>
5:13 pm - Thursday April 19, 2260

የህወሓት ሊቀ መንበር በፓርቲያችን ላይ የጥቃት ዘመቻ ተከፍቷል አሉ (ቢ.ቢ.ኤን)

አዲሱ የህወሓት ሊቀ መንበር ‹‹በህወሓት ላይ የጥቃት ዘመቻ ተከፍቷል፡፡›› አሉ፡፡ በቅርቡ በውዝግብ እና በትርምስ ውስጥ በተካሔደው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ ሊቀ መንበር ሆነው እንዲመረጡ የተደረጉት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ.ሚካኤል፣ በፓርቲያቸው ላይ ተከፍቷል ያሉት ጥቃት፣ አሁን የተፈጠረ ሳይሆን ቆየት ማለቱንም ተናግረዋል፡፡ ጥቃት ከፍተውብናል ያሏቸውንም ወገኖች ‹‹ጠላት›› ሲሉ ፈርጀዋል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን፣ ከስርዓቱ ልሳን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልሳቸው ላይ፣ በፓርቲያቸው ላይ ተከፈተ ያሉት ጥቃት መሰረቱ፡- “ህወሓትን ማዳከም ስርዓቱን ለማፍረስ መሰረት ነው፡፡” ከሚል ስሌት የመጣ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ህወሓት አሁን ባለው አገዛዝ ስር ያለው የስልጣን ድርሻ፣ ከሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎች የተሻለ እና በውሳኔ ሰጪነት ረገድም ብርቱ ድምጽ እንዳለው የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ይህ ሁኔታ፣ ከሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎች በተለየ ሁኔታ በህወሓት ላይ ትኩረት እዲደረግ እንዳስገደደ ተንታኞቹ ይገልጻሉ፡፡
የአንድ ሀገር ከፍተኛ የስልጣን እርከን የሆኑትን መከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት ተቋማት፣ የፖሊስ መስሪያ ቤቶችን እና መሰል ቦታዎችን ላለፉት ሀያ ስድስት ዓመታት አንቀው የያዙት የህወሓት ባለስልጣናት፣ የተለየ ዘመቻ ተከፈተብን ብለው ማለቃቀሳቸው አሳፋሪ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ተቃዋሚዎች፣ ከሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎች በተለየ መልኩ በህወሓት ላይ የተለየ ትኩረት አድርገው የሚታገሉት በተገለጹት ምክንያቶች መሆኑንም ተንታኞቹ ያክላሉ፡፡ በፓርቲው ላይ የተለየ ትኩረት የሚደረገው በተገለጸው ምክንያት ቢሆንም፣ የህወሓቱ ሊቀ መንበር ግን፣ የትግራይን ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ፣ በህወሓት ላይ ብቻ ያነጣጠረውን ትግል፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው ማቅረባቸውን የተመለከቱ ታዛቢዎች፣ ጉዳዩን የመጨነቅ ምልክት ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ህወሓት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ እንደተቀሰቀሰበት ስለተረዳ፣ የመጨረሻ አማራጩ የትግራይን ህዝብ ከጎኑ ማሰለፍ መሆኑን የተናገሩት የፖለቲካ ተንታኞቹ፣ ህወሓት ከመጣበት ህዝባዊ መዓት ራሴን ማትረፍ የምችለው የትግራይን ህዝብ ከጎኔ ሳሰልፍ ብቻ ነው ብሎ እንደሚያምንም ተንታኞቹ ያክላሉ፡፡ የቁርጡ ቀን ሲመጣ፣ የህወሓት ባለስልጣናት ክልላቸውን ገንጥለውም ሆነ በማንኛውም መንገድ ራሳቸውን ሊያተርፉ የሚችሉት፣ የትግራይን ህዝብ አመኔታ ሲያገኙ ብቻ መሆኑን፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተቀረው ኢትዮጵያዊ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱን መንገር ነው ይላሉ ተንታኞቹ፡፡ ይህን ለማሳካትም እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ከወዲሁ ስራቸውን መጀመራቸውንም የፖለቲካ ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡
ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ፣ ከዘጠኙ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አንዱ ሆነው የተመረጡት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከሳምንት በፊት የስርዓቱ ቅምጥ ከሆነው ዛሚ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ልክ እንደ ደብረጽዮን ሁሉ፣ በህወሓት ላይ ዒላማ እየተደረገ እንደሚገኝና፣ ዒላማውም የትግራይን ህዝብ እየጎዳው እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ የፓርቲው አመራሮች በዚህ ወቅት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ በመስጠት የተጠመዱት፣ መጪው ጊዜ ስላስፈራቸው መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
Filed in: Amharic