>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9414

እንዲህም ይታሰባል. . (አቻምየለህ ታምሩ)

የሰው ልጅ እየተማረ፣ተሞክሮና ልምድ እያገኘ ሲሄድ በበጎ ምግባርና በመንፈሳዊ ፈቃድ እየተመራ፤በፀዳ አእምሮና ከወገንተኛት ነፃ በሆነ ህሊና እየተመለከተ፤ ያካበተውን ሞያዊ ክህሎትና የቀሰመው የምርምር መሳሪያ አጣምሮ እውነትን ከውሸት ይለያል፤ ወገኑን ከትክክለኛ የሀቅ ከፍታ ለማድረስ ይጥራል።

የኦነጋውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች መማርና ተሞክሮና ልምድ ማግኘት ትሩፋት ግን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የፈጠራ ታሪክና የሐጢዓት ክስ የማምረት እሽቅድምድም ይመስላል። አንዱ ኦነጋዊ ዶክተር የዲግሪ ማሟያ ወረቀቱን ሲያገባድድ ግኝቱን «ምኒልክ ኦሮሞን ጨፍጭፏል» ብሎ ለገበያ ሲያቀርብ ያየ ሌላኛው የመንፈስ ወንድሙ ተነሳና የዚህኛውን ዶክተር ድምጸት ከፍ አድርጎ «ምኒልክ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞ ጨፍጭፏል» ብሎ ሌላ ሸቀጥ አመረተ። በዚህ ፉክክር የተማረከው ጀማሪ ደግሞ አውስትራሊያ ተሻገረና በሌጣው ላይ ዶክተርነት ደርቦ «ምኒልክ አፍሪካዊ ሂትለር ነው» ሲል ሳይማር መጠምጠሙ ሳያንሰው ወሲባዊ ብስጭቱን ወደ ፖለቲካ ለወጠው። ይህ ከታች የምትመለከቱት ደግሞ ማዕረጉ ሳይለብደው፤ ምን ይሉኝ ሳይል ንጉሱንም የቱለማው ተወላጅ የኃይለ ማርያም ወልዴ አያና ገመዳ ልጅ 17 አመታት አንቀጥቅጦ የገዛበትን የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ዘመንም የአማራ የአደረገው።

አንዳንዴ ኦነጋውያንን ሳስባቸው ትላልቅ ህጻናት መስለው ይታዩኛል። በልጅነታችን የምሰማው ሁሉ እውነት ይመስለን ነበር። ኦነጋውያንም ሰውን ሁሉ የሚያስቡት የክህደት ሸቀጣቸውን ከፍቶ የማያይ፤ መረጃና ማስረጃ አገላብጦ እውነቱን የማያወጣና ሳይሞግት የሚቀበላቸው ይመስላቸዋል። ወደ ሀምሳ አመት የሚጠጋ በያዙት ፖለቲካ ኖረውበትና እድሜያቸው የአዛውንት ቢሆንም አስተሳሰባቸው ግን ዛሬም የህጻን ነው፤ የ50 ዓመት ህፃናት። ጨቅላ መሆን ያልፈቀደ በኦነጋውያን መንደር የተወገዘ ነው። በኦነጋውያን መንደር የፈጠራ ታሪካቸውን ለመድገምና በውሸት ላይ ውሸት ለመደረብ ካልሆነ በስተቀር በየእለቱ የሚያመርቱትን የፈጠራ ታሪክ በእውነት መነጸር ለማየት የሚደረግ ጥረት ቢኖር ማንነቱን እንደካደ ይቆጠራል። በኦነግ የፈጠራ ታሪክ ልክ የተሰፋ ጥብቆ ፓለቲካዊ ተክለ ሰውነትን እንደ ማንነቱ ካልተቀበለ ማንነቱ እውቅና የለውም።

ይህ ከታች ሲናገር የምትመለከቱት ግሰለብ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ሕዝቅኤል ገቢሳ ነው። ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ለፈረንጆቹ አማራ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ኦሮሞን በማግለል ጭቆና አስፍኖ ኢትዮጵያን ሲገዛ መኖሩን፤ ለመቶ አመታት ያህል ሲገዙ ሌላውን assimilate በማድረግ ማጥፋታቸው፤ የዛሬዎቹ የአማራ ልሒቃንም አማራ ጨቋኝነትና ኦሮሞን ባጠቃላይ አግልሎ ይገዛበት የነበረውን የድሮውን ለመመለስ እንደሚታገሉ በስሜት ተውጦ ተናግሯል።

የታሪክ ሰዎች የታሪክን ምንነት ሲያስረዱ History has Records of Names, Dates ,Places and Reference to Sources ይላሉ። በዚህ መሰረት እስቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩን ጠይቁት። የትኛው የአማራ ድርጅት ነው የድሮውን ስርዓት ለመመለስ የሚታገለው? እስቲ ይንገረንና እኛም እንወቃቸው።

ፕሮፌሰሩ ስለ አማራ የኢኮኖሚ የበላይነትም ተናግረዋል። ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል። ራስ መስፍን ስለሺን አማራ ናቸው? ራስ መስፍን የጦር አበጋዝ፤ በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን መንግሥት የሸዋና የካፋ ጠቅላ ግዛት እንደራሴ እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ54 ዓመታት ያገለገሉ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ራስ መስፍን ስለሺን የሚያህል የመሬት ከበርቴ አይገኝም። ራስ መሥፍን ስለሺ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት ራስ መስፍን ቁጥ አንድ ሀብታም ነበሩ።

የራስ መስፍን ባለቤት የቄለሙ ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ የልጅ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ የሺመቤት ጉማ ወለጋ ውስጥ ብቻ 500 ጋሻ መሬት ነበራቸው። ከራስ መስፍንና ከባለቤታቸው በተጨማሪ በየአካባቢው የነበሩት በርካታ ፈርጣማ የኦሮሞ የመሬት ከበርቴዎችን ዝርዝር ማቅረብ ይቻላል። አነስተኛ ይዞታዎችን በሚመለከትም የባለቤትነት ዝርዝሩ ቢወጣም አማራው ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ የመሬት ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። በሌላ ጽሁፍ ከነዶሴው በሰፊው እመለስበታለሁ።

ፕሮፌሰር ተብሎ ቀርቦ ይህን ያህል ሲዋሽ ምን አይሰማውም ማለት ነው? ምንም? እንዴት መታደል ነው! «የታሪክ ፕሮፌሰር» እየተባለ በዲግሪ ማማ [terminal degree] ደርሶ ለኃላፊነት እያነሰ፤ የሚስተው እጥፍ ድርብ [exponentially] እየጨመረ ሲሄድ ህሊና ሀፍረት የሚባል ነገር የለም? ግን እንደዚህ አይነት ሰዎች የትኛው የብሎኬት ፋብሪካ ይሆን የሚመረቱት

Filed in: Amharic