>

ከአል-አሙዲን ሀብት ጀርባ ያሉ ሃይሎችና የሀብቱ መነሻ ምንጭ ሲፈተሽ (ወንድወሰን ተክሉ)

**መንደርደሪያ-እውነታ-

የሰለሞን እጽነሽ የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል
ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል
**ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ**

ዘውድ ያልደፉት ቱጃር አል-አሙዲን አይሆንም ወይም ሊሆን አይችልም የሚባል ክስተት አጋጥማቸው ዜግነትን በመረጡበት ሀገራቸው ሳኡዲ ዓረቢያ ከተቀፈደዱ ሳምንት አለፋቸው።

የ71ዓመቱን ቱጃር ህይወት በሶስት የህይወት ክፍል ክፍያ ላስቀምጠው እወዳለሁ።

1ኛ-ቱጃሩ ከተወለዱበት እስከ ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ የተሰደዱበት የልጅነት ዘመን የሆነውና የ20ዓመታት ቆይታ ግዜን የሚሸፍነው ወቅት ነው። በዚህ ዘመን የእሳቸው ደረጃ [እስታተስ] ታዳጊ ተማሪ ፣አባት አልባና ስደተኛ ደረጃ ላይ እንደነበሩ እንረዳለን።
ዘመኑም ከ1939-1959 ዓ.ም ሲሆን ስፍራውም በኢትዮጵያ እንደሆነ እንረዳለን።

2ኛ-በ25ዓመት ዘመን የተከፈለውና ሁለተኛው የህይወታቸው ዘመን ሲሆን ዘመኑም ከ1960-እስከ 1985ዓ.ም ያለውን ግዜ የሚያመላክት ሲሆን ስፍራውም በሳኡዲ ዓረቢያ መሆናቸውን ያወቅንበት ወቅት ነው።
በዚህ የህይወታቸው ዘመን ቱጃሩ የዜግነት ለውጥ አድርገው ሳኡዲ ዓረቢያዊ የሆኑበትና በሀብት ደረጃም በባንክ፣ኮንስትራክሽን እና ነዳጅ ጉድጋድ 1.5ቢሊዮን ዶላር ሀብት ያፈሩበት ዘመናቸው ሲሆን
የሀብታቸው ስፍራም ሳኡዲ ዓረቢያ፣ስዊዲን፣ሞሮኮና እንግሊዝ እንደሆነ እናያለን።

3ኛ- በ25 ዓመታት የህይወት ዘመናቸው የተሸፈነ ሲሆን ይህም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከመጡበት 1985 እስከ ዛሬ 2010ድረስ ያለውን የህይወታቸው ዘመን ያወቅንበት ሲሆን የሀብታቸው መጠንም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ካላቸው 1.5ቢሊዮን ዶላር ዓስር እጥፍ አድጎ ባለ 15.3ቢሊዮን ዶላር ባለቤት የሆኑበት የህይወታቸው ወርቃማው ዘመን እንደሆነ እናያለን።
የሀብታቸው ስፍራም ኢትዮጵያ፣ዮጋንዳ፣ጂቡቲ፣አሜሪካ፣ሳኡዲ፣ሞሮኮ፣እንግሊዝ፣ስዊድን እንደሆነ እንረዳለን።

ዛሬ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆኑት ቱጃር ለገናና የሀብት ዝና ያበቃቸው የህብት ምንጭ ባለፉት 25ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የከፈታቸው ከ70በላይ ድርጅቶቻቸው አማካይነት እንደሆነ ከኢኮኖሚያዊው እድገታቸው ታሪክ ቅደምተከተል ላይ መረዳት ይቻለናል። የአል-አሙዲን ትልቁ የሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች በዚህ አጋጣሚ ቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ።

******

በንጉሳዊው የሳኡዲ መንግስት በሙስና ተከሰው በእስር ያሉትን ትውልደ ኢትዮጵያዊውን አል-አሙዲን የመታደግ ዘመቻን መንግስት በይፋ መጀመሩ ተሰምታል።

የሳኡዲ ዓረቢያዊው ቱጃር በህገሩ መታሰር ምክንያት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? ደግሞስ ለመታደግ መፈለጋቸው የሚቻላቸው ነውን ?የሚሉ ጥያቄዎችን መልስ ፍለጋ ስንባዝን ዘርፈብዙ የቱጃሩን እና የህወሃትን ታሪክ እንድንይ እንገደዳለን።

**የአል-አሙዲን እና ህወሃቶች ምስጢራዊ ግንኙነት መነሻ–

ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው አሜሪካዊ፣ካናዳዊ፣አውሮፓዊና የሌሎችም ሀገራት ዜጎች የሆኑ የውጪ ዜጎች ቁጥር በአስር ሺህ የሚቆጠሩና በኢትዮጵያ ውስጥም በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ያሉ ቢኖሩም አንዳቸውም ቢሆኑ ቱጃሩ ያገኘውን መብት፣ጥበቃና እንክብካቤን አምስት ፕርሰንት እንካን እንዳላገኙ ይታወቃል።

ቱጃሩ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያዊው ይበልጥ ተንቀባረውና ያሻቸውን ሆነውና አድርገው እንዲስተናገዱ ተደርገዋል። በ1980ዎቹ ውስጥ እሳቸውና ህወሃት የሀገሪታን አንጡራ ሀብትን መንግስታዊ ድርጅቶችን ፕራይቭታይዝ ማድረግ በሚል ስም እኩል ሲቀራመቱ ከህወሃት ጋር ታግለናል ያሉት ብአዴኖች የበይ ተመካች ከመሆነ ያለፈ ነገር የደረሳቸው አልነበረም።

በሻኪሶ የሚገኘው የለገደንቢ ወርቅ ማእድን በዓመት ከ5ሺህ ቶን በላይ ወርቅ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡበትን የሀብት ምንጭ በ48ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንዲገዙ ተደርገዋል።

የሚገርመው በሕገ መንግስቱ ባንክ፣ኢንሹራንስ፣ማእድን ወዘተ ለውጪ ዜጎች የሚፈቀድ አይደለም ቢልም ለቱጃሩ ግን ኢትዮጵያዊነታቸውን በሳኡዲ ዓረቢያዊ ቀይረውም የተቻለ ቀላል ነገር ነበር የሆነው።

በነገራችን ላይ የሳኡዲም ሆነ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የጥምር ዜግነትን እውቅና የማይሰጥ ቢሆንም ቱጃሩ ግን የሁልት ሀገር ዜግነትን በመጎናጸፍ ሲምነሸነሹ ቆይተዋል።

ህዋታዊያን ገና በጫካ ደረጃ እያሉ ከቱጃሩ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።ቱጃሩ በዓረቡ ዓለም በተለይም በሳኡዲ ዓረቢያ የህወሃት ተወካይ በመሆን የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡ እንደነበረ የሚያስረዱ መረጃዎች ቢኖሩም በሁለቱም ወገኖች [በህወሃትም ሆነ በቱጃሩ በኩል ማለቴ ነው] በኩል ለህዝብ ይፋ እንዳልሆነ ይታወቃል።

አል-አሙዲን በወሎ ወልዲያ በ1939ዓ.ም እንደተወለዱ የሚታመን ሲሆን አባታቸው የሳኡዲ ዜግነት ያለው የመናዊ ሲሆን እናታቸው በወሎ የትግራይ ተወላጅ እንደሆኑ ይነገራል።

ቱጃሩ በአንድ ወቅት በእናታቸው የትግራይ ተወላጅ መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም ያለኝ መረጃ እንደሚያስረዳው ግን ቱጃሩ የእናታቸውን አባት የዘር ግንድ ሳይሆን የእናታቸውን እናት የዘር ግንድ ቆጥረው የትግራይ ተወላጅነታቸውን እንደመረጡ ነው እንጂ መረዳት የቻልነው የአል-አሙዲን እናት አባት የአማራ ተወላጅ መሆናቸው ይነገራል።

እናታቸው እና አባታቸው ገና በልጅነታቸው እንደተለይዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አል-አሙዲን የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት አባታቸው ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ ጉዞ ላይ እንዳሉ በዛሬዋ ኤርትራ እንደሞቱና እንደተቀበሩ የቱጃሩ አብሮ አደግና የክፍል ባልደረባ ከ17ዓመታት በፊት በሸራተን አዲስ አጫውቶኛል።

**የአል-አሙዲ ወደ ሳኡዲ ጉዞ

በ1958 የ12ኛ መልቀቂያ ፈተናን በወሰዱ ዓመት በሃላ ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ ሪያድ ያቀኑት የዛሬው ቱጃር በጣም እድለኛ ከመሆናቸው የተነሳ በወቅቱ የትምህርት እድል በማግኘታቸው መጀመሪያ የባንኪንግ ትምህርትን በሪያድ ንጉሳዊያን እና ባለሀብት ቱጃር ልጆች በሚማሩበት ትምህርት ቤት እንደተማሩ ይነገራል።

በወቅቱ [በሪያድ ተማሪነታቸው ዘመን ማለቴ ነው] ቱጃሩ ከታዋቂው አሸባሪ ቢን ላደን ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው እንደተማሩ የሚያስረዱ መረጃዎች ደርሰውናል።

በ1999ዓ.ም ላይ የአሜሪካው ጋዜጣ [USA Today ]ሼህ ሁሴን ሞሀመድ አል-አሙዲን ለቢን ላደን የ$5ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በዓመት እያደረጉ ነው የሚል ክስ ሲያሰማ ሁላችንም [የነጻው ፕሬስ አባላት]ይህ የግብጽና የኤርትራ ደላሎች ጸረ ኢትዮጵያ ክስና ጥቃት ነው በማለት እየተቀባበልን ተከላክለናል-ተጫጩህናልም። ስንጫጫህ የቱጃሩን ንጽህና አምነንበት ሳይሆን ባለን ውስን መረጃ መሰረት ቱጃሩ ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም ስራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው መከላከል የዜግነት ግዴታችን ነው በሚል እምነት እንደሆነ አስታውሳለሁ።

ድርጊቱ ከተከሰተ ወራት በሃላ በአቶ ጌታቸው ክብረስላሴ አስተዋዋቂነት ቱጃሩ ጋር በሼራተን አዲስ በተዋወኩበት እለት አቶ ጌታቸው ነጻው ፕሬስ በአጠቃላይ የመከላክል እርምጃ ወስዳል በማለት ሲነግራቸው እሳቸውም እኛን አሞግሰው የአሜሪካዊውን ጋዜጣ ተግባር በማጣጣል ገልጸው ገልጸውልኝ ነበር።

እኔ በወቅቱ ቱጃሩን ለቃለ መጠይቅ የማሳድድበት ወቅት ነበር። እሳቸውን ማግኘት ጠ/ሚ መለስን ለማግኘት ያህል ሆኖብኝ በአይቻልም ስሜት እንድሞላ ቢያስገድደኝም አንድ ቀን በዚሁ ሆቴላቸው አገኛቸዋለሁ በሚል በኪሴ ሳይሆን በአእምሮዪ እየተመራሁ የሸራተንን ዘርፈ ብዙ ክፍሎችን ማታ ማታ ማሰሱን ስራዪ ብዪ ተያይዤዋለሁ።

በዚህ ተግባሬም የሼራተን ሆቴል ሴኩሪቲ ዲፓርትመንትና ዋና ስራ አስኪያጁም ድረስ ታውቄ ማስጠንቀቂያ የተሰጠኝ ወቅት ነበር።

እሳቸውን ማሳደዱን ሳላቆም በዚያው በሸራተን ልዩ ልዩ ክፍሎች እሳቸውን ባገኝ በሚል እየዞርኩ ባለሁበት የህዳር 1993ዓ.ም ላይ ዶ/ር አብዱል መጂድ ሁሴንን አግኝቼ በግድ ማለት ይቻላል ቃለ መጠይቅ በማድረግ በኢትኦጵ መጽሄት ላይ የፊት ሽፋን በማድረግ እንዲወጣ አደርጋለሁ ።

መጽሄቱ ከታተመ በሃላ ነው እንግዲህ በወቅቱ የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ክብረስላሴ ተዋውቀውኝ እኔንም ከቱጃሩ ጋር እነ የሀባስ ትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት አቶ አብዱላሂ ዩሱፍ፣አቶ አረጋ እና ሌሎች የዘነጋሃቸው ሰዎች ባሉበት በታህሳስ ወር ላይ በ1992 ዓ.ም ቱጃሩን የተዋወኩት።

እንደ እድል ሆኖ ሳምንት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ሁለት ግዜ ስንገናኝ ኢንተርቪው እንዲሰጡኝ ብሞግት ፣ብለምን ተቀባይነትን አጥቼ ቃል መጠይቁን ባላደርግም በዚያው አጋጣሚ ያገኘሃቸው ቅንጥብጣቢ መረጃዎችን ግን ለንባብ ሳላበቃ ሙሉ ስብእና እስኪያገኙ በሚል ያስቀመጥካቸው ጠቃሚ ነበሩ።

እሳቸውን በተዋወኩ ሳምንት ግዜ ውስጥ አንድ ሌላ እንግዳ እዚያው ሸራተን አዲስ እንግዳ መቀበያ ቀርቦኝ እርዳቴዪን እንደሚፈልግ ይገልጽልኛል፡ይህ ሰው በእድሜ የገፋና የቱጃሩ አብሮ አደጋቸውና ብሎም የክፍል ባልደረባቸውም የነበረ እሀገር ውጪም በሳኡዲ ለተወሰኑ ዓመታት በቅርብ አብሮ የነበረ ሰው እንደሆነ በመግለጽ ዛሬ ግን እሳቸውን የማግኘት ችግር እደገጠመው በመግለጽ እንዳገናኘው ይጠይቀኛል።

ሰውዪው እኔን ለምን እንድረዳው እንደመረጠኝ አልጠየኩትም ግን እንግዳ መቀበያ ተቀምጦ የእኔን በሆቴሉ ውስጥ ወዲያ ወዲህ መራራጥ ተመልክቶ ቱጃሩ የሚገኝበትን ያውቃል ብሎ እንደገመተ ገምቼ ማስረጃ እንዳለው ጠየኩት።

የቱጃሩ አብሮ አደግም የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት እሱ ቱጃሩና ሌላ አንድ ተማሪ ሆነው የተነሱትን ፎቶ አሳይቶኝ ከእሳቸው ጋር በማገናኘቱ በኩል እንዳግዘው አጥብቆ ይጠይቆኛል።

ቱጃሩ በ1960 መጀመሪያ ወይም በ1959መጨረሻ ላይ ወደ ሳኡዲ እንደሄዱ የገለጸልኝ ሲሆን እሱ ግን ከሁለት ዓመት ቆይታ በሃላ በ1962ዓ.ም ወደ ሳኡዲ እንደሄደ ተናግራል።

በነገራችን ላይ በዚህ በ1957/8በተነሱት ፎቶ ላይ ሶስት ወጣቶች ውስጥ የዛሬው ቱጃርና ቢሊየነር ብቻ በቁምጣና ያለጫማ ሆኖ ያየሁ ሲሆን ሁለቱ ወጣቶች ግን ባለጫማና ባለ ቦላሌ/ሱሬ/ የለበሱ መሆናቸውን አይቻለሁ።

ሰውዪውን ከአብሮ አደጉ ቱጃር ጋር ማገናኘቱን ሁኔታ ሳልፈጽም ከአል-አሙዲን ጋር 3ኛ ዙር የመገናኘት እድል ሳላገኝ ተራርቀን ብንለያይም [ዳግም አላገኘሃቸውም ] በወቅቱ ግን የሰማሁትን የአል-አሙዲን ታሪክ መዝግቤ አስቀምጬው ስለነበረ ዛሬ ከማስታወሻዪ ላይ እየቀነጫጨብኩ መጠቀሜን ለመግለጽ ነው የላይኛውን ታሪክ ለመግለጽ የቻልኩት።

**የአል-አሙዲን ሀብት ምንጭ መነሻ-

በታህሳስ 1992 ዓ.ም ላይ ባሰፈርኩት የማስታወሻ ደብተሬ ላይ “ዘውድ ያልጫነው ንጉስ” በሚል አርእስት ስር ሰውዪው በወቅቱ ያቃቃማቸውን ወደ 18 የሚጠጉ ዘርፈ ብዙ ድርጅቶቹን [ዛሬ ከ18ዓመት በሃላ እነዚህ ድርጅቶች ወደ 70ደረጃ አድገው ተመንድገዋል]ባሰፈርኩበት ምንጩን አስፍሬያለሁ።

ሰውዪው [ቱጃሩ ማለቴ ነው-የማስታወሻ አርእስቴ ሰውዪው የሚል ነውና]በሳኡዲ ሪያድ በአንድ ስሙ ባልተጠቀሰ ልኡል እስፖንሰርነት የአካውንቲንግ ትምህርት ከተማሩ በሃላ በመጀመሪያ የተሰማሩበት የስራ ዘርፍ የባንክ አገልግሎት ላይ እንደሆነ እኚህ አብሮ አደጋቸው ሰውዪ ይናገራሉ።

በተሰማሩበት የባንክ አገልግሎትም ጠቀም ያለ ገንዘብ በመያዝ የራሳቸውን ባንክና ኮንስትራክሽን ድርጅት በማቃቃም በነዳጅ ቁፋሮ ተግባር ላይ መሳተፍ እንደጀመሩ ቢነግሩኝም የባንክ ሰራተኛ በነበሩበት ወቅት ለዛሬው ቢሊዮነርነት መነሻ የሆናቸውን ጥሪት እንዴት እንደቃጠሩም አብሮ አደጋቸው ከመግለጽ ወደ ሃላ አላሉም።

ሰውዪው በባንክ ሰራተኛነታቸው መንደርደሪያ ጥሪት መቃጠር የቻሉበት ስራ ገንዘብ በማሸጋገር ተግባር [Money laundering] ሲሆን በወቅቱ በ1970ዎቹ ማለት ነው በአፍሪካ፣በዓረቡ ዓለም እና በዓለም ላይ ከፍተኛ የነጻነትና የመብት የትግል እንቅስቃሴ እያደረጉ የነበሩ በርካታ የአርነት መሰል ታጋይ ድርጅቶች በገፍ የነበሩበት ወቅት ሲሆን ለድርጅቶቹ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ በማበርከት ጠርቀም ያለ ጥሪት ለመያዝ እንደቻሉ አብሮ አደጋቸውና በሳኡዲም አብረው የነበሩት ሰውዪ ገልጸውልኛል፡፣

ቱጃሩ በባንክ ሰራተኝነታቸው በገንዘብ ማዘዋወር ተግባር ጠርቀም ያለ ገንዘብ ከያዙ በሃላ የራሳቸውን ባንክና የነዳጅ ቁፋሮን የሚያከናውን ኮንስትራክሽን እንዳቃቃሙ ይናገራሉ።

ይህን የባንክ ስራቸን እና የኮንስትራክሽን ስራቸውን ይዘው የነዳጅ ጉድጋዶችን ከመቆፈርም አልፈው በመለስተኛ ሽርክና የነዳጅ ማውጪ ጉድጋድ ባለቤት መሆን እንደቻሉ የኢንቨስትመንት እድገታቸው ታሪክ ያስረዳል።

በሳኡዲ ያላቸውን የሀብት መጠን በዚህ መልክ መሰረት ካስያዙ በሃላና በስዊዲን እና በሞሮኮ በነዳጅ ስራ ላይ ከተሰማሩ በሃላ ግን በአጠቃላይ ከሀገራቸው ከወጡ ከሃያ ዓመት በሃላ የመጀመሪያውን አንድ ቢሊዮን ዶላር መቁጣር እንደቻሉ ነው በእሳቸው አንደበትም ተነግሮ ሰምተናል። [አል-አሙዲን በራሳቸው አንደበት የሀብታቸውን መነሻ ያልተናገሩ ሲሆን ከ20ዓመት በሃላ 1ቢሊዮን ዶላር መስራታቸውን ገልጸዋል]

ሆኖም ቱጃሩ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት በ1984ዓ.ም ላይ ባለ1.4ቢሊዮን ዶላር ባለሀብት እንደነበሩ ከሁሉ በፊት ማስተዋል የሚገባን የዛሬውን ሀብት 15.3ቢሊዮን ዶላር ምንጭ የምንፈትሽበት ስለሆነ ነው ልብ ልንል ይገባል።

**የህወሃትና አል-አሙዲን ግንኙነት-

ሰውዪው ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት ቢሊዮን ዶላር የቆጠሩ ቱጃር ቢሆኑም ግን ከህወሃት ጋር መገናኘት የጀመሩትና ሲረዱ የታዩትም ገና ቢሊዮን ደረጃ ሳይደርሱ ህወሃቶች ጫካ እያሉ እንደሆነ በተጨባጭ መረጃም መረዳት ችያለሁ።

ድርጅቱ[ህወሃት ማለቴ ነው]በይፋ ለኢትዮጵያ ህዝብ በድርጅቱና በአል-አሙዲን መካከል ያለውን ግንኙነት በይፋ ባይገልጽም በግል በተለያየ መድረክና ግንኙነት ላይ ግን የግንኙነታቸውን ስር የሰደደ መሆን ሲገልጹ አድምጫለሁ።

አምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ፣ህልዊ ዮሴፍ፣ዶ/ር ክንፈ አብርሃ እና አንዳንድ አነስተኛ የህወሃት ካድሬዎች የህወሃትና የቱጃሩ ግንኙነት ስር የሰደደና ከጫካ ጀምሮ የሆነ መሆኑን በተለያየ መድረክና ስፍራ ጠይቄያቸው ያረጋገጡልኝ ሲሆን ሲያደርጉላቸው የነበረውን የድጋፍ መጠን በአሃዝ መግለጽ እንደማይቻላቸው ገልጸው ግን የቱጃሩ አስተዋጽኦ ከፍተኛና ወሳኝ እንደነበረ ያሰምሩበታል።

በ26ቱ ህወሃት መራሹ አገዛዝ ወቅት አንዳችም አለመግባባትና መስናክል ሳያጋጥመው በጠበቀ ግንኙት የቀጠለ ፖለቲካውና ኢኮኖሚያዊ ግንኙት የህወሃት-አል-አሙዲን ግንኙነት ብቻ ሲሆን በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ጥሎ የውጭ ዜግነትን ለተቀበለ ሰው ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በላይ የቀጠለ ታላቅ የኢንቨስትመንት ፍሰትና መንግስታዊ ልዩ ጥበቃን የተጎናጸፈ ብቸኛው ሰውና ተቃም አል-አሙዲን እና ድርጅታቸው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።

ለምንድነው ይህን መሰል ስር የሰደደና ጥብቅ ወዳጅነት በሁለቱ መካከል ሊኖር የቻለው ብለን ስንጠይቅ መልሱ በጫካ ደረጃ የተመሰረተው ወዳጅነትና በቱጃሩ እናት በኩል በተቆጠረ የዘር ዝምድና ምክንያት ነው የምንል ብንሆንም እውነታው ግን ከዚህም በላይ ያለፈ ምክንያት እንዳለ ያሳየናል።

ለህወሃታዊያን ይህ የዘር ግንኙነትና የቆየ ወዳጅነት ብቻ ለዘላቂ ወዳጅነት የሚያበቃ አለመሆኑን የህወሃትን ሰነተፈጥሮና ባህርይ የምናውቅ ሁሉ ጠንቅቀን እናውቃለንና ሌላኛው ምክንያት ምን ይሆን ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል።

ህወሃት ባለስልጣናቱንም ሆነ ባለሀብቶችን እንደ ሸንኮራ መጥጦ በመትፋት ታሪኩ በጣም ይታወቃል። እንደነ ዶ/ር እሸቱ [ዩኒቲ ኮሌጅ]የአዲግራት መድሃኒት ፋብሪክ፣እስታር ቢዝነስ ግሩፕና መሰል ብቅ ብቅ ያሉ ባለሀብት ሆንን ያሉ ሰዎችና በአምስት ደርዘን በላይ የሚቆጠሩ ባለስልጣናት እንደሸንኮራ እየተመጠጡ ባለፉበት ሁኔታ ታኝኮና ተመጦ ያልተተፋ እጅግ ጠቃሚ ባለስልጣን፣ባለሀብትና ምሁር ማነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችን ስም ሲሆን ቱጃሩ አል-አሙዲን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እንደሆነ እንረዳለን።

ሰውዪው ባቃቃማቸው ከ70 በላይ ድርጅቶች ውስጥ ከ50ሺህ በላይ ሰራተኞችን እያስተዳደሩ ያሉ ባለሀብት ስለሆኑ ነው ወዳጅነታቸው እየጠበቀ ያለው እያልካችሁ እንዳልሆነ ተረዱሉኝ። በአንጻሩም ህወሃት ክሰውዪው የሚያገኘው ጥቅም እያደገ በመምጣቱና ያም ጥቅም ውስብስብና ምስጢራዊ በመሆኑ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት እስከዛሬ ድረስ ያለምንም እንከን እንደቀጠለ ነው መረዳት የምንችለው።

በ1984 ዓ.ም[1992] ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ብዙም ሳይቆዩ የአል-ታድ ታላቅ ውጥን የተባለለትን ፕሮጄክት ከታዋቂው ኢትዮጵያዊ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ጋር በሽርክና ስራ ሸራተን አዲስን በ$200ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት ባስተዋወቁበት ዓመት ቱጃሩ ባለ 1.4ቢሊዮን ዶላር ባለቤት እንደነበሩ የምናስታውስ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ብንሆንም እወነታው ግን የሚረሳ አይደለም።

በአቶ ታደለ ይድነቃቸው ግንባር ቀደም ተሳትፎ ከታላቁ ቤተመንግስት በታች ያለውን ታሪካዊ ቦታ [በጣሊያን ግዜ በመቶ በርሚል የሚቆጠር ጠገራ ብርና ማርትሬዛ ተቀብሮበታል ተብሎ የሚታወቅ ሰፈር ነው] ከያዙ በሃላ ቱጃሩ በኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ታደለ ይድነቃቸው ላይ ባለስልጣናቱን በመጠቀምና ታላቅ ክህደት በመፈጸም ከሽርክና ውጪ ካደረጋቸው በሃላ ፕሮጄክቱን ጠቅልለው ተቆጣጠሩ።

በነገራችን ላይ የቱጃሩና የህወሃት ጥብቅ ቁርኝትና ፍቅር አቶ ታደለ ይድነቃቸው ያቃቃሙትን ይድነቃቸው ኮንስትራክሽንን በሀገር ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ እስከማገድ [ስልታዊ ማገድ]አድርሶ አቶ ታደለ ያላቸውን ግዙፍ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ማሽኖችን እያከራዩ ለመኖር ተገደው እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፣

ህወሃት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሶስት አቅጣጫ በሞኖፖል ደረጃ የተቆጣጠረ ሆኖ ሳለ ለዓለምና ለኢትዮጵያዊያን ግን የማራምደው ነጻ ገበያና የግል ባለሀብትን እየፈጠርኩ ነው ሲል ይደመጣል።

ስርዓቱ ኢኮኖሚውን በሞኖፖል ደረጃ የተቆጣጠረበት የሀብት መቆጣጠሪያ ክፍልም –

1ኛ-በህወሃት መራሹ ድርጅቶች ስር
2ኛ-በግል ኢንቨስተሮሽ ስም ስርና
3ኛ-በመንግስታዊ መዋቅር ስር በማድረግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ 95%በላይ የተቆጣጠረ ሲሆን በግል ኢንቨስትመንትነት ስር ከተሰለፉትና ትልቁን ሚና እንዲጫወቱ ከተደረጉት ውስጥ ቁጥር አንድ የሆኑት ቱጃሩ አል-አሙዲን እንደሆኑ እናያለን።

ታላቁ የአል-ታድ ውጥን[አል-ታድ ማለት -አል-አሙዲን -ታደለ ይድነቃቸው ማለት ነው] በሚል ለሸራተን ግንባታ፣ለአል-ታድ ኮንስትራክሽን $250ሚሊዮን ዶላር እና የለገ ደንቢን ወርቅ ማእድን በ$48ሚሊዮን ዶላር ግዢ ቱጃሩ ወደ $300ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሲያደርጉ [ከ1984 እስከ 1985ዓ.ም ድረስ ማለት ነው]በአጠቃላይ ያላቸው ሀብት መጠን ገና ከ$1.5ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳልበለጠ ገሀድ የሆነው መረጃ ግልጽ ያደርጋል።

እዚህጋ በቅደም ተከተል ልናስተውል የሚገባን ወሳኝ ነጥቦችን ልጥቀስ-

1ኛ-አል-አሙዲን በ1958ዓ.ም የ12ኛ መልቀቂያ ፈተናን ተፈትነው በ1959/60ላይ ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ ሪያድ ባዶ እጃቸውን እንዳቀኑ እናስተውል።

2ኛ-ከሃያ አምስት ዓመታት ልፋት በሃላ በ1985ዓ.ም የመጀመሪያውን አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሰሩ [1.4ቢ] ልብ ልንል ይገባል። የአንድ ቢሊዮን ዶላር ምንጭም -የባክ ስራ፣የነዳጅ ዘይት ቁፋሮ ኮንስትራክሽን፣በሳኡዲ፣በስዊዲን እና በሞሮኮ የነዳጅ ጉድጋድ ባለቤት መሆን እንደሆነም ልብ እንበል።

3ኛ-በ1984 እና 1985ዓ.ም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ሲጀምሩ የሀብታቸው መጠን ወደ 1.5ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ልብ እንበል።

4ኛ-ከሸራተን እና ለገ ደንቢ መጀመር ዓምስት ዓመት በሃላ በ1990ላይ ሸራተን በከፊል አልቆ ሲመረቅ የሰውዪው ሀብት ወደ 4ቢሊዮን ዶላር አድጋል ሲባል እንደነበረና በ1997 ደግሞ ወደ ከ6-7ቢሊዮን ማሻቀቡን መስማታችንን ልብ እንበል።

5ኛ-ዛሬ ሰውዪው[አል-አሙዲን] በ15.3ቢሊዮን ዶላር [አንዳንድ ግዜ የሀብታቸውን መጠን በ12-እና 13ቢሊዮን ዶላር መካከል የሚገልጹም አሉ] በአፍሪካ ከናይጄሪያዊው ዳንጎቴ ቀጥሎ 2ኛ በሳኡዲ ዓረቢያ ከቢንታለል ቀጥሎ2ኛ እና በአጠቃላይ ከዓረቡ ዓለም በ3ኛነት ደረጃ ላይ እንዳሉ እየሰማን ነው።

ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ባዶ እጃቸውን ከወጡ የመጀመሪያው 25ዓመታት የሳኡዲ ቆይታቸው ውስጥ $1.5ቢሊዮን ዶላር ሲሰሩ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ 25ተመሳሳይ ዓመታት ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ 70በላይ በጅቡቲና ዩጋንዳን ጨምሮ ወደ 80ድርጅቶችን የከፈቱና ባለ $15.3ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ሆነው ሳለ ዛሬም ጭምር “እኔ ለኢትዮጵያ ስራ ለመፍጠር ብዪ እንጂ ትርፍ አገኛለሁ ብዪ ድርጅት ከፍቼ አላውቅም”ሲሉን እንሰማለን።

ወዳጃቸው ህወሃትም በተመሳሳይ መልኩ ከ90በላይ ግዙፍ ድርጅቶችን በመቶ ቢሊዮንስ ብር ካፒታል ኤፈርት የተባለውን ድርጅት በአቶ መለስና በወ/ሮ አዜብ አገላለጽ አክሳሪ ድርጅት፣ከስሮ ለመፍረስ እየተፍገመገመ ያለ ድርጅት ተብሎ እየተነገረን እንዳለ ሁሉ ቱጃሩም በኢትዮጵያ ውስጥ አትራፊ ኢንቨሰተር ሳይሆኑ በጎ አድራጊ ስራ ፈጣሪ መሆናቸውን እስኪያቅለሸልሸን ግተውናል።

ከሁሉ በላይ እጅግ የሚያሳምመውና እኔን የሚያበሳጫኝ የህገራችን ሀብት ያለአግባብ መዘረፉ ብቻ ሳይሆን ከተራ ቢሊዮነርነት ወደ ዓለም ዓቀፍ ቢሊዮነርነት የተሸጋገሩት ኤፈርትና አል-አሙዲን ለዚህ ክብር ያበቃቸውን የሀገራችንን የሀብት ጸጋ ገፍፈው እኛ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስራ ፈጣሪ በመሆን የተሰማራን እንጂ ትርፍ ኖሮት አትራፊ ሆነን የምንቀሳቀስ አይደለንም የሚሉት ስላቅ ነው ከዘረፉት ይበልጥ እሚያንገበግበኝ።

ምናል ምስጋነቢስነትን ትተው አዎን አትርፈናል ቢሉና የሀገራችንን ውለታ እንካን በምስክርነት ቢገልጹ እያልኩ በክህደታቸው እበግናለሁ።

በሚዲሮክ ኢትዮጵያ ስር ካሉት ከ70በላይ ድርጅቶች ውስጥ ቢያንስ በ50ዎቹ ውስጥ ከእኩሌታ ያላነሰ የባለቤትነት ድርሻ በህወሃትና በድርጅቱ ኤፈርት ስር የተያዘ ሲሆን እጅግ ውስን በሆኑት ድርጅቶች እንደ የለገደንቢው ወርቅ ማእድን ውስጥ እኩሌታው ድርሻ በማቹ መለስና አል-አሙዲን ስር መሆኑን መረጃዎች ቢጠቁሙም ቱጃሩ ግን የሁሉም ድርጅቶች ብቸኛ ባለቤት እንደሆኑ ተደርጎ ለዓለምና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲለፈፍ ክርማል።

***ህወሃት ቱጃሩን ሊታደግ ይቻለዋልን?

የቱጃሩን መታሰር በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ተደርጎ በህወሃት መራሹ መንግስት አቃም ከመወሰዱም በላይ ከሳኡዲው አልጋ ወራሽ እርምጃ ጀርባ የግብጽ እጅ አለበት በማለት ቱጃሩን የመታደግ እርምጃ በመንግስት ደረጃ መጀመሩንም ሰምተናል።

ከቱጃሩ መታሰር ጀርባ የግብጽ ስም የተጠቀሰው ግብጽዊያን ጋዜጦች የሰውዪን መታሰር የዘገቡበትን ሁኔታ ላይ በመንተራስ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ በመቐሌው ስብሰባ ላይ ከተወያየበት በሃላ ቢባልም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን ቱጃሩ በህዳሴው ግድብ ላይ በይፋ ከሚያደረጉት ግዙፍ መዋጮ ሌላ ከህወሃቱ ኤፈርት ጋር የግድቡ ባለቤትነት ድርሻቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ የህዋቶች ክስ ግብጽ ላይ ሊያነጣጥር እንደቻለ መገመት አያዳግትም።

ሆኖም ቱጃሩን የመታደጉ ዘመቻ የተሳካ የሚሆነው የሳኡዲ መንግስት በቱጃሩ ላይ በከፈተው የክስ ዓይነት ላይ የተሞረኮዘ ሆኖ እደሚገኝ እናየለን።

ሰውዪው የታሰሩት ኢትዮጵያን በተመለከተ በግብጽ ፍላጎት ከሆነና ወይም የሳኡዲ መንግስት በሰውዪው በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ባደረጋቸውና በባከኑበት ፍሬ አልባ የኢንቨስትመንት ብክነቶች ምክንያት ከሆነ አዎን የመታደጉ ዘመቻ ውጤታማ ህኖ ይደመደማል ስል በአንጻሩም ሰውዪው የታሰሩት ከኢትዮጵያ ውጪ እዚያው በሳኡዲ ዓረቢያ ውስጥ ባደረጉት ጥፋት ላይ የተሞርኮዘ ከሆነ የህወሃት መራሹ መንግስት ሰውዬውን የመታደግ ዘመቻ ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ማለት ዘበት ይሆናል።

እንደ ተባራሪ መረጃዎች መሰረት ሰውዪው በሳኡዲ መንግስት በኩል በጋምቤላ የሩዝ እርሻ ልማት ለማስፋፋት በሁለት ዙር ክፍያ እስክ 7ቢሊዮን ዶላር እንደተቀበሉና መተግበር እንዳልቻሉም ይነገራል።

ችግሩ ይህ የጋምቤላው ኢንቨስትመት ጉዳይ ከሆነ እሳቸውን የማስፈታቱ ዘመቻ ለህወሃት ቀላል ይሆናል።
ህወሃት መራሹ ስርዓት በቀላሉ ለሳኡዲ መንግስት ቃል የተገባውን መሬት በማስረከብ ወዳጁን መታደግ ይቻለዋል ማለት ነው።

ቱጃሩ በገዘፈው ስማቸውና ተክለቁመናቸው ስር የራሳቸው አድርገው የፈለፈላቸውን እና የህወሃት ንብረት የሆኑ ድርጅቶችን ሽፋን በመስጠት ለህወሃት ከማገልገላቸውም በላይ ዛሬም ጭምር ከሀገራችን የህወሃትን እና ባለስልጣናቱን ገንዘብ ከሀገር በማዘዋወር ተግባራቸው ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ እንዳሉ ይታማሉ።

የቱጃሩ የገዘፈ ተክለቁማን የሀገሪታን ሀብት በግል ሞኖፖል ተቆጣጥሮ ህዝባን የእድሜልክ ተገዢው ለማድረግ ሌት ተቀን እየጣረ ላለው ህወሃት ታማኝና አሳማኝ ጭምብል በመሆናቸው እጅግ ግዙፍ የሀገር ሀብት በእሳቸው ስም እንዲሰበሰብና ብሎም በእሳቸው ኔትወርክ ከሀገር ውጪ እንዳሻው ማዘዋወሪያ ተግባርን የሚያካሂድባቸው ስለሆኑ ስለእሳቸው ደህንነት እጅግ ሲጨነቅ እሳቸውም ስለህወሃት ህልውና እጅግ ተጨንቀው የቻሉትን ሲያደርጉ እያየን ነው።

በ1997ቱ ምርጫ ንቢቱን ምርጡ በሚለው የቱጃሩ ቅስቀሳ አንጀቱ የበገነው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም አዲስ አበባ የቱጃሩን ምርት ፔፕሲኮላን አንጠጣም በሚል አድማ አድርጎ የኮካኮላ ምርት አቅርብቶ እንዲመነደግ ባደረገበት ወቅት ቱጃሩ “ቢወደኝ እማይጠቅመኝ ቢጠላኝ እማይጎዳኝ ድሃ ሕዝብ ቢጠላኝ ምን ያመጣል ” ብለው እንደተሳለቁ አይዘነጋም።

ሀገራችን ድሃ ትባላለች ግን የብልጽግናዋ ብዛት እነሆኝ ባለ1.5ቢሊዮን ዶላር ባለቤት የነበሩት ቱጃሩ አል-አሙዲን ዛሬ ባለ አስር ቢሊዮን [13-15ቢሊዮን ]ባለቤት አድርጋላች።

በሀገራችን የተንሰራፋውና ኢኮኖሚዋን ተቆጣጥሮ ያለው የቱጃሩ ኢንቨስትመንት ካፒታል ምንጭ በሶስት አቅጣጫ የመጣ መሆኑ ይታመናል።
1ኛው-በራሱ በቱጃሩ ግለ መነሻ ካፒታል ፈሰስ በኩል
2ኛ-በህወሃት መራሹ ንግድ ድርጅቶች በኩልና
3ኛ-በሳኡዲና ዓረብ ሀገራት ያሉ ባለሀብቶችንና መንግስታትን ካፒታል ያካተተ እንደሆነ እንረዳለን።

ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ቱጃሩና ህወሃቶች በጥመረት ከዓረብ ሀገራት በፈሰሱት ባለካፒታሎች ላይ ስልታዊ የሆነ የክህደት እርምጃ በመውሰድ በእጃቻው የገባውን ህብት በጋራ እንደተቆጣጠሩትና እንደተቀራመቱት ሲሆን ድርጊቱም ለቱጃሩ የመታሰሪያ ምክንያት በመሆን ዳፋ እንደሆናቸው ጠንከር ያለ ግምት አለኝ።

ሀገራችን ድሃ ትባላላች ግን ምንም ያለንበረውን ህወሃት በመቶ የሚቆጠር ድርጅት ባለቤት የሆነን ኤፈርትን ባለቢሊዮነር አድርጋለች- ይህን ሁሉ እየተበዘበዘችም ዛሬም የሀገራችን ሀብት ያልተነካና ዜጎቻን ማበልጸግ የሚቻለው እንደሆነ አምናለሁ።

በቱጃሩ ላይ የደረሰው ባለረዥሙ እጅ የኢትዮጵያ አምላክ ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል- የእናንተን አላውቅም-ለእኔ የታየኝና የተሰማኝ እውነታ ይህ ነው።

Filed in: Amharic