>

የነጋሶ ጉዞ፤በመረራ የቡዳ ፖለቲካ መንገድ ላይ

…ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እያናደደህ የምትወደው ጀግና ነው። ያመነባትን እውነት ፤በእኛ ሃገርን ፖለቲካ ውስጥ ሲያስስ የኖረ ሰው ነው። ይመስለኛል። የደምቢዶሎው ልጅ ራሱ እንደሚለው፤ ፖለቲካን የተዋወቃት 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ነው—መምህር ለመሆን AAU ውስጥ በነበረው በእደማርያም ት/ቤት ሲማር። ቀጥሎም በአአዩ ታሪክ ሲማር በተማሪዎች እንቅስቃሴ በመሳተፍ በፖለቲካ ፍቅር ወደቀ።መምህር ሆኖ አይራ ጊሊሶ ት/ቤት ሲያስተምር የፊውዳል ስርአትን የሚቃወም ሰልፍ እየመራ ቆየ።
.
…በኋላም ለሁለተኛና ሶስተኛው ዲግሪ ወደ ጀርመን አቀና።ቦሌ ላይ የሸኘው የቅርብ ዘመዱ ሌንጮ ለታ እንዲህ አለው፤
” አሁንም ታሪክ ልትማር ነው የምትሄደው?”
“አዎን ” አለው፤
“አንተ ታሪክ እስክትማር…እኛ ታሪክ ሰርተን እንጠብቅሃለን።”…በጊዜው ሌንጮ ከነ ታደሰ ብሩ ጋር ኦነግን እየሰራ፤እያቋቋመ ነበር።

ነጋሶ ፍራንክፈርት ውስጥ በገተ ዩኒቨርስቲ ዶክትሬት ድረስ ተማረ።ቴሲስ የሰራው “የደቡብ ምእራብ ወለጋ፤የሰዮ ኦሮሞዎች ታሪክ “በሚል ነው።ጀርመን እያለም እውነትን በፖለቲካ ውስጥ ማፈላለግ ተያያዘ።ኦነግ አውሮፓ ባሉት የኦሮሞ ተማሪዎች ዘንድ ቅቡል መሆን ሲጀምር እሱም ተቀላቀለ። …ነጋሶ የሚፈልጋትን እውነት እዚያ አላገኛትምና ከድርጅቱ ለቀቀ።
.
…የህወሃት ሰዎች የድርጅታቸውን አላማ ለማስተዋወቅ ጀርመንኛ የሚችል ያገር ሰው ሲፈልጉ አገኙት። “ተባበረን “አሉት ተባበራቸው።
በየጊዜው ፓምፕሌቶች ያስተረጉሙት ጀመር።
“ምናይነት ደግ ኦሮሞ ነው” – አመሰገኑት። በዚያውም ለኦህዴድ መለመሉት።እውነትን በኦህዴድ/ኢህአዴግ ውስጥ ሊያስሳትም በሽግግሩ ጊዜ መጣ።ያገኛት ይሆን?
…የሚወደው ታሪክን ተምሮም ታሪክንም ለመስራት ሳይረፍድበት በመድረሱ ደስ አለው።…በሽግግሩ ወቅት ግርማ ብሩ እና ግርማ ው/ጊዮርጊስ አንድ የፖለቲካ ድርጅት መስርተው ነበር።መለስ ዜናዊ ጠራውና ሁለቱን ግርማዎች ለኦህዴድ እንዲመልምላቸው ሹክ አለው።
” አንደኛውን ግን ተጠንቀቀው…ባህርዩን ለማንበብ የማይመች ፤’የሸዋ ዲፕሎማት ይመስላል” አለው።…በነጋሶ ማግባባት ግርማዎቹ የመሰረቱትን ፓርቲ አፍርሰው ኦህዴድን ተቀላቀሉ።
.
…ዶር ነጋሶ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ፣በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆኖ አገለገለ። የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚቴ ውስጥም አባል ተደረገ።…አንድ እለት ኩማ ደመቅሳ ቤቱ እራት ጋበዘው።ዶር ነጋሶ ሲሄድ አባዱላና የኦሮሚያ የያኔው ፕሬዘዳንት ሀሰን አሊም ኩማ ቤት አሉ። ለካ ግብዣው ለእራት ሳይሆን በአዲሱ ህገመንግስት መሰረት ፕረዘዳንት እንዲሆን ነበር።አረዱት።ሆነ።

…ዶር ነጋሶ እንግዲህ ሶሻሊስት ነው። የተቀላቀለው ድርጅትም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ድልድይ ወደ ሶሻሊዝም እንደሚሻገር ነው የሚያውቀው።እሱ ቤተመንግስት ተቀምጦ የሚሆነው ከዚህ ውጭ ሆነበት።ግራ ሲገባው አንድ እሉት መለስ ቢሮ ሄደና፤
” ሶሻሊዝሙስ የት ሄደ ?” አለው፤
“ሎከር ውስጥ ቆልፈንበታል…ለጊዜው የምንከተለው ደረቅ ካፒታሊዝምን ነው።”
እናም ‘ስለተካድኩ ተናደድኩ’ ይላል ነጋሶ።
.
…በ1993 ጅማ ላይ የኦህዴድ ሊቀመንበር የሆነው ነጋሶ ስብሰባ ሊመራ ሲል ፤መለስ ሳያሳውቅ ተከሰተ።
“ስብሰባውን የምመራው እኔ ነኝ”
“ለምን ?”አለው ዶር ነጋሶ፤
“ኢህአዴግ አደጋ ላይ ነው፤አንተ ደሞ በአደጋ ወቅት የመምራትልምዱ የለህም።”
እናም መለስ ስብሰባውን መምራት ጀመረ። በእረፍት ሰአት ጭራሽ ሌላ ነገር በሬዲዮ ሰማ–የአዳዲስ ጄኔራሎችን ሹመት።ይህን ሹመት ማፅደቅ የነበረበት ደሞ ፕረዘዳንቱ ነው።በንዴት መለስ ዘንድ ሄዶ ጮኸበት።እንዴት እንዲህ ይደረጋል?
…ምሳ ሰአት ላይ ግርማ ብሩ ነጋሶን እንዲህ አለው፤”ምንድነው እንደዚያ እየጮህክ ጠሚውን ያናገርከው?”
የሆነውን አጫወተው።ግርማ ብሩ ግን ተረጋግቶ “እኔ አንተን ብሆን ስሜቴን ለመለስ አላሳየውም ነበር።”
…መለስ ያኔ ስለ ግርማ ብሩ ያለው ነገር ታወሰውና ዝም አለ።
.
…የተፈራው አደጋ አልቀረም።ህወሃት ለሁለት ተሰነጠቀች።የመቀሌው ጉባኤ ላይ የእነ ስዬ ረግጦ መውጣት ታወቀ። መለስ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችን ሰብስቦ በደስታ እየተወራጨ ፤
“እነዚያን ቦናፓርቲስቶች ጃኬታቸውን ገፈን አሰናበትናቸው… ” ምናምን እያለ ደነፋ።
ዶር ነጋሶ ለመለስ መልስ ሰጠው፤
” አሁንስ በሁኔታህ…ማእረጋቸውን በመቀስ ቆርጠን፤ቂጣቸውን በጩቤ ወግተን…ያለውን መንግስቱ ኃ/ማርያምን መሰልከኝ…”
…ይሄኔ የድርጅቱ አመራሮች ተደናገጡ።
…ገነት ዘውዴ ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች፤ “ዴሞክራቱን መሪ እንዴት ከአምባገነኑ ጋር ታመሳስለዋለህ!?”አለች።
ነጋሶ ይህን ፓርቲም ጥሎ ወጣ።ምክንያቱም እውነት እዚህም የለችም።በግል ተወዳድሮ ፓርላማ ገባና እውነትን ፈለጋት። የለችም። ‘መድረክ ‘ውስጥም ፈለጋት የለችም።አንድነት ፓርቲ ውስጥም ድራሹዋ የለም።
…ስልጣንን ገደል ግቢ ላላት ታላቅ ሰው “የነጋሶ ህግ”የምትባል አዋጅ አወጁበት። አንድ ፕረዘዳንት፤ሌላ ፖለቲካ ውስጥ ከገባ ጥቅማጥቅሙን የምትነፍግ አዋጅ።ጉዳዩ አልነበረምና በግልም በቡድንም ጉዳዩን አሰሳት።የለችም።
…አዎን! በእኛ አገር ቦተሊካ ውስጥ ስልጣንን ከሻትክ ታገኛታለህ እንጂ እውነት ግን የለችም። ሃብት ከፈለግህ ትጎናፀፋለህ እንጂ ሃቅ ግን የለችም።…ይህን ዘግይቶ ያወቀው ዶክተር መፃፉ ላይ እንደሚለው ፤ጉዞው በፀፀት እና ቁጭት የተሞላ ይመስላል። በቀደም እለትም እነ ለማ መገርሳ “ላመኑበት ነገር ሃቅን ይዞ ፤በእኛ የቡዳ ቦተሊካ መንገድ በመጉዋዝ መታገልና መሸወድ ያለ ነው። አይዞን!” የሚሉት መሰለኝ።ልክ ናቸው?
(ዶ/ር መረራ ጉዲና የእኛን ቦተሊካ አንዱ ቡድን ሌላኛውን ቡዳ የሚልበት ነው፤ይለዋል)

 

Filed in: Amharic