>
5:14 pm - Monday April 20, 9693

ህወሃት በመቀሌው ስብሰባ ባድመን ለመስጠት... (በወንድወሰን ተክሉ ልዩ-ሪፖርታዥ)

 

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በመቀሌ ዝግ ስብሰባ ተቀምጦ የነበረው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመለወጥ በሚያስችለው ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ላይ መምከሩ የተገለጸ ሲሆን የባድመን መሬት ለአስመራ የመስጠትና የኤርትራን ተቃዋሚን ማስታጠቅ ማቆም እንደሆነ አፍሪካን ኢንተለጀንስ ዘግባል።
የህወሃት አመራር ባድመን አሳልፎ በመስጠትና ብሎም በኢትዮጵያ ተጠግተው ትጥቅና ስልጠና እየተሰጣቸው ያሉትን የኤትራ ተቃዋሚ ሃይሎችን ማስታጠቁን በማቆም ጉዳይ ላይ ለመምከር የቻለው ድርጅቱ በውስጥና በውጭ ያጋጠመውን የህልውና አደጋን ለመከላከል ነው ከሚል እድምታ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ጉረቤት ሀገራትን እና በተለየም የአፍሪካ ቀንድ ላይ ያነጣጠረው አዲሱ የህወሃት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና በቀጠናው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥነው ልዩ ጥንቅር ቀጥሎ ቀርባል።

**ዓባይ ተኮር ክልላዊ ተጽእኖና ህወሃትን ያፍረከረከው ውስጣዊ የለውጥ ትግል-

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ክፍተኛና ፈጣን የለውጥ ንፋስ ደጋግሞ እየገረፋት ያለችው የአፍሪካ ቀንድ ለብዙዎች የክልሉ ገዢዎች ያልተጠበቀ መቅስፍት እንዳመጣባቸው ሁሉ ለጥቂቶች ደግሞ በረከትን እንደቸራቸው ይታያል።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ውስጥ በኢትዮጵያና በየመን የተፈጠረው ውስጣዊና ውጫዊ የለውጥ ማእበል ከሀገራቱም አልፎ አከባቢውንና ከፊል ምስራቅ አፍሪካን እንዲሁም የመከካለኛው ምስራቅ ፖለቲካዊ ምህዋር በሚያናጋ መልኩ ክልሎቹን ሲንጥ እየታየ ነው።

የለውጡ ማእበል ለህወሃት መራሹ ስርዓትና ለየመኑ ሱኒ መራሹ መንግስት የመቅሰፍት ምርት ያስታቀፋቸው ሲሆን በተለይ-በተለይ ለኤርትራ ድግሞ ያልተጠበቀ በረከት Blessing in disguise ያመጣላት እንደሆነ ክሁኔታው እየተረዳን ነው።
ህወሃት መራሹ ስርዓት ከአቻው የኤርትራ ገዢ ሃይል ጋር እርቅ ለመፍጠር በይፋም ሆነ በሚስጥር ተደጋጋሚ ሙካራዎችን ቢያደርግም በአስመራ እምቢተኝነት ምክንያት እስካሁን ለፍሬ ሳይበቃ እንደቆየ ይታወቃል።

የአስመራ እምቢተኝነት ይህወሃትን የእንታረቅ ጥያቄን በአጠቃላይ ሁኔታ አልቀበልም ከማለት የመነጨ ሳይሆን በህወሃት በኩል ለመታረቂያነት በቀረበው ማስማሚያ ነጥብ ላይ ባለመስማማት እንደሆነ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ።

በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባድመ ለኤርትራ ይሰጥ ዘንድ የተላለፈው ፍርድ የሁለቱ ሀይሎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት የሰመረ እና ያልሰመረ እንዲሆን ዋናው አስካል እንደሆነ ይታወቃል።

በህወሃት በኩል ሲካሄድ የቆየው የእስከዛሬው ምስጢራዊና ይፋዊ የእንደራደር ውትወታ ባድመን ሳንሰጥ እንደራደር በሚል አቃም ቢሆንም በሻእቢያ በኩል ደግሞ በተቃራኒው “የመደራደሪያችን ቁልፍ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሲተገበር ብቻ ነው”የሚል በመሆኑ ፍሬ አልባ ለመሆን በቅታል።

ዛሬ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በተነሱት የለውጥ ማእበሎች አስገዳጅነት ህወሃት ለመጀመሪያ ግዜ ለህልውናው ደህንነት ሲል የባድመን ሁኔታ የሻእቢያን ፍላጎት በማርካት እራሱን ለማዳን ሲል ሊሰጥ እንደተነሳ የሚነገረው ጭምጭምታ ከተተገበረ ከአዳኝነቱ ይልቅ ገዳይነቱ የበለጠ እንደሆነ ለጠንቃይ ግብር ሳንገብር ማወቅ ይቻለናል።
እንደ የአፍሪካን ኢንተለጀንስ ሪፖርት ኢትዮጵያ አዲስ የውጪ ፖሊሲ ያረቀቀች ሲሆን በመጪው ጥር ወር ላይ በካብኔት ምኒስትሮችና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ከተደረገ በሃላ ከስድስት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ የሀገሪታ የውጭ ፖሊሲ ሆኖ ይወጣል ይላል።

በውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራና ልምድ ያካበቱ ዲፕሎማቶችን እንደነ ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቃሚ አምባሳደር፣አቶ ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ በቻይና አምባሳደርና አቶ ሞገስ ተስፋሚካኤል የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ለሰላምና ልማት ኢንስቲቲዩት ፕሬዚዳንትን ያካተተ የዲፕሎማቶች ኮሚቴ በኤርትራና በአፍሪካ ቀንድ ላይ የፖሊሲ ለውጥን ያካተተውን ምእራፍ ያቀፈው አዲስ ፖሊሲ እንዳረቀቁ አፍሪካን ኢንተለጀንስ ያትታል።

መንግስት በኤርትራ ላይ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን ቀደም ሲል ከዓመት በፊት መግለጹ አይዘነጋም።

አዲሱ ፖሊሲ ኢትዮጵያ እስከአሁን ከኤርትራ፣ግብጽ፣የመን፣ሳኡዲ ዓረቢያ፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ሶማሌ እና ሶማሌ ላንድ ጋር ስታደርግ ከነበረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፖሊሲ የተለየ እንደሆነ ይነገራል።

ከ2011 ጀምሮ በቀጠናው ከተከሰቱት ወሳኝ ክስተቶች ውስጥ በኢትዮጵያ የዓባይ ግድብና ከሁለት ዓመት በፊት የተነሳው ሕዝባዊ ዓመጽ ሲሆን በየመን የሺዓ ሁቲዎች የሚመራ ሃይል ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በሳኡዲ ዓረቢያ መራሹ የሱኒ ህብረ ብሔር ጦር ውጊያ መከፈቱ ለዛሬው ህወሃት መራሹ መንግስት አካባቢውን ያማከለ አዲስ የውጭ ፖሊሲ እንዲያረቅ እንዳደረገው መገመት ይቻላል።

በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል በህዳሴው ግድብ ላይ የተፈጠረውን ውዝግብ በሚያስማማ ሁኔታ ሳይቃጭ በየመን የተፈጠረው ክስተት የግብጽና የሳኡዲ ዓረቢያን ወታደራዊ ህብረት ከመፍጠሩም በላይ የሀገራቱ [የግብጽ] ጦር ሃይል በኤርትራ አሰብ፣በሶማሊያ ቦሳሶና ሞቃዲሾ የጦር ተቃም እንዲከፍቱ ስላደረጋቸው ህወሃት መራሹ መንግስት ለውጪ ሃይል ስውርና ግልጽ ጥቃት ተጋልጫለሁ ብሎ እንዲያምን አድርጎታል።
በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተነሳው ህዝባዊው የለውጥ ማእበል የህወሃት መራሹን መንግስት ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ የሚለውን አጠቃላይ የትግራይን ህዝብ ህልውና ለከፍተኛ አደጋ አጋልጣል በሚል አቃም የመፍትሄ አቅጣጫ መፈለግ ከጀመሩ ስነባብተዋል።

ሰሞኑን በመቀሌ ሲካሄድ በነበረው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ዝግ ስብሰባ ላይ ለውይይት ከቀረቡት መወያያ ነጥቦች ውስጥ ስርዓቱ ከኤርትራ ጋር በሚኖረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ እንደመከሩ ድረ-ገጹ ያትታል።

የህወሃት አመራር የባድመን ለኤርትራ በማስረክብ ሁኔታ እና የኤርትራ ተቃዋሚዎችን የማስታጠቅ ሂደትን በማቆም ሂደት ላይ እንደተወያየ ይነገራል።

ሁለቱም የመወያያ ነጥቦች በህወሃት መራሹ መንግስትና በአስመራው መንግስት መካከል ላለው Nowar,No peace ፖሊሲ መሰረተ ድንጋይ ሆኖ እያገለገለ ያለ ተግባር ሲሆን የአስመራውን አገዛዝ ወዳጅ ለማድረግ “መውሰድ የሚገባን እርምጃ ነው” በሚል አቃም ላይ መድረስ ብቻ ሳይሆኑ በነጥቡ ላይ ለመወያየት መብቃት በራሱ የህወሃት ድርጅታዊ አቅምና ሃይል ክፍኛ መዳከሙን አመላካች እውነታ እንደሆነ እናያለን።

ለህወሃት መራሹ ስርዓት በተለይም የትግራይን ህዝብ ህልውና ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠው የህወሃት የሀገር ውስጥ አገዛዝና ፖሊሲ የፈጠረው ሕዝባዊው ዓመጽ እንጂ ውጪኛው ሃይል እንዳልሆነ እናያለን።ሆኖም ይህንን ውስጣዊ አመጽ ለግል ዓላማቸውና ጥቅማቸው ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብለው በዓይነ ቁራኛ እየተጠበቁ ካሉት የውጭ አስጊ ሃይሎች ውስጥ ግብጽና ኤርትራ ግንባር ቀደም ሲሆኑ የሁለቱን ጸረ ህወሃትነትን ለመነጠል ከግብጽ ይልቅ ለኤርትራ መከፈል ያለበት ዋጋ አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ አነስተኛ ነው የሚል ግምገማ በህወሃት በኩል ተመራጭ ሃሳብ እንደሆነ ይገመታል።

የህወሃት ትልቁ ጭንቀት በውስጥ የተፈጠረበትን የህልውና አደጋ ሳኡዲን ከጎና ያሰለፈችው ግብጽ ኤርትራን፣ሞቃዲሾን፣ደቡብ ሱዳንንም በመጠቀም በዓባይ ላይ ያላትን አቃማን ህወሃት መራሹን መንግስት አንበርካካ ታስፈጽምበታለች የሚል ይመስል የአስመራው ሰውዪ የሚጠይቀውን ሁሉ በመስጠት ከግብጽ አፋትቶ ከህወሃት ጋር ማጋባት በሚል ስሌት ከተመሩ በእርግጥም ባድመም ለአስመራ ልትሰጥ ተወስናል-በኢትዮጵያ ያሉ የኤርትራ ተቃዋሚዎችም ስንቅና ትጥቅ መከልከል ብቻ ሳይሆን ምድሪታንም ይለቁ ዘንድ ት እዛዝ ተዘጋጅቶላቸዋል ልንል እንችላለን ማለት ነው።
ነገር ግን-ህወሃት ባድመን ለኢሳይያስ አስረክቦ ከግብጽ መራሹ ጸረ ህወሃት እርምጃ እድናለሁ ቢልም-በከፊል ቢሰራለትም ባድመን በመስጠቱ በተመሳሳይ መልኩ ከኢትዮጵያዊያን በኩል ከሚሰነዘርበት ጥቃት ህልውናውን መከላከል እንደማይቻለው የተገነዘበ አይመስልም።

Filed in: Amharic