.. ቤተ እምነቶች በአጭበርባሪ አመራሮች ቤተመንግሥት በነፍሰ ገዳዮች በሌቦችና በቀጣፊዎች የትምህርት ተቋማትም በካድሬዎችና በዲግሪ ሸማቾች ሲወረር ይህ በህሊና የመገዛት ቅዱስ ስልጣኔ እስከ መቼ ይዘልቃል ? .. ህሊናቸውን እንደ ሌጦ የገሸለጡ ቀጣፊ ከሐዲና አረመኔ ግዢዎችን እያዬ ያደገ አእምሮ ከየት የመሪነት ዕውቀት ሊገበይ ይችላል ? ..
ነፍስ በማጥፋት በመዝረፍ በመስረቅ በመቀማትና በጉቦ የናጠጡ ጉምቱ ከበርቴዎችን የተመለከተ አእምሮ ሰርቶ ማግኘትን ከየት ሊማር ይችላል ? .. እውነት የተናገረ በችጋር ሲሰቃይ ንብረቱን ሲቀማ ሲሰደድ ከሥራ ሲባረር ሲታሰር ሲገረፍና ሲገደል ያዬ አእምሮ እንዴት ወደ እውነት ሊጠጋ ይችላል ? .. አንድነትን አገርን ባንዲራንና ክብርን የወደደ በጥይት ሲበረቀስ የተመለከተ አእምሮ እንዴት ለአንደነት ለአገርና ለክብር ሊቆም ይችላል ? ..
የዘር የቋንቋና የሃይማኖት ክልል የሚገነቡ ፖለቲከኞችን ስብከት ሲሰማ የኖረ አእምሮ እንዴት ከሰው ይልቅ ሰውነት ላይ ከቋንቋ ይልቅ መግባባት ላይ ከሃይማኖት ይልቅ እምነት ላይ ሊያተኩር ይችላል ? .. ተበዳይ በዳዩን ይቅርታ እሚያስጠይቅ “ሽማግሌ” እየተመለከተ የወጣት አእምሮ በምን ቋንቋ የሽምግልናን ትርጉም ሊረዳ ይችላል ? ..
ጉበኝነት አቃጣሪነት ሎሌነት ስርቆትና አድርባይነት የኑሮ ፈሊጦች በሆኑበት ማህበረሰብ ውስጥ ያደገ አእምሮ በምን ተአምር በሥነ ምግባር ሊታነጽ ይችል ይሆን ? .. ጥላቻን በሚሰብክ ገለባ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ያለፈ አእምሮ እንዴት ፍቅር እሚያፈራ ዛፍ ሊሆን ይችላል ? .. በእውቀትና በሥነ ምግባር የተሳሉ ምሁራን ተነቅላው በድንቁርና በምግባረ ብሉሹነት የዶለደሙ ካድሬዎች ከተተከሉበት የትምህርት ተቋም የዋለ አእምሮ በምን ሞረድ ሰልቶ ሊወጣ ይችላል ? .. የአየነው እጅጉን ሳይሆን የቆስጠንጢኖስ በርሄን ክፍለ ትምህርት እንዲከታተል የተፈረደበት ተማሪ በምን ሙያ ሊመረቅ ይችላል ? .. ቤተ መጽሐፍት ከሚሰሩበት ሳይሆን መጸሐፍት ለስኳር መጠቅለያ በሚሸጡበት የፍልስፍና ብራናዎች እየተሰረቁ በሚቸበቸቡበት አገር አእምሮ እንዴት ሊበለጽግ ይችላል ? .. ዓለምን በጥበብ ያሸበረቀው ኢንተኔት ተነፍጎት በጨለማ የሚደናበር አእምሮ እንዴት ብርሃን ሊያፈልቅ ይችላል ? .. ዜናዎችንና ጦማሮችን የሚያቀርቡ ጋዜጦች መጽሔቶች ሬዲዎኖችና ቴሌቪዥኖች ከሚታፈኑበት አገር አእምሮ በምን መልክ በሐሳብ ሊሰላ ይችላል ? .. በሆዳቸው በሚያስቡ ካድሬዎች የውሸትና የቅጥፈት ምላስ የረጠበ አእምሮ በምን ሐሳብ በስሎ ጣዕም ያለው ሊሆን ይችላል ?