ይብላኝልህ ላንተ – ተኝቷል እስረኛ!!
ከታጠቅከው ክላሽ – ከጥይት ያለፈ
እውነትን አስታቅፎህ – እጅግ የገዘፈ
በፍፀም ሠላም ውስጥ – ለ….ሽሽሽ ብሎለሃል
በእርካታ ተሞልቶ – እስረኛው ተኝቷል!!
ተኝቷል እስረኛው – ሃሳቡን አራግፎ
ባንተ ህሊና ውስጥ – ሐቅ እውነቱን ፅፎ፡፡
አወይ አለማወቅ …
ለአሳሪው ነው እንጂ – ሰቀቀኑ ጭንቁ
መቼ ታስሮ ያውራል – የእስረኛው ሐቂቁ፡፡
አንዳንደዜ ሰዎች – ሐቅን ይስታሉ
እውነትን ሳይለዩ – ታሰረ ይላሉ!!
ሰዎች ምን ነካቸው – ታሠረ የሚሉ – ቃል የሚያቃልሉ
እንዴት ይታሰራል – እውነት ያለ ውሉ!?
ማነው የታሰረው – ማነው እስቲ ነፃ
ቀኑን የሚያቃዠው – ሌት የሚያባትተው – የእውነት ፍላፃ
አሳሪውን እንጂ – የሚስበረግገው
ሰላም ነው ህሊናው – ታሳሪ ሚባለው!
ደግሞስ በምን ተዓምር – ማቆምስ ይቻላል
እውነት እንዴት ሆኖ – በምን ይታሰራል!?