>

"ደህንነቱ በነለማ ላይ ጫና እያደረሰ ነው"

ሚልኬሳ

ሰብሰባው ከመጀመርያው ጀምሮ ውጥረት የበዛበት፣ መዘላለፍ የበዛበት፣ በልቅ ቃላት የታጀበ ነበር። አቶ ለማና ዶ/ር አብይ “ስብሰባው መካሄድ የለበትም፤ መጀመርያ ሐገሪቷ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ይረጋጋና ነው ወደ ሰብሰባው የምንመለሰው” አሉ። አቶ ገዱና ሌሎች የብአዴን አባላትም “እነ ለማ ትክክል ናቸው” አሉ። በህወሓትና በደኢህዴን በኩል ደግሞ “በሐገሪቷ የተነሳው ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻው የአመራር ችግር ነው፤ ቀውሱ የሚፈታውም በኛ በአመራሮች መካከል ያለው ችግር ሲፈታ ነው” አሉ። 
እነ አብይ “የኢህአዴግ የአመራር ችግር አለ ከተባለ የህወሓት የበላይነት ነው፤ በተለይም የደህንነት ሀላፊ የስራ-አስፈፃሚ አባል ማድረግ እኛ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ነው፤ የህወሓት የበላይነት ሲፈታ ነው የአመራር ችግሩ የሚፈታው፤ አሁን ተራው የኛ ነው” አሉ።

እነ ብናልፍና ገዱ “እነ ለማ ትክክል ናቸው” አሉ።

በህወሓትና በደኢህዴን በኩል ለሁሉም ነገር ግልፅ ውይይት እናድርግ፤ የህወሓት የበላይነት የሚባለው ነገር እውነት ይሁን አይሁንም ጭምር ወደ ግልፅ ውይይት መድረክ እናምጣው” አሉ።
ነገሩ እየተካረረ ሄዶ ወደ መዘላለፍ አደገ። ብአዴንና ኦህዴድ ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣት አኮብኩበው ነበር።

ሰብሰባው ቀጠለ።

አቶ ጌታቸው አሰፋ “እኛ እዚህ ቁጭ ብለን ግልፅ ውይይት እናድርግ፥ የቆሸሸውን ቤታችን እናፅዳ፤ ሐገር እናድን የምንለው ሁላችንም የኢትዮጵያን ጥፋት የማንምኝና የታሪክ ተወቃሾች መሆንን የማንመኝ ሐላፊነት የሚሰማን አመራሮች ነን ብለን ስለምናምን ነው። በመሐከላችን ችግር ቢኖር እንኳ መፍትሔው የጠረጴዛ ላይ ውይይት እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ሁላችን እናውቀዋለን። “ወደ ውይይት አንገባም” ማለት ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተባብሶ እንዲቀጥልና ሀገሪቷ እንድትፈርስ መፍቀድ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። መቸም እናንተ ጊዜያዊ ስሜት አስክሯችሁ ወይም በመሐላችን በተፈጠረ ያለመናበብ የተፈጠረ እንጂ በግሌ እናንተ የእውነት ሐገር እንድትፈርስ የምትመኙ ናችሁ ብየ አላምንም። ለዚያም ነው ብዙ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ሲከሰቱ ፤ አንዳንዶች በግላችሁ በተሳሳተ መስመር ላይ ገብታችሁ ብዙ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ስትሰሩ አይተን እንዳላየን በዝምታና በርዕግስት የምናልፈው። ” ቀጠለ አቶ ጌታቸው “ለምሳሌ አቶ ለማ በዚህ ቀን ክእንትና የተባለ የኦነግ አመራር የተፃፃፍከው፤ ከእንትናም ጋር በስልክ ያወራኸው ሁሉ እናውቃለን፤ አቶ ዐብይ ከእነ እንትና ጋር ያወራኸው፤ አቶ እገሌ ከግብፅ ሰዎች ጋርም የተባባልከው ዝርዝር መረጃ ከእጃችን አለ፤ ከብአዴን ማን ከግንቦት-7 ሰዎች ጋር ምን ምን እንደተባባለ ይኸው መረጃው እጄ ላይ አለ፥ የተከበሩ አቶ እገሌ በዚህ በዚህ ቀን ከአቶ ነአምን ዘለቀ ጋር የመከሩት ምክር ዶክመንት ይኸውና። አቶ እገሌ ስለሚያንቀሳቅሱት የማፍያ ኔትወርክ ዝርዝር መረጃም ከእጃችን ነው። እንደዛም ሆኖ ግን አሁን እዚህ የተሰበሰብነው በዚህ ጉዳይ እሰጣ-እገባ ልንገባ ወይም ኦዲት ልንደራረግ ሳይሆን አሁን የገጠመንን ፖለቲካዊ ቀውስ ስለመፍታትና ሀገር ከጥፋት ስለመታደግ ነው። እዚህ ያለነው ሰዎች ሀላፊነት የሚሰማን ሰዎች ነን ብየ አምናለሁ፤ ስለሆነም ከስሜታዊነት ወጥተን በሰለጠነ መንገድ እንደምንወያይ እምነቴ ነው።”

Filed in: Amharic