>

የጉድ ሀገር ጉድ: ሰውን በቁም መቅበር ወይስ ማሰር? (ጌታቸው ሽፈራው)

“ህዳር 9/2009 ዓም ከእርሻ ስመለስ ነው የያዙኝ።   ዳንሻ ወስደው ደብድበውኛል።  ከዛ ወደ ትግራይ ወሰዱኝ። ወደ ትግራይ መሆኑን ከመገመት ውጭ  ልዩ ቦታውን አላውቀውም። ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ አስገቡኝና ግንዱ ላይ በተጠለፈ ገመድ አስረው ጉድጓዱ ውስጥ አስቀመጡኝ። የታሰርኩት ያለ ምግብና ያለ ውሃ ነው።

ተከሳሽ ፈረደ ክንድሻቶ ይርጋ 

ከዛም ወደ ሁመራ መለሱኝ። ለረዥም ሰዓት እጆቼን ወደኋላ አስረው ፀሀይ ላይ አስጥተውኝ ዋሉ። ሁመራ ካለው የወታደራዊ ካምፕ ነው። በዱላ ክፉኛ ደብድበውኛል። በዛን ወቅት ነው ብልቴን የመቱኝ። አሞኝ ስለነበር ማዕከላዊ አላስገቡኝም። ያቆዩኝ ባህርዳር ነው። ብልቴን ስለመቱኝ ለረዥም ጊዜ ተሰቃይቻለሁ።

ቂሊንጦ ከመጣሁ በሁዋላ እንኳ ለሶስት ወራት ያህል ህክምና ማግኘት አልቻልኩም ነበር። ቃሊቲ ጤና ጣቢያ ከ5 ጊዜ  በላይ ተመላልሻለሁ። ፖሊስ ሆስፒታል ለሶስተኛ ጊዜ ተመላልሻለሁ።  ከዛ በኋላ ነው ጥቁር አንበሳ እየታከምኩ ያለሁት።   በድብደባው ምክንያት ከብልቴ በተጨማሪ ሆዴ ላይ ጉዳት ደርሶብኝ ነበር።  በቀዶ ጥገና ተደርጎልኛል።”

በእነ ሚፍታህ ሸህ ሱሩር 74ኛ ተከሳሽ ፈረደ ክንድሻቶ ይርጋ ከተናገረው የተወሰደ ነው። ፈረደ በደረሰበት ጉዳት ሱሪ መልበስ አይችልም።  በጉዳቱ ምክንያትም ያነክሳል።

Filed in: Amharic