>

የቡራዩ ጓንታናሞ - ክፍል ፪ (ኣስራት ኣብርሃ)

ባለፈው ፅሁፌ ወደ አንድ ትልቅ ግቢ እንዳስገቡኝ ገልጬ ነው ያቆምኩት። ከዚያ እቀጥላለሁ። (በነገራችን ላይ ኮማንደሩ በጥፊና በእርግጫ ያስመታኝ ቢሮው ውስጥ ከሰቀለው የመለስ ፎቶ ስር አስቀምጦ ነው። ከፎቶው ግርጌ ስር በኦሮምኛ ተፅፎበታል፤ መቼም “ራዕይህን እናስቀጥላለን” የሚል ነው የሚሆነው!) በግቢው ውስጥ ካሉት ክፍሎች ወደ አንዱ እንድገባ ተደረገና በላዬ ላይ ተቆለፈብኝ። አቆላለፋቸው ለዘላለም ነበር የሚመስለው፤ በመጀመርያ ከውጭ እንዲሸገጥ አደረጉና ከዚያ ደግሞ በቁልፍ ከረቸሙት።
በመጀመርያ በጨለማው ምክንያት በደንብ ሊታየኝ ስላልቻለ ግራ ገባኝ። ክፍሉ መብራት የለውም። በዚያ ላይ ምንም ሰው የለበትም፤ ብቻን ነኝ። ለብርሃን ማስገቢያ ተብሎ በብረት ርብራብ የተሰራ ትንሽ መስኮት አለች። በዚያ በገባው ብርሃን ክፍሉን ስቃኘው ብዙ ቦታ ላይ የደረቀ ደም ስመለከት መግረፊያ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ሆንኩ። “ወያኔዎቹ” በእጅ አዙር ሊያስደበድቡኝ ፈልገው ይሆን ብዬ ጠረጠርኩ። ከዚያ ክፍሉ ውስጥ መንጎማለል ያዝኩ። ወዲህ ወዲያ እላሁ፤ አምስት ኪሎ በሽቦ እንደታጠረው አንበሳ መንጎማለል እንጂ ሌላ የማደርገው ነገር አልነበረም።

ክፍሉ በደንብ ተመለከትኩት። ለአንድ ወንድ ላጤ መኖርያ ካሰብነው ይበዛበታል። ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ በእግሬ መለካት ጀመርኩ። በእኔ እግር 16 ተኩል በ16 ተኩል ነው የሆነው። የእኔ እግር ደግሞ 41 ቁጥር ጫማ ተጠቃሚ ነው። የጫማ ቁጥር ግን ምን ማለት ነበረ! ሴንትሜትር ነው ወይስ ሌላ? ብቻ የክፍሉ ስፋት ከላይ እንደገለፅኩት ነው። በክፍሉ ውስጥ ዞሬ ዞሬ ሲደክመኝ በፊት ልብ ያላልኳት የሳር ፍራሽ አገኘሁና ሄጄ ተቀመጥኩባት። ማጠሯ ገረመኝ፤ ሰው ሊተኛባት የተሰራች መሆኗ ለማመን ከብዳል፤ በጣም አጭር ነች። በሰሜን ዋልታ የሚኖሩ እስኪሞስ የሚባሉ ድንክዬ ሰዎች ብታስተኛ ነው።

በዚህ ሁኔታ ላይ ውዬ መሸ። ከጠባቂ ፖሊሶች አንዱ “ብር ካለህ ምግብ ገዝቼ ላምጣልህ” አለኝ። ምንም ዓይነት ምግብ እንደማያስፈልገኝ ስነግረው እንደነበረው ዘግቶኝ ሄደ።በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ እንቅልፍ ሊወስደኝ ስላልቻለ ወደኋላ ተመልሼ በልጅነቴ ስላሳለፍኩት ነገር እያሰብኩ መቆዘም ጀመርኩ። በ7 አመቴ ገዳም ወስደው 12 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ያሳደጉኝ አያቴ ሳስታውስ እንባዬ መጣ። ከብት ማገድ ስለማልወድ ነበር አያቴ ቤት መሆን የምወደው። እናቴ ስትናፍቀኝ ደግሞ እየሮጥኩ እሄዳለሁ፤ ብዙም ሩቅ አልነበረም፤ በእግር የአንድ ሰዓት መንገድ ነው።

እንዲህ አንዱን ሀሳብ ሳነሳ ሌላው ስጥል በግምት እኩለ ሌሊት አለፈ። በዚህ ጊዜ የክፍሉን በር መከፈት ጀመረ። የምፈተንበት ሰዓት ደርሰዋል ማለት ነው ብዬ ተነስቼ ቀቆምኩ። በዚህ ጊዜ ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ተናደድኩ እንጂ አልፈራሁም። በሩን ከፍተው አንደ ሰው ከፍትረው አስገቡት፤ መጥቶ ስሚንቶው ላይ ተዘረረ። ፖሊሶቹ በሩን እንደነበረው ቆልፎት ሄዱ። ተመስገን አልኩኝ። የከፋ ነገር የለም ማለት ነው ብዬ ተፅናናሁ። ስለገባው ሰውዬ ግን ማሰቤ አልቀረም። መልኩን ማየት አልችልም፤ ክፍሉ ጨለማ ነው። እብድ ወይም ሰከራም እንዳይሆን ብፈራም ቢያንስ አጠገቤ ሰው በመኖሩ ተስፋ እንዳደርግ ምክንያት ሆነኛል። ላናግረው ብሞክር መልስ አልሰጠኝም። ከወደቀበትም ሳይንቀሳቀስ ብዙ ቆዬ። በዚያው እንቅልፍ የወሰደውም መሰለኝ፤ እኔም ትንሽ ቆይቼ ተኛሁ።

ጠዋት ስነሳ ሰውዬን አየሁት፤ ፈርጠም ያለ ወጣት ነው። ሰውነቱ በድብደባ ብዛት ጠቋቁሯል፤ ከንፈሩ ከማበጡ የተነሳ የሳልቫኬር ከንፈር መስለዋል። ዝም ብዬ ስመለከተው አይቶ በኦሮሚኛ አናገረኝ፤ ኦሮምኛ እንደማልችል ገለፅኩለት። ከዚያ በተሰባበረ አማርኛ እዚህ ለምን ልታሰር እንደቻልኩ ጠየቀኝ። አላውቅም ስለው፤ ይሄ እኮ ፖሊስ ጣቢያ አይደለም አለኝ። በዚህ ጊዜ ፖሊሶች መጡና ልጁን ይዞውት ሄዱ። ይፍቱት፣ ይልቀቁት አላወቅኩም ነበር። በሶስተኛው ቀን ግን ወደ መደበኛው ፖሊስ ጣቢያ ስሄድ እዚያው አገኘሁት።

እዚያ ቦታ ሶስት ቀን ለብቻዬ ቆየሁ። ከቤተሰብ ጋር አገናኙኝ ብልም የሚሰማኝ አላገኘሁም። ከሚጠብቁኝ ፖሊሶች አንዱ “ያንተ ጉዳይ ፖለቲካ ነው ስለተባለ ከማንም ጋር እንዳትገናኝ ተብለዋል” አለኝ። በኋላ እንደሰማሁት ደግሞ ቤተሰቦቼ፤ ጓደኞቼና የፓርቲዬ አባላት እኔን ለማየት ቢመጡም የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊዎች አስራት አብርሃም የሚባል ሰው አላሰርንም ብለው ክደው ኖሯል። እኔ ስታሰር አብሮኝ የነበረው ሀፍታይ ገብረሩፋኤል እርሱ ሲታሰር እዚህ ነበርኩ ቢልም አላየህም ብለው ካዱት። በዚህ ምክንያት በቤታችን ለቅሶ ተጀምሮ እንደነበር ነው የተረዳሁት። የሆነ ቦታ ወስደው ገድሎት ይሆናል በሚል። አንድም ጉዳዩ ወዲያው በሚዲያ በመውጣቱ አንድም ደግሞ በሌላ እነርሱ በሚያውቁት ምክንያት ታጥፎ ይሆናል እንጂ የታሰበልኝ ነገርማ ነበር! የፈለጉትን ለማድረግ የሚከለክላቸው ምንም ዓይነት ምድራዊ ሀይል እንደሌለ በተግባር ሊያሳዩኝ ፈልገውም ሊሆን ይችላል።

የሆነ ሆኖ እኔ ምግብ አልበላም ብዬ ውዬ አደርኩ። እንደገና ዋልኩ፤ ከሚጠብቁኝ ፖሊሶች አንዱ ለምን ምግብ እንደማልበላ ጠየቀኝ እዚህ በረሀብ ድፍት ብል ማንም ግድ እንደሌለውና እንደማይጠየቅም አስረዳኝ።
እኔም ቤተሰቦቼ ሳላገኝ፤ ወደ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ምግብ አልበላም አልኩት። ቀጥሎ ትንሽ አሰበና “በእኔ ሀላፊነት ከቤተሰብህ ጋር በስልክ ላገናኝህና ምግብ ብላ” አለኝ። ባቀረበው አማራጭ ተስማማሁና የባለቤቴን ስልክ ሰጠሁት። ለማንም እንዳትናገሪ ብሎ ካስጠነቀቃት በኋላ ደህና መሆኔን ነገራት በዚህም ምክንያት ከታሰርኩ በኋላ ለመጀምርያ ጊዜ ምግብ በላሁ።

ከዚያ ሰኞ ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት ያቀርቡኛል ብዬ ስጠብቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ወስደው ከእስረኞች ጋር ቀላቀሉኝ። አላሰርነውም እያሉ ሲያላግጡ ሰንብተው እነርሱ በሚያውቁት ምክንያት ከሰዓት ላይ ወደ ፍርድ ቤት አቀረቡኝ። የአንድነት አመራሮች ኢንጂነር ግዛቸውና ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ጨምሮ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በፍርድ ቤቱ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ማንም ሰው አይገባም ተብሎ የፍርዱን ሂደት በዝግ ችሎት ተካሄደ። ሶስቱም ዳኞች ወጣቶች ነበሩ። የመሀል ዳኛዋ ደግሞ ሴት ነች። የቀረበብኝ ክስ “እስረኞችን በሀይል ለማስፈታት ሙከራ ማድረግ” የሚል ሆነ። የፖሊስ ጣቢያው ሀላፊ ግን እኔን ሊጠይቅ ለመጣ ሁሉ “ፖሊስ ሰደበ” እያለ ነበር የሚናገረው። ምናልባት በመጀመርያ ሀላፊው ወደላይ ሪፖርት ሲያደርግ እስረኞች ለማስፈታት ሞከረ ብሎ ከተናገረው ጋር እንዳይምታታበት ብሎ ይሆናል። ሰደበን ቢሉ አዋጪ መሆኑ በኋላ ገብቷቸው ነበር ማለት ነው። ያም ቢሆን መሰወርና መደበደብ ምን አመጣው ብሎ የሚጠይቀው ሰው ቢያገኝ መልስ የሚኖረው አይመስለኝም።
ዳኛዋ “አንተስ ምንትላለህ?” አለችኝ። የሆነውን ሁሉ በዝርዝር ነገርኳት። ከዚያ ሶስቱም ዳኞች ለተወሰነ ደቂቃዎች ከመከሩ በኋላ ክሱ አሳማኝ ሆኖ ስላላገኘነው ያለቀጠሮ በ500 ብር ዋስ እንዲፈታ ወስነናል አለች። ይዞኝ የሄደው ፖሊስ ውሳኔውን ሊቃወም ሞከረ፤ ውጭ እንደወጣንም “አመራሩ ነው ተወያይቶ የሚፈታህ እንጂ እርስዋ ስላለች አይደለም” አለኝ። እኔም “አንተ የምትለው አመራር እኔ አላውቀውም። ጉዳዩ በፍርድ ቤት መልስ አግኝተዋል” አልኩት በንዴት። የሆነ ሆኖ ለመፈታት ተጨማሪ 24 ሰዓት መጠበቅ ነበረብኝ። ያሰሩኝ ሰዎች ዳኛዋ እንደፈታችኝ እንዲሰማኝ አልፈለጉም።

ዳኛዋ ግን የቡርቱካን ሚዴቅሳ ዓይነት መንፈስ ያላት ለመሆኗ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሀገር ያለ አንድ ደግ ሰው አይቀርም እንደሚባለው፤ በዚህ የወጣትነት እድሜዋ ፍትህና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ያደረገችው ጥረት አድንቃለሁ።

በመጨረሻ ያደርኩበት ክፍል የተወሰነ ገጠመኝ ብገልፅ ደስ ይለኛል። ከድብቁ እስር ቤት ወጥቼ ከሌሎች እስረኞች ጋራ ተቀላቅዬ ነው ያደርኩት። እዚህ ከገጠመኝ ሰዎች አለም ተክኤ የተባለ “ኤርትራዊ” የደርግ ወታደር ታሪክ እጅግ አሳዛኝ ነው። አስመራ አከባቢ ተወልዶ ያደገው አለም ተክኤ አሁን እድሜው ወደ 60ዎቹ የሚጠጋ ነው። በ1972 ነው ውትድርናውን የተቀላቀለው፤ የ21ኛው ክፍለጦር አባል የነበረው አለም ሁለት ጊዜ በጥይት ተመቶ ቆስለዋል፤ መጨረሻ ላይ የቆሰለው በ1981 ዓ.ም. አሰብ ላይ ነበር።
ኤርትራ አትገነጠልም፤ ቀይ ባህራችን አይሄድም ብሎ የተዋጋው አለም አሁን ያለበት ሁኔታ የሚገርምም የሚያዛዝንም ነው። የተዋጋለት ዓላማ ተሸንፈዋል፤ የትውልድ ሀገሩ ዛሬ ተገንጥሎ ሌላ ሆኗል። ቤተሰቦቹ ይኑሩ ይሙቱ የሚያቀው ነገር የለም። በተወለደበት መንደር ተረስተዋል። እርሱ ግን እዚህ ቡራዩ ሚስት አግብቶ ሶስት ልጆች ወልዶ እነርሱን ለማሳደግ ደፋ ቀና ይላል፤ ህይወት ግን እንዲህ ቀላል አልሆነችለትም።

“ምን ሆነህ ነው የታሰርከው?” አልኩት። “ሞባይል ሰረክህ” ተብዬ አለ። “እውነት ነው ሞባይል ሰርቀሃል?” ስለው እያፈረ መስረቁን ነገረኝ። “ከአንድ የዱቄት ፋብሪካ ነው የምሰራው፤ ደሞዜ ስድስት መቶ ስትሆን የጡረታና የግብር ብለው ቆራርጠው 530 ነው የሚደርሰኝ፤ ሶስት ልጆች አሉኝ፤ በዚህ ላይ ባለቤቴም ስራ የላትም” አለኝ። “እና በዚህ ምክንያት ወደ መስረቅ ገባሁ እያልከኝ ነው?! አልኩት። “አንዳንዴ በጣም ሲቸግረኝና ልጆቼ የሚበሉት ሲያጡ በአውቶብስ እየተሳርኩ ኪስ አወልቃለሁ” አለ። አለም የጫትና የሽጋራ ሱስም አለበት። ፍርድ ቤት ቀርቦ መስረቁ በግልፅ በማመኑ ምክንያት 8 ወር ተፈርዶበታል። መቼም ከእድሜው፣ ከሁኔታው አንፃር ሊሰርቅ ይችላል ብለህ የምትገምተው ሰው አይደለም።
አበቃሁ!

Filed in: Amharic