>
5:13 pm - Sunday April 18, 3554

የህወሓት አዙሪት፡ በድርጅቱ መግለጫ ላይ የቀረበ ትንታኔ! ! (አስፋው ገዳሙ)

ህወሓት ከ35 ቀናት የዝግ ስብሰባ በኋላ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ስልጣናቸውን ያጡና በስልጣናቸው ላይ ሌላ ስልጣን የጠቀለሉት ታውቋል፡፡ ለመሆኑ ይኸው መግለጫ ካለፉት መግለጫዎች የሚለዩትና የሚያመሳስሉት ነጥቦች ምን ምን ናቸው? በመግለጫው ምን ዓይነት መልእክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው የተለቀቀው? የፖለቲካ እንደምታውስ ምን ይሆን? እስቲ አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን በዝርዝ እንመልከተው፡፡

‹‹ ካለፉት ጥቂት ኣመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ ኣመራሩ እየተዳከመ ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመና፣ ኣመለካከትና ኣደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ህዝባዊነቱ እየቀነሰ፣ የህዝብን ችግር በማያወለዳ መልኩ ሳይፈታ በትንንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ ኣድሯል፡፡›› የህወሓት/ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ (Pdf)፣ ገፅ-2፡፡

በህወሓት ታሪክ ውስጥ በአመራር ላይ ይህን የመሰለ ትችት ሲሰነዘር ለመጀመርያ ጊዜ ይመስለኛል፡፡ አሁንም ቢሆን ‹‹የጦስ ደሮ›› የሆኑ ቢኖሩም፣ የስራ አስፈፃሚ ኮምቴው (ፖሊት ቢሮው) እንዳለ የችግሮቹ ምንጭ ሆኗል ሲባል ዘንድሮ የመጀመርያው ነው፡፡ ከአሁን በፊት ‹‹ከታች ያሉት ናቸው እንጂ ከላይ ያሉት እማ ብፁአን ናቸው›› ዓይነት አስተያየት ነበር ሲሰነዘር የነበረው፡፡ ትችት ሲሰነዘር “ተቺው ስላልገባው ነው” ተብሎ ስለሚታሰብ የአፀፋ ምላሹ አደገኛ ነበር፡፡ አሁን ግን፣ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ማእከላዊው ኮምቴ፣ በተለይም ስራ አስፈፃሚው ኮምቴ መሆኑን እንደሚከተለው ገልጿል፦፡

‹‹ለተፈጠረው ችግር ማእከላዊ ኮሚቴው በኣጠቃላይ ተጠያቂ ቢሆንም የችግሩ የከፋ መገለጫ የህወሓት ስራ ኣስፈፃሚ ኮሚቴ እንደ ኣካልም ሆነ እንደ ግለሰብ ኣመራሩ መሆኑን በመውሰድ ጥልቅ የሂስና ግለ ሂስ መድረክ ኣካናውኗል፡፡›› የህወሓት/ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ (Pdf)፣ ገፅ-3፡፡

ለማንኛውም ግን ድሮም ሆነ አሁን የችግሮቹ ምንጭ አመራሩ ነበር፡፡ ምክኒያቱም፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ የሚያቀርበውና አፈፃፀማቸውን ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው የኸው አካል ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ ኣድራል፡፡›› የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነውም፣ አንድ ከሃገራችን ሁኔታ ጋራ የሚይጣጣሙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ይዘው በመቅረባቸው ነው፡፡

ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋራ መዋሃድ ሲገባቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ከፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋራ እንዲዋሃዱ ነበር ሲሰራ የነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መቀረፅ ያለባቸው ሃገራችን ካሏት የሰውና የጥሬ ሃብት ጋራ በማጣጣም ነው፡፡ ወይም አስፈላጊው ስልጠናና ብድር እንደሚገኝ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ያለው አካሄድ ግን “ብድርም ስልጠናም ሊገኝ ይችላል” ከሚል ግምት በመነሳት ነው፡፡ የብድር ምንጭ ሲጠፋ ብዙ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ሆኖው የሚቀሩትም ለዚህ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ የፀረ ሽብርና የመገናኛ ብዙሐን አዋጆችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ህወሓቶች እነዚህ አዋጆችን ከእንግለዝና ከካናዳ ‹‹ቃል በቃል›› ኮርጀው እንዳመጧቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት፣ አዋጆቹን ከሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋራ ማጣጣም ሲገባቸው የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከአዋጆቹ ጋራ እንዲጣጣም ነበር ታጥቀው ሲሰሩ የነበረው፡፡ በአጠቃላይ ለአመራሩ በሚመች መለኩ ነበር ሲሰሩ የነበሩት፡፡ ይኽም፣ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህግ የበላይነት እንዳይነግስ እንቅፋት ነበሩ ማለት ነው፡፡

‹‹አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡ ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙርያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ፣ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስፈቀምጧል” የተባለው ለዚህ ነው፡የህወሓት/ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ ገፅ 2-3

የእነዚህ ነጥቦች እንደምታ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ አመራሩን ሲቃወም የነበረ፣ በአመራሩ ‹‹በፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ›› ስለ ነበረ ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን አጥተዋል፡፡ መብታቸውን የጠየቁ ከስራ መባረር፣ እስርና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ስለዚህ፣ እነዚህ ወገኖች የገንዘብና የሞራል ካሳ ይገባቸዋል፡፡ ሃገራችንና ህዝባችንም መካስ አለባቸው፡፡ በምን መልኩ? የሕግ የበላይነትን እንዲሰፍን በመታገል፣ ከህግ በላይ የሆኑ አካላትን በህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ፣ ትካላዊ አሰራር እንዲያብብ ከልብ በመስራት፡፡ ሌላው ቢቀር መብታቸው ስለጠየቁ ብቻ በእሰር እየማቀቁ ያሉ ዜጎች ሊፈቱ ይገባል፡፡ በተጨማሪም እርቀ-ሰላም መውረድ አለበት፡፡ አመራሩ ለሃገርና ለህዝቡ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ነው፡-

  • ከ‹‹ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ›› መላቀቃቸውን አምነን የምንቀበላቸው፡፡ 
  • ‹‹በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር›› ለምስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውን የምንገነዘበው፡፡
  • የራሳቸው ክብርና ጥቅም እንደማያስቀድሙ ቃል መግባት የሚችሉት፡፡ እኛም የገቡትን ቃል እንደ ለመዱት እንክት አድርገው እንዳማይበሉት ልንተማመን የምንችለው፡፡
  • ከአሁን በኋላ ለህዝብ ያላቸው ወገንተኝነት እንደማይሸረሸር እርግጠኛ መሆን የምንችለው፡፡ 
  • ‹‹ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ የሚቆጥር>> አመራር ሊከስም የሚችለው፡፡
  • ያኔ ነው ‹‹መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙርያ መለስ እንቅስቃሴዎችን›› መጠመድ የሚችሉት፡፡
  • ‹‹በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር›› ከስረ መሰረቱ የሚነቀለው፡፡ 
  • ያኔ ነው ‹‹በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው›› አመራር ታሪክ የሚሆነው፡፡

የአሁኑ መግለጫ ካለፉት መግለጫዎች የተለየ ነው?  

ፎቶ (ከግራ ወደ ቀኝ) ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረግዚያብሄር (የህወሓት ም/ሊቀመንበር)፣ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (የህወሓት ሊቀመንበር)

መግለጫው ‹‹ ይህ የስትራተጂካዊ አመራር ድክመት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦቻችን አፈፃፀም ላይ እጅግ ከባድ ተፅእኖዎች ፈጥረዋል›› ይላል፡፡ በዚህ መሠረት “ፀረ-ህዝብና ፀረ ልማት ሆኗል” ማለት ነው፡፡ ‹‹በህዝብ ተሳትፎና በጠራ መስመር ማስመዝገብ የጀመርናቸውን በርካታ ለውጦች ማስቀጠል ያልተቻለበት አንዳንዴም ወደሃላ መመለስ የጀመሩበት ሁኔታ እንደነበረ በጥልቀት ታይቷል›› እያሉ ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ህዝቡ በልማትና በሃገር ግንምባታ ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆን እጅና እግሩን አስረው ለድህነት፣ ለችጋርና ለመከራ ዳርገውታል፡፡ ሃገሩን ትቶ እንዲሰደድ ፈርደውበታል፡፡ ሃገሪቱን ለአእምሮ እጥበት (brain-drain) ዳርገዋታል፣ የነገ መሪዎቿን አሳጥተዋታል፡፡  የከፍተኛ አመራሩ ድክመት ‹‹በህዝብ ዘንድ ካስከተለው ከፍተኛ የአመኔታ መሸርሸር›› በተጨማሪ የገጠሩም ሆነ የከተማው የልማት ስራዎችን ‹‹ለአደጋ ያጋለጠ እንደነበረ ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡›› ሆኖም ግን፣ አሁንም “ችግሩ ያለው ድርጅቱ በሚከተላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሳይሆን በአፈፃፀም ላይ ነው” እያለ ነው፡፡ በመግለጫው ገፅ ሶስት ላይ የተቀመጠውን ቃል በቃል እንጥቀሰው፤

‹‹በገጠርም በከተማም የቀረፅናቸው ፖሊስዎችና የቀየስናቸው ስትራተጅዎች ትክክለኝነት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ባይኖርም ኣፈፃፀማችን የደረሰበት ደረጃ ባቀድነው ልክ ኣስተማማኝ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ በህዝባችን ዘንድ ተገቢ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ማድረጉም በትክክል ለይቷል፡፡›› የህወሓት/ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ ገፅ -3

ይህ አባባል፣ የመግለጫውም ሆነ የግምገማው ከድሮዎቹ የተለየ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ መግለጫው በአንድ በኩል ‹‹የቀረፅናቸው ፖሊስዎችና የቀየስናቸው ስትራተጅዎች ትክክለኝነት ላይ የሚያጠራጥር ነገር የለም” ይላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የአፈፃፀም ችግር አለብን›› የሚለው አባባል ብዙ ግዜ ይሆን ተደጋግሟል፡፡

አባባሉን እንኳን መቀየር የተሳነው ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ጥልቅነቱ ምኑ ላይ ነው? ሊፈፀም የማይችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ፋይዳው ምን ይሆን? ሌላ ፖሊሲና ስትራቴጂ የማይሞክሩት ለምን ይሆን? ከአሁን በፊትም ስራ አስፈፃሚዎች ተቀይሯል ነገር ግን አዲሶቹም እንደ ድሮዎቹ ‹‹የአፈፃፀም ችግር›› እያሉ ሲደጋግሙ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን፣  ‹‹የአፈፃፀም ችግር አለ›› ማለት የህወሓት ስራ አስፈፃሚዎች የድርጅቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስፈፀም ተስኗቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አመራሮቹ የብቃት ችግር አለባቸው ወይም ፖሊሲና ስትራቴጂ መቀየር አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ግን የማይፈፅሙትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ይዘው  በየግዜው ‹‹የአፈፃፀም ችግር አለ›› ማለት “ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ” የሚሉት ዓይነት ነው፡፡

ድርጅቱ በመግለጫው ‹‹በገጠር የእርሻ ትራንስፎርሜሽን፣ በከተማ የኣነስተኛና ጥቃቅን ልማት፣ የከተሞች እድገት፣ የወጣቶች እና ሴቶች ስራ ፈጠራ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ባቀድነዉ ልክ ላለመመዝገቡ የስትራተጂክ አመራሩ ድክመት ዋናውን ድርሻ ይወስዳል›› ቢልም የመቐለው ጨምሮ የውሃ ችግር ለምን እንዳልተፈታ፣ የትምህርት ጥራት ለምን እንደ ወደቀ፣ ድህነት ለምን እንደተንሰራፋ በትክክል አልገመገመም፡፡

በአጠቃላይ፣ ከፍተኛ አመራሩ በ‹‹ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ›› የሆነበት ምክኒያት የህግ የበላይነት ስለማይከበር ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ ሳይሆን ድርጅቱ ‹‹የዴሞክራሲ ጫፍ›› በሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስለሚመራ ነው፡፡ ይህ የማርክሰ ሌኒን አስተሳሰብ ከፍተኛ አመራሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያለ አንዳች ጥያቄ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ያስገድዳል፡፡ ይህን የማይቀበል ‹‹ፀረ ልማት›› ተብሎ ይመታል፡፡ ስለዚህ፣ የሃሳብ ልዩነት አይቀበልም! አሰራሩ ግልፅነትና ተጠያቄነትን የለውም፡፡ ለዚህ ነው ከአዙሪቱ መውጣት ያቃተው!!

 አስፋው ገዳሙ

Filed in: Amharic