞ ጀግኖች ጋር በማስተባበር፥ ዛሬ ሁሉንም በአሸናፊነት በሚወጣበት ጎዳና እየተራመደ የሚገኝ ረቂቅ ፖለቲከኛና ጥሩ የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑን በሚያረጋግጥበት ጎዞ ላይ ይገኛል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ገበሬ መሳሪያውን አስመዝብቦ እንዲይዝ ፈቃድ መስጠቱን ተከትሎ፥በወያኔ/ኢህአዴግ ለግምገማ ተጠርቶ በተወቀሰና የትግራዩ አባይ ወልዱ የአማራው ጀኔራል ብሎ ለማሸማቀቅ በሞከረበት ጊዜ፥እኔስ ጀኔራል ብሆን በሬውን ሽጦ የገዛውን ጠበንጃና በሰሊጥ ለውጦ ራሱን ያስታጠቀውን ህዝቤን አስመዝግቦ እንዲይዝ በመፍቀዴ ነው፥የመንግስት ካዝና ገልብጠህ፥ የህዝብ ገንዘብ ዘርፈህ፥ ትግራይን በነብስ ወከፍ ያስታጠከው አንተ ምን ልትባል ነው በማለት ሽጉጥ የመማዝ ያክል ከአባይ ወልዱ ጋር ተዘላልፈው ከተለያዩበት ጊዜ ጀምሮ፥ የወያኔ ትግሬ አገዛዝ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ላይ ቂም ቋጥሮ ሲያደባው ይኖራል፥ መጀመሪያ በሙስና እና ከስደኛ አማራ ጋር በማሴር፥ ከዚያም ከአማራ ህዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ ክልሉን ማረጋጋት አልቻልክም በሚል ሰበብ ከህዝብ ነጥለው ለመምታት ሞከሩ፥ በመቀጠለም፥ ህዝባዊ ወገንተኝነት ያሳዩ የዞን ባለስልጣናትን ጨምሮ የአማራ ልዩ ኃይልና ፖሊስ አባላትን በግምገማና በሹም ሽር ከጎኑ እየነጠሉ አነስነሱበት፥ በመጨረሻም ከህዝቡ አቀያይመው ለመነጠልና ባይተዋር ለማድረግ፥ በመሰሪው በረከት አሸማቃቂነት ለአንተ ስም መጠገኛና ለህዝቡ ሰላም በሚል አታለው የጠገዴን መሬት፥ ግጨውንና ማርዘነብን እስከ ሶሮቃ ለትግራይ እጁን ይዘው አስፈረሙት፥ እሄ ሁሉ የተደረገው ገዱ አንዳርጋቸውን ከህዝቡ ጋር ሳያጣሉ ምንም ዓይነት እርምጃ መውሰድ የሚያመጣውን ከባድ አደጋ በመፍራት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ብዙዎች ይገምታሉ፥ በመሆኑም ለአማራ እንቢተኝነት መቀጣጠል ምክንያት የሆነውን የማንነት ጉዳይ በማጣጣል፣ የወልቃይት ጥያቄ ሳይመለስ፥ ብዙ የአርማጭሆ ወጣትና ጀግናው ጎቤ መልኬ በጦር ሜዳ ላይ፥ ሻለቃ ይላቅ አሸነፈ አዲስ አበባ በቃሊት እስር ቤት የተሰውለትን የጠገዴን መሬት ለትግራይ በመስጠት ከህዝቡ ጋር አቀያይመው፥ ወያኔ ህወሃቶች ገዱን ከላይ እስከ ታች ከብአዴን አመራር ጋር አናክሰው በመለያየት፥ ጠቅላላ የድርጅቱን አመራር በትግሬ ለመተካትና ከእጃቸው እየወጣ ያለውን የአማራ ክልል ለመቆጣጠር ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥንቃቄ በተሞላበት የፖለቲካ ጥበብ እንደከሸፈና ያሰቡት ሁሉ ሳይሳካላቸው መቅረቱን አሁን በተከሰተው እውነት መዝነን የገዱን የትግል ስልት ለመታዘብ ችለናል።

የገጠመን ችግር አማራ እና ኦሮሞ እጅ ለእጅ ተያይዞ ካልታገለው ሊፈታ እንደ ማይችል የተገነዘበው ገዱ አንዳርጋቸው በሰይፍ ጠርዝ ላይ ተጉዞ ጠላቶቹን ገልብጦ እንደተነሳ የሚያሳዩ እውነታዎች አምና በተናጠል በተወቀሰበት ፓርላማ ዘንድሮ በበበላይነት ተከስቷል፥ አቶ ለማ መገርሳን ቡድን አስመርቶ ወደ አዲስ አበባ ፓርላማ ይዞት የተመለሰው የአንድነት ኃይልና እያሳየ ያለው የሰከነ የለውጥ ሂደት አጥንትና ጅማቱ ገዱ አንዳርጋቸው ነው ብንል ማጋነን አይደለም።

Filed in: Amharic