>

የወያኔ ድራማ ጣራ የነካበት የውጥረት ሰዓት! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

አሁንስ እንዲያው የሰለቸኝ ነገር ቢኖር ወያኔ ሕዝብ ባስጨነቀው ትንፋሽ ባሳጣው ቁጥር ሕዝብን ለማጃጃል፣ ለማታለል፣ ለመደለል፣ ለመሸንገል፣ ለማዘናጋት፣ የማይሆን ተስፋ አስጨብጦ ለማሳረፍ አንድ ድራማ (ትውንተ ኩነት) ደርሶ በተወነ ቁጥር “ኧረ እባካቹህ አትመኑ! ይሄንን ያደረጉት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ትግላችን ላይ ብቻ እናተኩር….!” እያልኩ ማስተባበሉ ነው፡፡

ሰዉ ግን በተለይም ኢሳትን ጨምሮ የአሜሪካ ድምፅ፣ የጀርመን ድምፅ፣ ኦ.ኤም.ኤንና ሌሎችም የብዙኃን መገናኛዎች በሙሉ ጸሐፍያን ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራውያን) እና ተንታኞችም ሁሉ ምኞታችን የተገለጸበትን ወያኔ ውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖ ባጣደፈው ባስጨነቀው ቁጥር የሚጣፍጠውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ምኞት አካቶ በሚያስደንቅ የትወና ጥበብ እየተወነ ከሽኖ የሚያቀርበውን ትውንተ ኩነት (ድራማ) መተረኩ ደስ ደስ ይላቸዋል፣ ይመቻቸዋል መሰለኝ አንዳንዶቹም ለወሬ ሱሳቸው የሚያወሩት ላለማጣት፣ አንዳንዱም በቅጥረኛነቱ የወያኔን ግብ ለማሳካት ሁሉም ብቻ የወያኔን ትውንተ ኩነት በማስተጋባት ሕዝብን በማደንዘዝ፣ የማይሆን ተስፋ በማስጨበጥ ሳያውቁት የወያኔ መጠቀሚያ ሆነው ወያኔን እያገዙት እየተባበሩት ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አካላት ሕዝብን የሌለን ነገር እንዲጠብቅ ማድረግ ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚያደክመው፣ ወያኔን ለመገላገል ሊሠራው የሚገባውን ሥራ እንዳይሠራ ምን ያህል እንደሚያዘናጋውና እንደሚያቅበው፣ የተወራው ነገር በተደጋጋሚ ውሸት ሆኖ ሲገኝ ወይም ውጤቱ በተደጋጋሚ የማይታይ የውኃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ደግሞ የሕዝቡን ሥነልቡና ምን ያህል እንደሚጎዳውና ይሄም ችግር ሕዝቡን ለድብርት፣ ለፍዘት፣ ለድንዛዜ እንደሚዳርገው ሊረዱ አልቻሉም፡፡

ሕዝብን በማጭበርበር፣ በማወናበድና በማስመሰል ጥበብ የተካነው ወያኔ ሰሞኑን ደግሞ ምን ድራማ እየተወነ ነው መሰላቹህ ድንገት በተጠራው አስቸኳይ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ “ኦሕዴድና ብአዴን የሕወሓት የበላይነት ማክተም አለበት! ብለው ወጥረው በመያዛቸው ሕወሓቶች ከመጨነቃቸው የተነሣ ስብሰባውን ረግጠው ወጡ፣ በሰዓታት ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ ይችላል፣ የሕወሓት የበላይነት አከተመለት፣ ሕወሓት የብአዴንንና የኦሕዴድን ባለሥልጣናት ጠራርጎ የማስወግድ እርምጃ ለመውሰድ ሊገደድ ይችላል፣ አዲስ አበባ በጦር ኃይል ተከበበች፣ በኦሕዴድ አመራሮች ላይ እርምጃ ሊወስዱ የነበሩ የወያኔ ደኅንነቶች ተያዙ፣ ሁሉም ነገር ግልብጥብጡ ሊወጣ ነው….!” እየተባለ ባለበት ሰዓት ተደርቦ ደሞ ምን ሌላ ድራማ መጣ “የኦሕዴድና የብአዴን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አድማ መቱ፣ ጠቅላይ ምኒስትሩ ወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮችን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀው ይሄ ካልተደረገ መደበኛ የምክር ቤቱን ስብሰባ እንደማይታደሙ አስጠነቀቁ….!” የሚለው ድራማም ተደርቦ እየተተወነና እየተስተጋባም ነው፡፡

ሕዝቡም እውነት መስሎት በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ በጊዜ ወደቤቱ እየገባ ነው፣ ወያኔ/ኢሕአዴግ ግልብጥብጡ መውጣቱን የሚያበስር ሰበር ዜና ለመስማትም ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በመጠባበቅ እንቅልፍ ሳይተኙ ሌሊቱን እስከማንጋት ድረስ ሕዝብ የተታለለበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል፡፡

ወያኔ ድራማው እውነት እንዲመስል በአጋጣሚ በሌላ ምክንያት የሞተ የኦሕዴድ ወይም የብአዴን ሰው ካለ የሞተውን ሰው የድራማው አካል ያደርገውና ወያኔን በመቃወሙ በደኅንነቶች እርምጃ ተወስዶበት የተገደለ አስመስሎ ያናፍሰዋል፡፡ ያኔ ሕዝብ ደግሞ ሰው መሞቱን አይቷል ሰምቷልና ድራማው እውነት እንደሆነ ለማመን ይገደዳል፡፡ ወያኔ እውነት ለማስመሰል ሲል በኦሕዴድና በብአዴን ባለሥልጣናት ዙሪያ ያሉ የአንዳንድ ምስኪን ሠራተኞችን ወይም አባሎችን ሕይዎት እንዲያልፍ እስከማድረግ ሁሉ ይደርሳል፡፡ ሕዝቡ እየተሸወደ ያለው በዚህ ነው፡፡ ወያኔ የፈለገውን ለማግኘት አያደርገውም የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደሌለ የሚረዳው በጣም ጥቂቱ ነው፡፡

ጥያቄው፦

* እንዲያው ሲመስላቹህ ስታስቡት የት ያለውና የምታውቁት እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ንጠት ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ወይም ክፍተት ወያኔ/ኢሕአዴግ ውስጥ ኖሮ ነው ወያኔ የሚተውነውን ድራማ እውነት ነው ብላቹህ አምናቹህ የተቀበላቹህትና የምታራግቡት?

* የወያኔ ቢሮክራሲ (አሠራር) እንኳንና እንዲህ ዓይነቱን የፖለቲካ ንጠት ቀርቶ ለማፋሸክና ለመንጠራራት እንኳ ለኦሕዴዶችና ለብአዴኖች የሚፈቅድ ነጻነት እንኳ ኖሮ ያውቃል ወይ?

* ወያኔ ይሄ ዓይነት ግዙፍ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ኦሕዴድና ብአዴን ውስጥ ተፈጥሮ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ዝም ብሎ የመመልከት ሆደ ሰፊነት፣ ተፈጥሮ፣ ልምድ፣ ባሕርይ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ኖሮት ያውቃል ወይ?

* እንኳንና እንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከውስጡ ተፏፉሞ እስኪፈጠር ዝም ብሎ ሊመለከት ቀርቶ ማንም ተራ ዜጋ እንኳ ተራ ነገር ተናገረ ተብሎ የሚቀፈደድበት ወኅኒ የሚወረወርበት ሀገር አይደለም ወይ ያለነው?

* ለምንስ ይመስላቹሀል እነኝህ “ሕወሓትን በስብሰባዎቻቸው እያወገዙ ነው፣ እየተቃወሙ ነው፣ እያፋጠጡ ነው፣ …. እንዲህ እንዲህ አሉ!” እየተባለ በሦስተኛ ወገን በኩል እንዲሁም የነሱ መሆኑ እንኳ ባልተረጋገጠ የፌስ ቡክ አካውንት (የመጽሐፈ ገጽ መዝገብ) ተናገሩ የሚባሉትን ነገሮች በግልጽ በይፋ እንዲያ ማለታቸውን “ውክልናችን፣ ተጠያቂነታችንና ታማኝነታችን ለወከለን ሕዝብ ነው!” ለሚሉት ሕዝብ ለማረጋገጥና ግልጽ መሆን የማይፈልጉት? ፣ አሉ በሚባሉት ነገር ላይም አላቸው የሚባለውን ያህል ቁርጠኝነት ውጤት ወይም ለውጥ ሲመጣ የማይታየው ወይም ከቀናት በኋላ አሉ ከተባሉት ነገር ተቃራኒ ነገር ሲያደርጉ የምናየው ለምን ይመስላቹሀል??? የዚህ ምክንያቱ እንዴት አይገባቹህም???

* ኦሕዴድና ብአዴን የሚባለውን ያህል በፓርላማ አባሎቻቸውና በካድሬዎቻቸው ደረጃ የዓላማና የአቋም አንድነት ያላቸው ከሆነ ታዲያ ኢሕአዴግ ላይ ለሚያነሡት የጥገናዊ ለውጥ ጥያቄያቸው ያለ ጥርጥር በወያኔ ሊያስበላቸው እንደሚችልና ከዚህም የተነሣ ይህ እያደረጉት ነው የሚባለው እንቅስቃሴ እውነተኛ ቢሆን ላለመበላትና የሕዝባቸውንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከለላ፣ ጥበቃና ጥብቅና ለማግኘት ሲሉ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ለአገዛዙ ያላቸውን መተማመኛ ድምፅ በመንፈግ ወይም በማንሣት ሕወሓትን ሽባ አድርገው የኢሕአዴግን ሥልጣን መቆጣጠር፣ ከወያኔ መረከብ የሚያስችላቸውንና ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችሉበትን እርምጃ መውሰድ ያልመረጡት ለምን ይመስላቹሀል???

ኦሕዴድና ብአዴን ወያኔን ጠየቁ የሚባለውን ጥገናዊ ለውጥ መጠየቅ ለእያንዳንዳቸው ለኦሕዴድና ብአዴን አመራሮች ምን ያህል አደገኛና በፈንጅ ላይ የመራመድ ያህል መሆኑን ያጡታል ብሎ የሚገምት ሰው ካለ የመጨረሻ ቂል ነው፡፡ ስለዚህም ጥገናዊ ለውጥ መጠየቅን ፈጽሞ አይሞክሩትም፡፡ ሰዎቹ የእውነት የሚወራውን ያህል የቆረጡ ከሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉት ለወያኔ ጊዜ ሰጥቶ እነሱን ቀረጣጥፎ እንዲበላቸው የሚያስችለውን ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ሊያደርጉ የሚችሉት ሕጋዊ መብታቸውን ተጠቅመው ከወያኔ የአጸፋ እርምጃ ለመዳን ለመጠበቅ ዕድል የሚሰጣቸውንና ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችልበትን ስር ነቀል እርምጃ ነበር ሊወስዱ የሚችሉት፡፡

ነገር ግን ጨዋታው ሁሉ ድራማ በመሆኑ እየተደረገ ያለው ነገር ሁሉ አመክንዮአዊውና የሚጠበቀው ሳይሆን ኢአመክንዮአዊውና የማይጠበቀው ሊሆን ችሏል፡፡ “ሕዝቡ ይሄንን ቁማራቸውን ሊያስተውል፣ ሊረዳ፣ ሊደርስበት አይችልም!” ብለው ይሄው እንደምታዩት ይጫወቱበታል፣ ይቀልዱበታል፡፡ በርግጥም እንኳን ተራው ሕዝብ ፖለቲከኛ ነን፣ ተንታኝ ነን የሚሉት እንኳ በወያኔ ድራማ ምን ያህል ተጭበርብረው፣ ተወናብደው፣ ተታለውና ተሸውደው ድራማውን እያጋፈሩ እንዳሉ የምታዩት ነው፡፡

ወያኔ እነኝህን ድራማዎች ደርሶ በአስደናቂ የትወና ችሎታ እየተወነ ያለበት ምክንያቶች፦

* ምዕራባውያኑ ሕዝባዊው ዐመፁና ወያኔ እየወሰደው ያለው የሚያሳጣ እርምጃ ስላሳሰባቸው እጅግ እንዳሳሰባቸውም በይፋም ይፋዊ ባልሆነ መንገድም እየገለጹለት ያሉበት፣ ሁኔታዎችን ለማረጋጋትና ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘትም ወያኔ ባስቸኳይ በተቃውሞ ካሉ ወገኖች ጋር ድርድር እንዲያደርግ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩበት ትንፋሽ ያጣበት ሁኔታ ስለሆነ ያለው ወያኔ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንደሆነ የሚተችበትን ሥርዓት አገዛዙ ውስጥ ሕይዎት ያላቸውና የሕዝባቸው ጉዳይ የሚገዳቸው፣ የሚያሳስባቸው፣ ለሕዝባቸው አሳቢ ተቆርቋሪ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ያሉ በማስመሰል ምዕራባውያኑ ይሄንን እንቅስቃሴ ተስፋ በማድረግ እያሳደሩበት ያሉትን ጫና እንዲያነሡ፡፡

* ከተቃዋሚዎች ጋርም በአስቸኳይ እንዲያደርግ ያዘዙትን ድርድር አድርግ እያሉ መወትወታቸውን እንዲተው፡፡

* ተቃውሞና ዐመፅ የበረታባቸው የኦሮሞና የአማራ ሕዝብም በኦሕዴድ እና በብአዴን የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ተስፋ እንዲጥል፣ አመኔታ እንዲያሳድር ለማድረግ የተቆመረ እጅግ አስደናቂ ቁማር ነው ሌላ አይደለም፡፡ ይሄ መሆኑንም ከእስከዛሬው መማር ከተሳናቹህ በሚቀጥሉት ጊዜያት እየተወራ እየተናፈሰ ካለው ነገር ከወሬ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ምንም ጠብ የሚል ነገር ካለመኖሩ የምታዩት የምታረጋግጡት ይሆናል፡፡

ምዕራባውያኑ ወያኔ አሳምሮ መተወን እስከቻለበት ጊዜ ድርስ ምንም ቢፈጠር ችግር የለባቸውም፡፡ እነሱ ችግር የሚሆንባቸው ወያኔ ማስመሰሉን፣ መተወኑን ሳይችልበት ቀርቶ ወይም ድራማው ፎርሾበት ማለት ፉርሽ ሆኖበት ለሰብአዊ መብት ቆመናል ባዮቹን የሚያሳብቅ የሚያሳጣ ሁኔታ የተፈጠረ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

“ነገሮች በወያኔ ላይ እየከፉ የሚሔዱ ከሆነ ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚያሳድረው ጫና መጠናከር ማየል ጋር ተያይዞ የምዕራባውያኑ ጫና በወያኔ ላይ የሚያይል የሚበረታ ከሆነ ኦሕዴድንና ብአዴንን ተዋንያን ያደረገው የወያኔ ድራማ መጨረሻው ምንድን ነው የሚሆነው?” ብላቹህ የጠየቃቹህኝ እንደሆን ወደፊት ድራማው ምን ድረስ ሊቀጥል ይችላል መሰላቹህ ኦሕዴድና ብአዴን ሕወሓትን አሸንፈው የወጡ በማስመሰል ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የበላይነት ወይም ፍጹማዊ የአራጊ ፈጣሪነት ሥልጣኑን ከሕወሓት እንዲረከቡ ተደርጎ ሕወሓት ያለ ተጠያቂነት የዘረፈውን እንደያዘ፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ ለፈጸማቸው ክህደቶችና ኢሰብአዊ ግፎች በማይጠየቅበት ሁኔታ ሥልጣን አስረክቦ ዞር እንዲል የተደረገ አስመስለው ሕወሐትን ከጉድ የሚያወጡበትን ጨዋታ እስከመጫወት ድረስ ሊሔዱ እንደሚችሉ ላረጋግጥላቹህ እወዳለሁ፡፡ ኦሕዴድና ብአዴን እዚህ ድረስ ነው በወያኔ ኃላፊነት፣ አደራና አመኔታ የተጣለባቸው፡፡

እናም ወገን ሆይ! ወያኔን ሳትሰማ ለድራማዎቹ ጆሮ ሳትሰጥ ዝም ብለህ ወያኔን ከነአጋሮቹ መደረማመስህን ማሳደድህን አጠናክረህ በመቀጠል ወያኔን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስወገድ ለመገላገል ብቻ ትጋ!!!

ለብአዴንና ለኦሕዴድ የወያኔ ድራማ ተዋንያን ልነግራቸው የምፈልገው ቁም ነገር ቢኖር ለማየት ያብቃቹህ ምን አለ አምሳሉ በሉኝ ወያኔ የሚሰጣቹህን ድራማ ስትተውኑ ድራማው በሚያመጣው ወይም በሚፈጥረው ያልተጠበቀ ሁኔታ ወያኔ በሁኔታዎች ተገዶ የጦስ ዶሮ አድርጎ ሳያጠፋቹህ ሳይበላቹህ ያልቀረ እንደሆነ ምናለ በሉኝ፡፡ ያዝንላቹህ መስሏቹሀል! ወያኔ ካዘነላቹህ ቢበዛ ይሄንን ሁኔታ የሚረዳው በኳላተራል ዳሜጅነቱ (ባይፈለግም መፈጸሙን በሚቀበሉት ጉዳትነቱ) ነው ስለዚህም ቅንጣት አያሳስበውም፡፡ የወያኔን ማንነት አሳምራቹህ እያወቃቹህት በዚህ መልኩ እንደማያጠፋቹህ ካልሠጋቹህ የመጨረሻ ቆሮንጮዎች መሆናቹህን እወቁት!

ይሄ ሆኖ ከሁለት ያጣ ሆናቹህ የሕይዎት ታሪካቹህ አጨራረስ በዚህ መልኩ እጅግ አሳዛኝ ሆኖ ለምንም ሳትሆኑ ከምትቀሩ እስኪ እባካቹህ ወያኔ እያስተወናቹህ ባለው ድራማ ላይ የሰጣቹህን ገጸ ባሕርያትንና ስምን የምር ተጠቀሙበትና ታሪክ ሥሩበት??? ሕሊናቹህን ሸጣቹህ፣ ሰብእናቹህን አራክሳቹህ በአህያው፣ በጥራጊው፣ በወራዳው፣ በቆሻሻው፣ በጭንጋፉ፣ በውርጋጡ፣ በምናምንቴው ወያኔ አህያ ምንትስ እየተባላቹህ እየተዘለፋቹህ እየተበሻቀጣቹህ፣ ሰብእናቹህ እየተዋረደ እየረከሰ ለሆዳቹህ አድራቹህ ለዚህ ውርጋጥ ተረግጣቹህ የተገዛቹህበት የእስከዛሬው ዘመናቹህ ይብቃቹህና እስኪ እባካቹህ እራሳቹህን እንደሰው ለመመልከት ሞክሩና ከዚህ በኋላ ያለውን ዘመናቹህን ተቀጠሙበት??? ለሕዝባቹህ፣ ለሀገራቹህ መሥዋዕትነትን ክፈሉበት??? እስኪ እባካቹህ ወንድ ይውጣቹህ??? ትንሽ እንኳ ይቆጫቹህ፣ ይሰማቹህ እንጅ ጃል??? የምታገለግሉት የገማና የተመረዘ ሥርዓት ሀገሪቱንና ሕዝቧን ዓይተነው በማናውቀው የቀውስ አዘቅት ውስጥ እያሰጠመን መሆኑ ዓይታያቹህም እንዴ???

ኧረ እባካቹህ! እባካቹህ! እባካቹህ! ወያኔ እኮ እናንተን በመመርኮዙ ሊያይልብን ቻለ እንጅ እናንተን መመርኮዝ ባይችል እኮ እፍ ብንለው ገደል የሚገባ ትቢያ፣ ጥራጊ፣ ገለባ እኮ ነበረ፡፡ ለህልውናው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ አናት ላይ እንዳሻው ለመጨፈሩ እናንተን መመርኮዝ በመቻሉ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ይሄንን ያህል የማይተካ ሚና እየተጫወታቹህለት ግን ምንም ያበረከታቹህለት ነገር እንደሌለ እያደረገ ተጀምሮ እስኪጨረስ እሱ ብቻውን ጠንካራ ጀግና ብረት በመሆኑ እስከዚህች ዕለት ድረስ ቀጥቅጦ እየገዛ እንደሆነ እጅግ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ በየጊዜው እየደነፋ መናገሩ እንዲያው ሌላው ሁሉ ይቅርና ይሄ ብቻ እንኳ አይሰማቹህም? አይቆጫቹህም? አይከነክናቹህም? አያቃጥላቹህም??? እንዴት ነው ላይሰማቹህ፣ ላይቆጫቹህ፣ ላይከነክናቹህ፣ ላያቃጥላቹህ የሚችለው??? ሰዎች አይደላቹህም እንዴ???

እስኪ ንገሩን እባካቹህ? እንዴት አድርጎ ነው ወያኔ ለቀፋፊና ለከት የለሽ ንቀቱ፣ ለአዋራጅና ቅስም ሰባሪ ዘለፋው ምላሽ ሊሰጥ የሚገባውን ሆርሞን (እድገንጥር) ከሰውነታቹህ ሊያጠፋው የቻለውና ሰብአዊ ባሕርዩ ከውስጡ እንደሞተበት ባሪያ ተናጋሪ ዕቃ ሆናቹህ ሁሉንም ነገር አሜን ብላቹህ ያለ አንዳች ቅያሜ፣ ቅሬታና መከፋት እንድትቀበሉ ያደረጋቹህ??? እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ! አሁን እናንተ ሰዎች ነን ትላላቹህ? እናንተ እኮ አልተቀበራቹህም እንጅ ሞታቹሀል እኮ! ተንቀሳቃሽ እሬሳዎች!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic