>
5:14 pm - Saturday April 20, 0605

ኢሕአዴግ አርጧል! (ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ)

አንድ፣ ተርታው (ordinary) ዜጋ ሳይቀር እየተገነዘበው የመጣ ሐቅ አለ፡፡ ይኽም ሐቅ ገዥውን ግንባር የተመለከተ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደንብሿል፤ አርጧል፤ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት አይችልም፡፡ ይኽ እውነት ነው፡፡ ገዥው ግንባር ዘመኑን የዋጀ ሐሳብ የሚያፈልቅ አዲስ ኃይል ማፍራት የማይችል ድርጅት ሆኗል፡፡ አሁንም የድርጅቱ ከፍተኛም ይሁን ዝቅተኛ አመራሮች አቶ መለስ ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ነው ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት፡፡ አዲስ ራዕይ የተባለው የድርጅቱ የንድፈ-ሐሳብ መጽሔት ሳይቀር አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች እንደገና እየቀባባ ማወጣት ጀምሯል፡፡ ጥልቅ ተሐድሶ የሚለው “አዲሱ” የኢሕአዴግ መርሐ ግብርም በአቶ መለስ አስተምህሮዎች ላይ የተንጠለጠለ እና የእሳቸውን ጽሑፎች መሠረት ያደረገ ነው፡፡

የሚገርመው የገዥው ግንባር መሪዎች ለስልጠና ሳይቀር አቶ መለስ የተናገሯቸውን ንግግሮች (ቪዲዮዎች) በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ አሁንም የሐሳቡ አምንጭም አሰልጣኙም አቶ መለስ ናቸው፡፡ አንዳንዴም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ሳይቀር የአቶ መለስ ንግግሮች ይቀርባሉ፡፡

ጥልቅ ተሐድሶ በሚባለው መርሐ ግብር ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ “መስመር መሳት” የሚል ይገኝበታል፡፡ መስመር መሳት የተባለውም በአቶ መለስ የተዘጋጁትን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች መተው ማለት ነው፡፡ አዲስ ሐሳብ፣ ከዘመኑ ጋር ሊሄድ የሚችል አቀራረብ ከድርጅቱ መስመር እንደመውጣት ይቆጠራል፤ ያስገመግማል፡፡

የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮችም ሆኑ አፈ ጮሌ (እና አድርባይ) ካድሬዎች የሚናገሩት ሁሉ የዛገና አዲስ ነገር ጠብ የማይለው እየሆነ፣ እንኳን ለሕዝቡ ለራሳቸው ለአባላቱም እጅ እጅ እያላቸው ምጥቷል፡፡ አሁንም እንደትናንቱ በጠላትነት የሚቀመጡት የፈረደባቸው ኪራይሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጥበት፣ ኒዮሊብራሊዝም የሚባሉት ጉዶች ናቸው፡፡ በዘመነ ደርግ የጥበቃና የቤት ሠራተኞች ሳይቀሩ ስለጭቁኑና ስለበዝባዡ “የፊውዶ ቡርዧ መደብ” እየተንደቀደቁ ይናገሩ እንደነበረው ሁሉ፣ የኢሕአዴግ ካድሬዎችም ምንነቱን ስለማያውቁት ኒዮሊብራሊዝም አንገታቸውን እየሰበቁ ይናገራሉ፤ ምንነቱን ስለማያውቁት ልማታዊ መንግሥት በፍፁም ልበ-ሙሉነት “ይተነትናሉ”፡፡ የፈረደባቸው እነ ፍራንሲስ ፉኩያማም የስድብና የውግዘት መዓት ይወርድባቸዋል! ለአብነት ያህል የሚዲያ ዳሰሳ በሚባለው ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡትን “ድንቅ የምሁራን ትንታኔዎች” ማየት ነው፡፡

አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተጀምሯል የተባለው የመተካካት ሂደት ውኃ በልቶታል፡፡ ዛሬ ኢሕአዴግ ውስጥ ስለዚህ አጀንዳ የሚያነሳ አንድም ሰው የለም፡፡ ሌላም ብዙ የድርጅቱን ቆሞ-ቀርነት ሊያስረዱ የሚችሉ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

የሆነ ሆኖ፣ ነገሮች ሁሉ እንዲህ ባሉበት እየረገጡም ቢሆን ኢሕአዴግ ሃያም ሠላሳም ዓመት ሊገዛ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ እንዴት?

“ያረጀው ሥርዓት እየሞተ ነው፤ አዲሱ ሥርዓት ግን ገና አልተወለደም”

ዝነኛው ጣሊያናዊ ፈላስፋና የፖለቲካ መሪ አንቶኒዮ ግራምሺ “ያረጀው ሥርዓት እየሞተ ነው፤ አዲሱ ሥርዓት ግን ገና አልተወለደም” የሚል ዘመን አይሽሬ አባባል አለው፡፡ አንድ ገዥ ፓርቲ ሐሳብ የደረቀበት፣ ያረጠ ድርጅትም ቢሆን እንዲሁ በቀላሉ ይንኮታኮታል ማለት አይቻልም፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሥልጣን ላይ በመኖሩ ምክንያት የገነባቸው ልዩ ልዩ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ያውን፣ እጅ እጅ የሚለውን ሐሳቡን እንደያዘ ሕዝብ እያስለቀሰም ቢሆን ይኖራል፡፡

በእርግጥ አንድ ድርጅት አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ አለመቻሉ፣ ይልቁንም ትኩስ የፖለቲካ ትውልድ መፍጠር አለመቻሉ ለድርጅቱ ትልቅ ጉዳት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ አልቻለም ማለት ነገሩ አለቀ ደቀቀ ማለት አይደለም፡፡ በፍፁም! እንዲያ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ገዥ ፓርቲዎች መንግሥታዊ ሥልጣንን ርስት ባላደረጉትም ነበር፡፡ የዙምባቡዌው አምባገነን ሮበርት ሙጋቤና ድርጅታቸው ዛኑ ፒኤፍ ለዚህ ትልቅ አብነት አይደሉምን? የዩጋንዳው አምባገነን ዩዌሪ ሙሴቬኒና ድርጅታቸውስ? የሱዳኑ ጀኔራል አልበሽርስ? ፈላጭ ቆራጩ ኢሳያስ አፈወርቂስና ድርጅታቸው ሕግዴፍስ? ኧረ ስንቱ! አፍሪካማ በዚህ በኩል ሀብታም ነች፡፡

ቁም ነገሩ፣ ግራምሺ እንዳለው በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል እያረጀና እያፈጀ ያለ ቢሆንም የብዙሃኑን ሕዝብ ቀልብ ሊገዛ የሚችል፣ አዲስና ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ (ተቀናቃኝ) የፖለቲካ ኃይል እስካልተፈጠረ ድረስ ነገሩ ሁሉ ባለበት ይቀጥላል፡፡

በእኔ እይታ የወቅቱ የአገራችን እውነታ ይኽን የመሰለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያለጥርጥር አርጧል፡፡ በዚህ ላይ መከራከር አይቻልም፡፡ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜት (ውስጣቸው እውነታውን እያወቀው) ሊነገሩን እንደሚሞክሩት ሳይሆን ገዥው ግንባር ራሱን ሊያድስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሆኖም የአገራችንን ሕዝብ (ብዙሃኑን) ከጎኑ ሊያሰልፍ የሚችል የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና ያለው የፖለቲካ ኃይል ስለሌለ ላልተወሰኑ ዓመታት በዚኸው ባረጠው ድርጅት እየቆሰልን መቀጠላችን የማይቀር ነው፡፡ አለመታደል!

ኢሕአዴግ እንደማንኛውም የሐሳብ የበላይነት (hegemony) ድርቅ እንደመታው ድርጅት፣ ፕሮግራሙን ለሕዝብ አቅርቦ መሸጥ እንደማይችል ስለተረዳ፣ በአንድ በኩል የፖለቲካ አመራሩን ትቶ በጸጥታው ዘርፍ ላይ ከፍ ያለ ትኩረት አድርጓል፡፡ የፖለቲካ ምልሽ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በሰለጠነ መልኩ ከመፍታት ይልቅ የጸጥታ ኃይሉን እየተጠቀመ ጥያቄ አቅራቢዎችን ዝም ለማሰኘት ሲሞክር በስፋት ይታያል፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ሕዝበኛ (populist) አጀንዳዎችን የሚያራምዱ አመራሮችን ወደፊት በማምጣት የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለማስቀየስ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ የዜጎችን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል፣ ከጊዜው ጋር የሚሄድ የፖለቲካ ፕግራምና ከዘመኑ የሚዘምን ድርጅታዊ ቁመና ሳይኖር ሲቀር የሕዝብን ስሜት በሚኮረኩሩ አላፊ ጠፊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ሕዝበኝነት የዚኽ ስሜታዊ አጀንዳ ዋናው መገለጫው ነው፡፡

የኢሕአዴግ መሪዎች ከዘመናት በኋላ የኢትዮጵያ ገናና ታሪክ የተገለጸላቸው እና ስለኢትዮጵያና ስለሕዝቧ ታላቅነት የሚዘምሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የሰሞኑ የነአቶ ለማ መገርሳ የ“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ተረክ ምንጩም ይኽ ሕዝበኛ አጀንዳ (populism) እንጂ ሌላ ምንም አዲስ ምክንያት የለውም፡፡
ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ ከተቻለ ይኽን ሕዝበኛ አጀንዳ እነመልግሥቱ ኃይለማርያምን በሚያስንቅ መልኩ ይገፋበትና የሕዝብን ስሜት ኮርኩሮ ድጋፍ ለማግኘት ይጥራል፡፡ ይኽ ስትራቴጂ የማያዋጣ ከሆነ ደግሞ ያው የጽጥታ (security) አማራጩን እየተጠቀመ ያዘግማል፡፡ በእርግጥም እንደአስፈላጊነቱ ሁለቱን ስትራቴጂዎች እያፈራረቀ እየተጠቀመ ላልተወሰነ ዓመታት መግዛት (መምራት አላልኩም) ይችላል፡፡ በሙሰኞች ላይ እየተወሰደ ነው የሚባለው ሙስናን የመዋጋት ድራማም ሆነ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኃላፊነት “መልቀቅ” ሁሉ ከዚህ ከመቀባባት እና ሕዝበኛ አጀንዳ ጋር የሚያያዙ ኩነቶች ናቸው፡፡

ሕዝቡ ምን ይላል?
ብዙሃኑ ሕዝብ ገዥው ግንባር የሐሳብ ድርቅ እንደመታው በሚገባ ተረድቷል፡፡ ሆኖም በአገር ቤት ኢሕአዴግን ሊተካ የሚችል ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል እንደሌለ ደግሞ ሕዝቡ ይረዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝቡ በአንድ በኩል በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነት እንዲፈጠርና አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ (ስቴተስኮ) እንዲቀየር ይፈልጋል፡፡

አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ሊቀየር የሚችለው በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ክፍፍል ሲፈጠር ነው የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በየትኛውም መንገድ ሊለቅ የማይችል ድርጅት ስለሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ በግንባሩ አባል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጠረው ክፍፍል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው እንግዲህ የኢሕአዴግ አስኳል ከሆነው ሕወሓት ውጪ ያሉትን ድርጅቶች መደገፍና ሕወሓትን እንዲገዳደሩ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት፡፡ ይኽ አስተሳሰብ በውጭም በአገር ውስጥ ሰፋ ያለ ደጋፊ ያለው ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግን ሊያንበረክኩት የሚችሉት በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው የሚሉ በርካታ ወገኖችም አሉ፡፡ ከአትላንቲክ ማዶ ለውጥ ይመጣል ብሎ በተስፋ የሚጠብቀው ሕዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በውጭ ያሉት ድርጅቶችም ኢሕአዴግን መጣልና አዲስ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር የሚቻለው ሁሉንዐቀፍ ትግል በማድረግ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች “ሁሉንዐቀፍ ትግል” የሚሉትን ፕሮግራም ነድፈው “መታገል” ከጀመሩ ከዐሥር ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ጠብ የሚል ውጤት ግን አልተገኘም!

በበኩሌ በአገር ውስጥ ብዙሃኑን ሕዝብ ሊማርክ የሚችል የጠራ ፕሮግራም ነድፎና ጠንካራ ድርጅታዊ አቅም ፈጥሮ ኢሕአዴን ሊተካ የሚችል አንድም ድርጅት የለም ባይ ነኝ፡፡ በአገራችን ከ70 በላይ፣ አንዳንዴም ከ90 በላይ (በላይ የሚለው ቃል ምንን እንደሚያመለክት ባይገባኝም) የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ ቢባልም፣ ብዙዎቹ እንደ ሱቅ በደረቴ አንዲት ጠማማ ቢሮና አንዲት ሰባራ ኮምፒውተር ያላቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ከድርጅቶቹ መሥራቾች (ባለቤቶች) በስተቀር አባል የሌላቸው አስቂኝ ፍጡራን ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የግለሰቦች መጦሪያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በእኔ በኩል በአገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች ላይ ምንም ተስፋ አላይም፡፡

በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በሚፈጠር ልዩነት ላይ ተስፋ ማድረግም ባዶ ምኞት ነው የሚመስለኝ፡፡ ኢሕአዴግ ከአፈጣጠሩ ስታሊኒስት ድርጅት መሆኑን መርሳት ትልቅ ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ በየትኛውም ስታሊኒስት ድርጅት ውስጥ መሠረታዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በጥቂት፣ እንዳንዴም በአንድ ግለሰብ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚህ ያለ እጅግ ጥብቅ (ዝግ) ድርጅታዊ ቁመና ባለበት ሁኔታ በፓርቲ አባላት መካከል ልዩነት የሚፈጠርበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከስንት አንድ ጊዜ ልዩነት ቢፈጠር እንኳን ተሸናፊው አካል (አንጃው) ወይ ፀባዩን አሳምሮ አርፎ ይቀመጣል፣ ካልሆነ ግን ይደቆሳል ወይም ይደመሰሳል፡፡ ይኸው ነው፡፡ ስለዚህ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በሚፈጠር ልዩነት ላይ ተስፋ ማድረግ ከንቱ ነገር ነው፡፡

ከአትላንቲክ ማዶ በሚደረግ የስደት ትግል ላይ ተስፋ ማድረግም ጨርሶ አያዋጣንም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የስደት ትግል ከሥሩ የተነቀለ ትግል ነው፡፡ እስኪበቃን እንዳየነው የስደት ፖለቲካ ለሕዝብ አላስፈላጊ ተስፋ በመስጠት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች መኖሪያና መጦሪያ ባደረጉት የስደት ትግል ላይ ተስፋ ማድረግ ራስን ማታለል ነው፡፡ በዓለም ላይ በስደት ላይ በሚኖሩ ኃይሎች የተመራና ለድል የበቃ የፖለቲካ ንቅናቄ የለም፡፡ እኛም በዚህ ረገድ ከበቂ በላይ ተሞክሮ አለን፡፡ ላለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት እና ከዚያ በላይ በስደት በጣም ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እየተመሠረቱ እና ሊፈፅሙ የማይችሉትን ቃል እየገቡ የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ አሁን ያሉት ድርጅቶች እጣ ፈንታም ከቀደሙት የተለየ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋ
በእኔ እምነ የኢትዮጵያ ተስፋ አዲሱ ትውልድ ነው፡፡ ይኽ ትውልድ ዘመኑ የፈጠረለትን ዕድል ተጠቅሞ አገራችንን ከገባችበት አረንቋ ማውጣት ይችላል፡፡ ይኽ በብዛትም በጥራትም አገራችን አግኝታው የማታውቀው፣ ነገር ግን ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው (እንዲያውም በአንዳንዶች ዘንድ በጫትና በወሲብ ሱስ የተለከፈ ነው ተብሎ የሚወገዘው) ትውልድ ኢትዮጵያን ከገባችበት አረንቋ ማውጣት ይኖርበታል፤ ይችላልም፡፡

ይኽን ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት በድል ለማጠናቀቅ ግን ይኽ የሁላችንም ተስፋ የሆነው ትውልድ ራሱን ከኢሠፓም ከኢሕአፓም፣ ከኦነግም ከኢሕአዴም አስተሳሰብ በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ማራቅ አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ ራሱን ከመንገኝነትም ይሁን ከልሂቃዊ (elitist) ፖለቲካ መጠበቅ አለበት፡፡ ጥቂት ብልጣብልጦችና አፈጮሌዎች በወንዝ ልጅነትም ይሁን በብሔረሰብ ፖለቲካ ስም የሚጋልቡት መሆን የለበትም፡፡

ይኽ ትውልድ ከፊት ለፊቱ እጅግ አስቸጋሪ ፈተና ተደቅኖበታል፡፡ ስለሆነም ብዙዎቹ በውጭም በአገር ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ስብስቦች ለዚህች አገር የሚበጅ ፕሮግራምም ሆነ ድርጅታዊ ቁመና ስለሌላቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በውጭም በአገር ውስጥም የሚገኙት ድርጅቶች አዲሱን ትውልድ ሊወክል የሚችል ሐሳብ ስለሌላቸው ወጣቱ ራሱ በያለበት እየተደራጀ የራሱን “ግራስሩት” (grassroot) መፍጠር፣ ጠንካራ የፖለቲካ ንቅናቄዎችን ማዋቀር እና የአገራችንን ፖለቲካ ከታች ወደላይ መገንባት አለበት፡፡

ወጣቱ ትውልድ በሥራ ማጣትም ይሁን በአገሪቱ የወደፊት ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ እንዲሰደድ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ግፊት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ በውጭ ያሉት ብዙዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች በበኩላቸው ወጣቱን በጽንፈኛ የብሔረሰብ ፖለቲካ ኮትኩተው በማሳደግ እነሱን ሥልጣን ላይ ለማውጣት የሚታገል እግረኛ ሠራዊት ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይኽ ትውልድ ከእነዚህ ኃይሎች ራሱን መጠበቅ አለበት፤ ከቶም የማንም መሣሪያ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ራሱን ከወንዜ ልጅና ከሌሎች ጠባብ ብሔረሰባዊ አጀንዳዎች ጠብቆ፣ አገርና ሕዝብ ሊቀይሩ በሚችሉ ሐሳቦች ዙሪያ እያደራጀ የራሱንና የአገሩን ጉዳይ ራሱ መወሰን መቻል አለበት፡፡ ጊዜው አሁን ነው

Filed in: Amharic