>

"ዞምቢዎቹ"

“Dead men walking”

ከአመታት በፊት ትታተም በነበረችው በተወዳጇ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ “ዞምቢዎቹ” በሚል ርዕስ ሁለት አርቲክሎች ወጥተው ብዙዎቻችን አንብበን ነበር ። ፀሃፊው መስፍን ነጋሽ ነበረ መሠለኝ ። እኔም ልሞክር ይሆን ?

ዞምቢዎቹ. የተቦዳደሰ አካላቸውን ከነቅርናቱ እየጎተቱ አሁንም በዙሪያችን አሉ ። ስጋቸው በስብሶ ከአጥንታቸው ላይ ተላቆ በቡቱቷቸው ውስጥ ተንዘላዝሎ ይታያል ፤ በእድሜ ብዛት እጅግ ቢደክማቸውም ሁለተኛውን ሞት ሞተው ከማለቃቸው በፊት ንፁህ ሰው ነክሶ ለመዘነጣጠል ወይም ዞምቢነትን በጥርሳቸውና በጥፍራቸው ቦጫጭቆ በመበከል ወደ ሌላ ሰው በማስተለለፍ ዘራቸውን ለማስቀጠል እጅግ ጓጉተዋል ።

ከአለቆቹ ዞምቢዎች የተራረፈውን የሰው ስጋ እየተስገበገቡ የሚበሉ ለቃቃሚ ተከታዮቻቸው ከኋላቸው ተሰልፈዋል ። ተከታዮቹ ዞምቢዎች እራሳቸው አያድኑም ። አይችሉበትም ። ምክንያቱም የራስ ቅል ፣ ጥርስና ከርስ እንጂ አንጎል የላቸውም ። አንጎላቸውን አለቃ ዞምቢዎቹ ቦጥቡጠው በልተውታል ። ተከታዮቹ ዞምቢዎች በምግብነት የሚወዱት የአካል ክፍል ሆድቃና ፈርስ ነው ። “ጨጓራቸው ደስ ብሎት የሚፈጭላቸው” የበሰበሰ ሆድቃና የገማ ፈርስ ነው ። አንዳንድ ጊዜ አለቆቹ ዞምቢዎች ረሃባቸው ለከት ሲያጣ ተከታይ ዞምቢዎችን ይበላሉ ። የሚበሉ ተከታይ ዞምቢዎችን ለአለቆቹ ዞምቢዎች ይዘው የሚያቀርቡላቸው ሌሎች ተከታይ ዞምቢዎች ናቸው ፤ ተራቸው ደርሶ እነሱም እስከሚበሉ ።

በሁለት የጠኔ ዘመናት አለቃ ዞምቢዎች ሌሎች አለቃ ዞምቢዎችን የበሉበት ጊዜ እንደነበረ በታሪክ ይነገራል ። አሁንም ሶስተኛው የእርስ በርስ መበላላት ሊመጣ ይችላል እየተባለ ነው ። አሁን አሁን ሰው እንደነበሩ ሁሉ ጭራሽ ረስተዋል ።

Filed in: Amharic