>

የፓርላማው ስብሰባ ብተቃውሞ ተቋረጠ (በውብሸት ሙላት)

የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው አዋጅ ላይ ዛሬ ጠርቶት የነበረው የሕዝብ ውይይት ተሰረዘ…
በስብሰባው ላይ የተገኙትና የመጀመሪያውን የተቃውሞ ደምጵ ያሰሙት የኦሮምያ ኮምኒኬሽን ጵ/ ቤት ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ባደረጉት ንግግር ከ600 ሺህ በላይ ህዝባችን በኦሮምያና ሶማሌ ግጭት በተፈናቀለበትና በየቦታው ግጭቶች በቀጠሉበት፣ ረቂቅ አዋጁም ህዝባችን ባልተወያየበት ሁኔታ ይህ ስብሰባ መጠራት እንደሌለበት በመጥቀስ ለሌላ ግዜ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል። ይህን የአቶ አዲሱ ንግግር አብዛኛው የኦህዴድ የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ድጋፍ ሰጥተዋል።

ከኢህአዴግ ስብሰባ አቋርጠው በድንገት የተገኙት አቶ አባዱላ ገመዳ ከአብዛኛው የኦህዴድ አባላት በተቃራኒ ስብሰባው እንዲቀጥል ሀሳብ ሰጥተዋል። ረቂቅ አዋጁ የቀረበው ለማዳበር እንጅ ለማጵደቅ አለመሆኑን፣ ሌሎች መድረኮች ወደፊት እንደሚኖሩና መወያየቱ ጥቅም እንጅ ጉዳት እንደሌለው ያደረጉት ገለጳ የአባላቱን የጉምጉምታ ተቃውሞ አስከትሎአል።

በስብሰባ አዳራሹ በርከት ያለ ሕዝብ ቢገኝም ተሰብሳቢዎቹ የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት ስለአዋጁ አንወያይም በማለታቸው ውይይቱ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡
አዋጁ ከፌደሬሽን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲላክ የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ውይይት እንደሚያደርግበት በመገናኛ ብዙሃን ተነግሮ ነበር፡፡ ይህ በተግባር አልሆነም ያሉት ተወያዮቹ ሰፊው ሕዝብ ሳይወያይበት በፓርላማው አዳራሽ ብቻ ለተገኘ ሕዝብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

 ተወያዮቹ፤ ለዓመታት የቆየው ይህ አዋጅ ለወራት ቢራዘም ምን ችግር አለው ለምንስ አስቸኳይ ሆነ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ውይይቱ ይካሄድ አይካሄድ በሚለው ላይ ውሳኔ ላይ ሳይደረስ ከረፋዱ 4፡17 ላይ ለሻይ እረፍት ወጥተዋል፡፡
ከ15 ደቂቃ የሻይ እረፍት በኋላ የተመለሱትን ተወያዮች በውይይቱ ላይ የተገኙት የፓርላማው አባል አቶ አባዱላ ገመዳ ከመቀመጫቸው ተነስተው ፊታቸውን ወደ እነሱ በማዞር ዘለግ ላለ ጊዜ አነጋግረዋቸዋል፡፡ ውይይቱ እንዲቀጥልም ሊያግባቧቸው ሞክረዋል፡፡
ይሁንና ተወያዮቹ ሌላ አንገብጋቢ ችግር እያለ እና ሕዝቡ ሳይወያይበት በፓርላማ ህዝባዊ ውይይት ሊደረግ አይገባም በሚል ሀሳባቸው ፀንተው 4፡50 ላይ ስብሰባው ተበትኗል፡፡
ተለዋጭ ቀጠሮም አልተያዘም፡፡
Filed in: Amharic