>

‹‹ልማታዊ መንግስት ነን ኒዎ ሊብራሊዝምን እንቃወማለን›› ይሉናል  (ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ)

‹‹…..ራዲዮና ኢቲቪው የእነሱ ነው፤ አዋጅና መመሪያ የሚጥልብን ፓርላማ የእነሱ ነው፡፡ አዋጅ ጣሳችሁ፣ አሸበራችሁ፣ እያለ የሚይዘን ፖሊስ የእነሱ ነው፤ ከፖሊሶቹ ተቀብሎ የሚፈርድብን ፍርድ ቤት የነሱ ነው፡፡ ያለ ወንጀሉ ተከስሶ የሚፈረድበት ዜጋ እሱ ራሱ የራሱ አይደለም፡፡ ራሳችንም የእነሱ ነን፡፡ የእኛ የሆነው ተስፋችን ብቻ ነው! ለሀገራችንና ለወገናችን ያለንን ብሩህ ተስፋ ምንም ሊያስረው አይችልም……>>

የማያዳምጥና የማያነብ መንግስት እድሜው ስንት ነው?
‹‹መንገዱ በዚህ ወር ይጠናቀቃል፤ ባቡሩ በዚህ ወር ስራ ይጀምራል›› ይሉናል፡፡ መንገዱ ወዴት ያደርሳል? ባቡሩ ወዴት ይወስዳል? ልጆቻችን ወጥተው የማይገቡበት መንገድ፣ የማይሳፈሩበት ባቡር ምን ያደርጋል? መንገዱ ሲሰፋ፣ መጓጓዣው ሲበረክት የልጆቻችን ፍርሀት፣ የእኛ የወላጆች ጭንቀት ከመበርከቱ በቀር ትርፉ ምንድነው?
ቁሳዊ ልማት ብቻውን ማህበረሰባዊ እድገት አያመጣም፤ ቀውስ ካልሆነ በቀር፡፡ የማህበረሰብህን . . . የነገ ወራሽህን. . የወጣቱን አስተሳሰብና አሰራር ሳታለማ (ሳትለውጥ) ታክሲ ብታመጣ፣ ወንዝ ውሀ ስትቀዳ፣ ጫካ እንጨት ስትለቅም ትደፈር የነበረችውን ልጃገረድ፣ ታክሲ ውስጥ ታስደፍራታለህ፤ ነገም ባቡር ውስጥ (ዛሬ በህንድ ሀገር ባቡር ማለት ብዙ የማያስከፍል ፔንሲዮን ነው)፡፡ እኛ ሀገር ብዙ መንገድ ብዙ ወንጀል፣ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሰፊ ዝርፊያ፣ ትልቅ ባለስልጣን ትልቅ ዘራፊ ከማለት የተለየ ፍቺ የሚኖረው መቼ ነው?
‹‹ልማታዊ መንግስት ነን፣ ኒዎ ሊብራሊዝምን እንቃወማለን›› ይሉናል፡፡ በልማት ስም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን አንጠፍጥፈው ወሰዱት፡፡ ይበጃል ያልነውን ስንጽፍና ስንናገር ጸረ ልማት ይሉናል፡፡ ደፈር ብለም መብታችንን ከጠየቅን አሸባሪ ይሉናል፡፡ በየእስር ቤቱ ያጉሩናል፤ ድንበር አሻግረው ያሰድዱናል፡፡ መብታችንንና የመናገር ነጻነታችን ልማታዊ ላሉት መንግስት ጭዳ አደረጉት፡፡
‹‹ልማታዊ አይደላችሁም! ኒዎ ሊብራል ናችሁ አንላቸዋለን፡፡ የምትኖሩበት ቤት፣ የምትነዱት መኪና፣ ልጆቻችሁ የሚማሩበት ትምህርት ቤት (ሀገር)፣ የምትገበያዩበት ሱፐር ማርኬት፣ የምትዝናኑበት ሪዞሪት. . . የልማታዊነት ሳይሆን የኒዎ ሊብራሎች መገለጫ ነው፡፡›› እንላቸዋለን፡፡
‹‹ዝም በሉ! የምንላችሁን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ›› ይሉናል፡፡ ማተሚያ ቤቱ የእነሱ ነው፤ ራዲዮና ኢቲቪው የእነሱ ነው፤ አዋጅና መመሪያ የሚጥልብን ፓርላማ የእነሱ ነው፡፡ አዋጅ ጣሳችሁ፣ አሸበራችሁ፣ እራለ የሚይዘን ፖሊስ የእነሱ ነው፤ ከፖሊሶቹ ተቀብሎ የሚፈርድብን ፍርድ ቤት የነሱ ነው፡፡ ያለ ወንጀሉ ተከስሶ የሚፈረድበት ዜጋ እሱ ራሱ የራሱ አይደለም፡፡ ራሳችንም የእነሱ ነን፡፡ የእኛ የሆነው ተስፋችን ብቻ ነው! ለሀገራችንና ለወገናችን ያለንን ብሩህ ተስፋ ምንም ሊያስረው አይችልም፡፡ የኔ ተስፋ ልጆቼ ውስጥ፣ ያልተወለደው የልጆቼ ልጆች . . . . . ውስጥ አለ፡፡ ተስፋ የሚታሰረው፣ የሚሞተው እርኩስ፣ ለሀገርና ለወገን የማይበጅ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
ዛሬ አትጻፉ ተብለናል፡፡ አትናገሩ ተብለናል፡፡ አንጽፍም፡፡ አንናገርም፡፡ ከተማው ጭር ብሏል፡፡ ሀገሩ ጭር ብሏል፡፡ መንግስትም ጭርታው ተስማምቶታል፡፡ እኛ ግን አንጽፍም እንጂ እንነበባለን፤ አንናገርም እንጂ እንደመጣለን፡፡ የማያነበንና የማያዳምጠን የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው፡፡ አንድ መንግስት ህዝቡን ሳያዳምጥና ሳያነብ ምን ያህል እድሜ ይኖራል? እንጃ! . . . . . አንድ ቀን መንግስት ህዝብን ማንበብ፣ ህዝብን ማዳመጥ ግዴታው ይሆናል፡፡
አቤት ታዲያ ያኔ የሚያነበው መአት! የሚያዳምጠው ቁጣ! ያኔ ማንም መንግስትን መሆን አይመኝም፡፡ እውነቴን እኮ ነው፣ አሁን 1983 ዛሬ ቢሆን ደርግን መሆን የሚመኝ አለ?

Filed in: Amharic