>
5:13 pm - Thursday April 18, 2616

ከሳሾች “ዓቃቤ ሕግ ቆሞ እየተደበደብን በቪዲዮ ተቀርፀናል” ሲሉ ዓቃቤ ሕጉ ከዳኛው ፊት “አዎ ቀርጨሃለሁ! ምን ታደርጋለህ?” ካለ… ?

ጌታቸው ሽፈራው

እነመቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ የተፈፀመባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ኮምሽኑ በተገቢው መንገድ እንዳላጣራ ገልፀዋል፡፡ ተከሳሾቹ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲያጣራላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

“ሰብአዊ መብት ኮምሽንን ፈርተነዋል። ለኢህአዴግ መረጃ እየሰጠ እያስደበደበን ነው።”  18ኛተከሳሽ አንጋው ተገኘ

“እምነታችንን አንቋሽሸዋል፣ ፂማችን በላይተር አቃጥለዋል፣ ፂማችን በደረቅ ምላጭ ላጭተውናል።” 8ኛተከሳሽ ኢብራሂም ከሚል

“ከእኛ ባልተናነሰ የተደበደቡት የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው በእኛ ላይ የመሰከሩት ናቸው። መብላት አቅቷቸው እኛ ነበር የምናበላቸው።” 31ኛተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ

“የገደሉ፣ ገልብጠው የገረፉን የወንበዴ ቡድኖችም ሊጠየቁ ይገባል።” 33ኛተከሳሽ ሸምሱ ሰኢድ

“የሰብአዊ መብት ጥሰቱን  የፈፀመብን ይህ ቡድን ነው። ይህ ቡድን መርምሮ ያሳውቃል ማለት ለመሸፋፈን ነው። ፍርድ ቤቱ ጊዜው ማጥፋት የለበትም። ጉዳዩን ለማጣራት ሌላ ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት” 1ኛተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ

በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 38 እስረኞች በምርመራ ወቅት ሸዋሮቢት  ተወስደው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመባቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ ባቀረቡት መሰረት ፍርድ ቤቱ የሰብአዊ መብት ኮምሽን እንዲያጣራ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
የሰብአዊ መብት ኮምሽን የምርመራውን ውጤት ለፍርድ ቤትና ተከሳሾች አድርሷል። ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች በሪፖርቱ ላይ አስተያየት ካላቸው እንዲያቀርቡ ከመደበኛው ቀጠሮ ውጭ ዛሬ ህዳር 29/2010ዓም እንዲቀርቡ  አስጠርቷቸዋል። ሆኖም የተከሳሾቹ ጠበቆች ቀጠሮው በምርመራ ሪፖርቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደሆነ ባለመገለፁ አስተያየት በፅሁፍ አለማቅረባቸውን አሳውቀው፣ አስተያየታቸውን ከመደበኛ ቀጠሮ በፊት በፅሁፍ እንደሚያስገቡ ገልፀዋል።

ያለጠበቃ የሚከራከሩት 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ እና 3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ በቃል አስተያየት የሰጡ ሲሆን ጠበቃ ያላቸው ሌሎች ተከሳሾችም አስተያየት ሰጥተዋል። ተከሳሾቹ  የሰጡት አስተያየት:-

“ድብደባው በሁለት ዙር የተደረገ ነው። አንደኛው ዙር እኔን ጨምሮ  175 ሰዎች ላይ ከነሃሴ 28 /2008 ዓም እስከ መስከረም 29/2009 ዓም   የተፈፀመ ሲሆን ከተደበደብነው 6 በመቶው ብቻ ነው በሪፖርቱ የቀበው። በሁለተኛው ዙር በስቅላትና በቶርች የተደረገ ነው። ይህም አልተመረመረም። ሰብአዊ መብት ኮምሽንን ፈርተነዋል። ለኢህአዴግ መረጃ እየሰጠ እያስደበደበን ነው። … ኢንስፔክተር አለማየሁ የተባለ  ድብደባ የፈፀመብን   ፖሊስ በብሔራዊ  ደህንነት ምክር ቤት ስብሰባ በቴሌቪዥን አይተነዋል። አሁንም ለእኛ ለመናገር አደጋ ነው።… አሁንም የተፈፀመብን እንደገና ይጣራ”  18ኛተከሳሽ አንጋው ተገኘ

“ኮምሽኑ በሪፖርቱ ላይ  ተገኘ በተባለው ጉዳይ ላይ ምክረ ሀሳብ ይስጥ ያለው እኛን የደበደበውን ፖሊስ ነው። ፖሊስ ከመደበቅ ውጭ ሊያጣራ አይችልም። ሊያጣራ የሚገባው ሌላ ገለልተኛ አካል ነው።” 3ኛተከሳሽ አሸናፊ አካሉ

“ከእኛ ባልተናነሰ የተደበደቡት የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው በእኛ ላይ የመሰከሩት ናቸው። መብላት አቅቷቸው እኛ ነበር የምናበላቸው። ምስክሮቹም እንደኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፣ ተገደው ነው የመሰከሩብን። የእነሱም ጉዳይ ሊጣራ ይገባል።” 31ኛተከሳሽ ጌታቸር  እሸቴ

አቶ ጌታቸር እሸቴ ከአሁን ቀደም በነበረው የምስክር መስማት ሂደት ዐቃቤ ህግ መኩሪያ አለሙን “እሱ ራሱ ቆሞ ነው” ያስገረፈን በማለቱ አቃቤ ህጉም “ምን ታደርጋለህ? ቀርጨሃለሁ!” ማለቱን በማስታወስ እንዲመዘገብለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል። ተከሳሾቹ ሸዋ ሮቢት ተደብድበው በግድ እንዲያምኑ የተደረጉትን፣ ዐቃቤ ሕግ ባለበት እየተናገሩ በቪዲዮ መቀረፃቸው ቀደም ሲል ገልፀዋል።

“በድብደባ ምክንያት የተፈጠረብንና ያሳየነው ጠባሳ አልተመዘገበም። የሰብአዊ መብት ኮምሽን ኮምሸነሩ ዶ/ር አዲሱ ገ/ እግዚያብሄር በፓርላማ ቀርበው የቃጠሎውን ምክንያት የመልካም አስተዳደርና የአመራር ችግር ነው ብለው  ሪፖርት አቅርበዋል። እኛ ደግሞ የተከሰስነው ከ6ወር በፊት ተደራጅተው ሽብር ፈፀመዋል ተብለን ነው። ፍርድ ቤቱ ህጋዊ ተቋም ነው። ፓርላማውም ህጋዊ ተቋም ነው። በመሆኑም ፓርላማ ላይ የቀረበው ሪፖርት ለፍርድ ቤቱም ሊቀርብ ይገባል። የገደሉ፣ ገልብጠው የገረፉን የወንበዴ ቡድኖችም ሊጠየቁ ይገባል። ህጉ በእኛ ብቻ ሳይሆን በእነሱም ላይ ተግባራዊ መሆን አለበት። የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችም በተመሳሳይ ተገደው ነው የመሰከሩብን።” 33ኛተከሳሽ ሸምሱ ሰኢድ

“እምነታችንን አንቋሽሸዋል፣ ፂማችን በላይተር አቃጥለዋል፣ በደረቅ ምላጭ ላጭተውናል። ይህ የሰብአዊ መብት ሪፖርት እንዲጣራ እንዳቀረብን ተፅፏል። ግን  የተፈፀመብንን አላጣራም። እኔ ከሽዋሮቢት ተመልሼ ፍርድ ቤት ስቀርብ ዳኛ ታረቀኝ ፂሜ በዛ ሁኔታ ተላጭቶ እንደማያውቁኝ ጠይቀውኛል። ሊጣራልን ይገባል” 8ኛተከሳሽ ኢብራሂም ከሚል

“የሰብአዊ መብት ኮምሽን በምክረ ሀሰቡ የፌደራል ወንጀል ምርመራን ነው ያጣራ ያለው። የሰብአዊ መብት ጥሰቱን  የፈፀመብን ይህ ቡድን ነው። ይህ ቡድን መርምሮ ያሳውቃል ማለት ለመሸፋፈን ነው። ፍርድ ቤቱ ጊዜው ማጥፋት የለበትም። ጉዳዩን ለማጣራት ሌላ ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት። የደረሰብን የስነ ልቦና ጉዳት እንዳለ  ሆኖ ተረግጠናል፣
አይናችን፣ እግርና ወገባችን ተጎድቷል። ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ነው፣ ምርመራ ክፍል አይደለም። በመሆኑም ሊጠየቅ ይገባል።” 1ኛተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በእነ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ቀሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ከታህሳስ 23/2010 ዓም እስከ ጥር 3/2010 ዓም ተከታታይ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል።

 

Filed in: Amharic