>

እንጉልፋቶዋ ህወሃት ብራቾ ሰብራለች !! (እንግዳ ታደሰ - ኖርዌይ)

የሶቪየት ህብረት የክልል ኮሚንስት ፓርቲ አባላት የታላቁን የጥቅምት ሶሻሊስት አብዮት በአል ለማክበር ሲሉ ስብሰባ ተቀምጠዋል ፡፡ የክልሉ የፓርቲ ሊቀመንበር በበአሉ ላይ ሞቅ ያለ ንግግር አደረገ ፡፡ ውድ ጓዶች ! ከአብዮቱ ማግስት በኋላ ፓርቲያችን ስላስመዘገባቸው አስደናቂ እድገቶች በኩራት አሁን እናገራለሁ ፡፡ ለምሳሌ ማርያን ውሰዷት ፡፡ ማርያ ከአብዮታችን በፊት ምን   ነበራት ? ማይም አርሶ አደር ነበረች ፡፡ አንድ ቀሚስ ብቻ የነበራት ፥ ለግሯ መጫሚያ ያልነበራት ምስኪን አርሶ አደር ነበረች ፡፡ አሁንስ ? አሁንማ ! የክልላችን ቁጥር አንድ ተምሳሌት ሆና ክልላችንን በሙሉ በወተት ምርት በማንብሽበሿ የወትተ እናታችን የሚል ስም ተጎናጽፋለች ፡፡

ኢቫን አንድሬቭን ተመልከቱት ! በክልላችን የመጨረሻው ድሃ የነበረና ፈረስ የሌለው ፥ ላም ያልነበረው ከመጥረቢያ አቅም እንኳ ያልነበረው የነጣ ደሀ ነበር ፡፡ አሁንስ ? አሁንማ የትራክተር ሾፌር ሆኖ ባለ ጥንድ ጫማም ጭምር ሆኗል ፡፡ ስሚርኖቪቺን ውሰዱ ! በክልላችን አደገኛ ቦዘኔ የነበረ ጠጪ ፥ እጁ የማይገባበት ቦታ ያልነበረው በተለይ በበረዳማው የከፋ ክረምት ሁሉ በየሰፈሩ እየገባ በጁ የገባውን ሁሉ የሚዘርፍ አሸባሪ ሌባ ነበር ፡፡ ዛሬስ ? ዛሬማ ይኽው የፓርቲያችን አንደኛ ጸሃፊ ሆኗል ፡፡

በቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት ምጸታዊ ቀልድ ጽሁፌን የጀመርኩት ፣ የንጉልፋቶዋ ሀወሃት ሰሞነኛ ምስቅልቅል ከዚህ ፖለቲካዊ የምጸት ቀልድ ጋር ስለተመሳሰለበኝ ነው ፡፡ ጣልያኖች መኪኖቻቸው ሲንተፋተፉባቸው ፣ እንጉልፋቶ ሆናለች የሚሉት አባባል አላቸው ፡፡ ቢያንስ በአገራችን ጣልያኖችን ከአምስት አመቱ የወረራ ዘመን በኋላ በብዛት ባናያቸውም ፣ ለአገሮቻችን ሰዎች የመኪና ጠጋኞች ወይም ባለጋራዦች ቃላት አውርሰዋቸው ስለሄዱ ፣ እንጉልፋቶን ሰምተን አድገናል  ህወሃት እንጉልፋቶ ብቻ አልሆነችም ፡፡ ብራቾም ሰብራለች ፡፡ ብራቾ የመኪና እግር ላይ በአራቱም እግሮቿ ላይ ያለ አንጓ መሳይ ብይ ነገር ነው ፡፡ ብራቾ ሲሰበር የድሮ ጣልያን ስሪት መኪኖች እግር ልክ እንደ ግመል እግር ጉልበት ለጉልበት ገጥሞ መኪናዋን የንፉቅቅ የምትሄድ ያስመስላታል ፡፡ ህወሃት ዛሬ ብራቾዋ ስለተሰበረ ቢያንስ ኦሮምያ ክልል፣ ውሎ ገባ የነበረው ጉዞዋ ታግቷል ፡፡ የሰላም ባሷ ብቻ ሳይሆን እራሷ ህወሃትም ኦሮምያ ላይ ብራቾ ሰብራለች ፡፡

ህወሃት ብዙ ስሚርኖቪቾችን በህወሀት ማእከላዊ ኮሚቴዎች ውስጥና ፣ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴዎቿ ውስጥ በማስቀመጧ በሙስና እንዲዘፈቁ አድርጋለች ፡፡ አንድ ቀሚስና ጫማ ያልነበራትን ማርያ/ አዜብን ህወሃት ኤፈርት ላይ ሹም በማድረጓ ፣ የሙስና እናት ተብላ እንድትጠራ አድርጋታለች ፡፡ አቶ አሰግደ ገ/ ስላሴ እንዳስነበቡን ከሆነ የህወሃት ቅጥር ሌት ተቀን እየታመሰ ነው ፡፡ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ኃይል እስኪታወቅ ድርስ የዝግ ስብሰባው በአውጫጭኝ አተረማመሰው ዘፈን እየታጀበ ነው ፡፡ በህመም ሰብበ ወደ አሜሪካ የፈረጠጡም ጭምር እንዳሉ አቶ አሰግደ ከዚያው ከወደ ትግራይ ያገኙትን ዜና እያቋደሱን ነው ፡፡ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛውም ክፍል በምሽት አበይት ዜናዎቹ ይኽንኑ የመቀሌ ስብሰባ ውጥረት እያሰማን ነው ፡፡

እንደ ሶቭየቱ የቀድሞ ፖለቲካዊ የምጸት ቀልድ ፣ ትግራይ በመቶኛ የእርከን እድገት ፥ የርሻ ተረፍ ምርት እድገቷ ወዘተ ሁሉ የጨበጣ እንደሆነ የተገማገቡበት ምስጢርና ጉድ ከወደ መቀሌ እየወጣ ነው ፡፡ እንደ ኢቫን አንድሬቭ ኪሮስ ቢተው ፣የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ በትግራይየሌለ የእርሻ ምርት የውሸት ዳታ በማቅረብ ፣ የተፈጥሮ ደን ሽፋን ፥ የመስኖ ልማት ሽፋን የውሸት ዳታ መሆኑ ኪሮስ ቢተውን የሚነካ ሂስ ኣርፎቦታል ይህ እንዳለ ሆኖ ኪሮስ ቢተው የወሸት ልማት ዳታ በማቅረቡ ፣እርዳታ ይሰጡን ለነበሩ ለጋሽ ኣገሮችም የእርዳታ እጃቸው እንዲስቡ ኣድርጓልበማለት ከባድ ሂስ ኣርፎቦታል  ፡፡  መስመር የአቶ አሰግዴ ጽሁፍ እንደወረደ ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንጉልፋቶዋንና ብራቾ ሰባሪዋን ህወሃት አዲስ ኩሽኔታ ገጥሞ ጉዞዋን እንደገና ለማስቀጠል የሚጥሩ ተቆርቋሪ አክቲቪስቶቿ ባይጋ ፎረምና ፣ በትግራይ ኦንላይን ላይ ሳይቀር ገበናችንን ለምን ለጽንፈኞችና / ለጠባቦች አወጣችሁብን እያሉ እያለቃቀሱ ነው ፡፡ ጭራሸ አስቂኙ ነገር ፣ አይጋ ፎረም የዲያስፖራ ጽንፈኞች አንጀታችሁ እርር ይበል ፣ ማርያ/አዜብ መስፍን ተመልሳ ጉባኤው ላይ እንድትገኝ ተደርጋለች የሚል የህጻን ቀልድ ብጤ ብሸሸቅ     ለጣጥፈዋል ፡፡

አይተ ብርሃኔ ካህሳይ የተባሉ ጸሃፊም ስድሳ ሺዎቹን የገበርችው ትግራይ አሸናፊ ሆና እንደገና መውጣት አለባት በሚል  ርዕስ በጻፉት ጽሁፍ ላይ ፣ ብአዴንን ለዚህ ያበቃች ትግራይ አፈር ለብሳ መቅረት የለባትም በሚል ቁጭት ጽፈዋል ፡፡ የማይደፈሩና ፣ የማይገሰጹትንም ባለራእይውንም ሟች መሪ ለዚህ ያበቁን እሳቸው ናቸው  በሚል ንዴት በጽሁፋቸው ሸንቁጠዋቸዋል ፡፡ እንዲህ ይነበባል ፡፡

TPLF begun to lose full control of the EPRDF after the acrimonious schism of its politburo in 2000. Meles obviously consolidated his position but the biggest beneficiaries of this sad state of affair was ANDM which played a decisive part in the departure of the crème de la crème of the TPLF. Although Meles managed to see off of his opponents, he had the misfortune of ending up with law calibre politburo members and this made him prone to undue influence by Addisu Legesse who was the leader of ANDM at that time.

የትግራይ ማንፌስቶ ላይ የተከተበው አማራ ጠል አንቀጽ ሁልጊዜ በትግራይ ብሄረተኞች ላይ በማቃጨሉ አማራ ላይ ጥላቻቸውና ጥርጣርያቸው ጎልቶ ወጣ እንጂ ፣ ዛሬ ዘፈኑ ተቀይሮ ከበድኑ ብአዴን ይልቅ ኦህዴድ ጥርስ አብቅሎ አንበሳው አገሳ እያለ በህወሃት ላይ ክንዱን እያፈረጠም ነው ፡፡  የህወሃት ተዘወሪ መኪና ከንግዲህ ኦሮምያ ክልል ላይ ብራቾ ሰብራለች ፡፡ ከሞያሌ እስከ ሰላሌ የሚጋልበው ዚታዎ ፣ ሸራው እየተፈታ ፣ የጫነው ዳውላ እየተራገፈ ህዝብ ድርሻውን እየተከፋፈለ ነው ፡፡ ኦሮምያ ቢያንስ የታችኛው ሰፊው የኦህዴድ ካድሬና ፣ ወጣቱ ትውልድ ቄሮ አንድ ለአምስት የተጠረነፉበትን የባርነት ሰንሰለት በጣጥሰው እነ-ለማ መገርሳንና ዶክተር አብይን አንታዘዝም እያሏቸው ነው ፡፡ ልከ እንደ ኦህዴድ የብአዴንም የታችኛው አካል ሰፊ ካድሬም ቢሆን ለህወሃትየ በግልጽ ባይታያትም ልቡ ከሸፈተ ቆይቷል ፡፡ ለአብነት ያህል የአማራ ክልል ምክር ቤት ስምንተኛ ጉባኤ ያካሄደው ስብሰባ ላይ ጣናን አስመልክቶ እነገዱ አንዳርጋቸውን ወጥ በወጥ አድርገዋቸዋል ፡፡ የካድሬው የማያፈናፍን ጥያቄ በራሱ ገላጭ ነው ፡፡

ጻድቃንን እና አበበ ተክለሃይማኖትን መልሶ ማስገባት ፣ አባይ ወልዱን ማንሳት ወይ በሞንጆሪኖ መተካት ከንግዲህ የድሮዋን ህወሃት ፈላጭ ቆራጭነት ለማስቀጠል አይረዳም ፡፡ ሻብያ ሱሪና ጫማ አልብሳ ህወሃትን እንዳሰለጠነች ሁሉ ፣ ህወሃት ውራጅ አልብሳ ያመጣቻቸው የብአዴን ካድሬዎችና ፥ ኦህዴዶች እንደ ትላንቱ ሰልቫጅ እየተሰጣቸው ለማገልገል እንደማይፈቅዱ እየታየ ነው ፡፡ እንደ አቶ ሃይለማርያም ትከሻቸውን አስፍተው ለሸክም ጎንበስ የሚሉ ከንግዲህ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ ህወሃት ህመም ላይ ነው ያለችው፣ ቢያንስ ኪሞዋን እየወስደች ከማለፏ በፊት መውደቂያዋን ቦታ ብታሳምር ይሻላታል ፡፡ ኧንደውም አንዳንድ አባላቶቿ ከዘመዶቻችን ኤርትራውያን ጋር ታርቀን መኖሩ ይሻለናል እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት መጽሃፍ ሲወጣ ፣እንዴት እኛን ትግራዋያንን ከኤርትራ ጋር ያጎት ልጆች ናችሁ አልከን ብለው በደራሲው አቶ ዩሱፍ ያሲን ላይ አካኪ ዘራፍ ሲሉ የነበሩ የህወሃት ልጆች ዛሬ ዋስትና  ለማግኘት ትግራይ እጆችዋን ወደ ኤርትራ ትዘረጋልች እያሉ ነው ፡፡ ይህ ሁሉ የህወሃት የሰከረ እና የከሰረ ፖለቲካ ውጤት ነው ፡፡ ኢትዮጵያ የታፈረችና የተክበረች ፣ ለሁሉም ልጆቿ እኩል የሆነች  አገር ትሆን ዘንድ የህወሃት ኪሞ መነቀል   አለበት ፡፡

Filed in: Amharic