>

ኢትዮጵያዊነት Vs ለማ መገርሣ (ዳንኤል ሺበሺ)

የኦሮሚያው ኦቦ ለማ መገርሣ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” አሉ? በርግጥ ልክ ነው፤ ግን ሱስምኮ ሰው ሰራሽ መፈወሻ ዘዴ አለው፡፡ ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል ሱስ ከሚያስይዙ ነገሮች የራቀ ሱሰኛን፤ ያ ሱስ ይለቀዋል ይባላል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሣይንሳዊ ዘዴ ማከምም የሚቻል መሰለኝ፡፡ ኢት/ያዊነት ለሩብ ምዕተ-ዓመት ከተቀበረበት በአንዴ ብድግ ስል ማየት የኢት/ዊነት ሥነ-ልቦናዊ ቁርኝት፣ ጉልበት፣ ስሜትና መንፈስ፤ እስከ ምን እንደሆን ብዙም ላልገባን ብዙ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በተለይ ብዙ ደጋፍና አባል ባይኖራቸውም የኦነግና የህወሓት አስተሳሰብ ተሸካሚ ከሆኑት ጎራ እንዲህ ያለው ቃል በይፋ መነገሩ የመልዕክቱን ደረጃ ከፍ ማድረጉ በእርግጥም የሚጠበቅ ነው፡፡ አንድን ነገር ማሰብ፤ ያሰቡትን በድፍረት መናገር፤ እና የተናገሩትን ሆነው መገኘት የየራሱ መለኪያ እንዳለውም ፈፅሞ አልዘነጋሁም ፡፡

አሃ! የተሳሳትኩ መሰለኝ፤ ሰውየው የተናገረው’ኮ እንደዛ አይደለም፡፡ አንዱ ጓደኛዬ ሲያርመኝ ኦቦ #ለማ መገርሣ ሲናገር “ኢትዮጵያዊነት ከሱስም በላይ ነው” ያለው እንጂ <ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው> ብሎ ብቻ አላለፈም በማለት፡፡ አዎን! አሁን በጣም ተስማማኝ፡፡ አንባቢዎቼ አትቀይሙኝ የግራ ጆሮዬን ለኀወሓት ደንነቶች ሰውቸው ስለነበረ አንደኛው ጆሮዬ በከፊል መስማት ተስኖታልና ዜናውን ሸራርፌ አድምጬው ይሆናል። ሊቃውንት “ከሰው ስህተት፤ ከብረት ዝገት” እንደሚሉት መሆኑ ነው፤ ኦቦ ለማ አፉ በለኝ፡፡

የኢትዮጵያዊነት ብዥታን ማከም የሚቻለው ግን ከነፍሱ፣ ከሥጋው፣ ከሕይወቱ እና ከመላ ሀሳቡ የኢትዮጵያዊነት ሐቅ በመቀበል ነው፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ለሀገር የከፈሉትን ዋጋ በማስታወስ ነው፡፡ ይሄንን በጥልቅ ስንረዳ፣ ኢትዮጵያዊነት ከዜግነት በላይ መሆኑን፤ ኢት/ዊነት የውርስ ጉዳይም አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያዊነት በግድ የሚፃፍብን ሳይሆን በፍቅር በእምነትና-በዕውቀት የተቀበልነው ማኀተም መሆኑን፤ ኢት/ዊነትን ያገኝነው እንደ ዲቪ ሎተሪ በማመልከቻና በውልደት ብቻ አለመሆኑን፤ በቀደምት ወላጆቻችንና በአሁኑ ትውልድ ደምና አጥንት የተገነባ መሆኑን በመረዳት ሲሆን፤ የሀገር ግንባታ ብቻም ሳይሆን እኛም እርስ በርሳችን በደም የተገናኘን መሆኑን፤ እንደ እናት ልጅ በደም፣ በአጥንት፤ በሽልና (Fetus) በእንብርት የተቆራኘን መሆናችንን ስንረዳ ኢትዮጵያዊነት ማለት መኖር ማለት ነው ብለን እንቋጨዋለን፡፡ በቃ! #መኖር ማለት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ነገራችን ነው፤ የአምላክ ፀጋ ብለን እንደመድመዋለን ፡፡

ወዳጆቼ ፦
ከኢት/ዊነት መራቅ የሚቻለው በክህደት ብቻ ነው ፡፡ የሚኒልክ፣ የቴዎድሮስ፣ የዮሐንስ ወይም የየትኛውም ነገሥታት ጉዳይ አይደለም፡፡ የኦሮሞው፣ ወላይታውና የአፋሩ ወ.ዘ.ተ ወላጆቻችን ለኢት/ዊነታቸው ተዋድቀዋል፡፡ ኢት/ዊነት ግን ረቂቅ ነው ያስባለው ምስጢር ይህ ነው፤ በደም ዋጋ የተገኘ ማንነት በመኖሩ ነው፡፡ እንደ ሌላው ዓለም ሀገራት በማመልከቻ የሚገኝ የዜግነት አይነት አይደለም፡፡

ኢት/ያም እንደ ሀገር ለዘመናት በእምነት የተቀበሏት በከፈሉት መስዋዕትነት፤ በደምና በአጥንት የተዋቀረች የቃለ-ኪዳን ምድር ናት፡፡ ሐቁን መቀበል እንጂ፤ ምክንያት መደርደረ የትም አያደርስም፡፡ የበደለን የጎዳን ኢት/ጵያዊ መሆናችን አይደለም፡፡ የአገዛዝ ሥርዓታችን ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የእያንዳንዳችን ድርሻ አለበት፤ እንደ ሰው በወላጆቻችንም በእኛም የተሰራ ስኀተት መኖሩን አምነን በመቀበል ወደ መፍትሄው መሄድ እንጂ ኢት/ዊነትን መራገም መሻልን አያሳይም ፡፡

ኦቦ ለማ በዚሁ መንፈስ ይቀጥሉበት፤ ወደ ኀላ የለም! ቃል ከተግባር ጋር እንጠብቃለን፡፡ የጋሽ ለማ አይነት አስተሳሰብ ያላችሁ በመጀመሪያ ሰው ነበራችሁ፤ ቀጥሎም ኢትዮጵያዊ ናችሁ፤ በመጨረሻም ወደ አይቀረው ዘለዓለማዊ ቤታችን እንሄዳለንና ደስ ይበላችሁ፡፡ ከፍታው የኛ ነው፤ ወደ ኋላ የለም! ወደ ኋላ፡፡ የትግላችን ፍሬ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ትግላችን ምን ያህል የነጠረ እንደሆነ አንዱ ማረጋገጫችን ይህ አስተሳሰብ በዚያኛው ጎራ ሳይቀር ማንሰራራቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር በውስጣችን ደምቆ ይኖራል፡፡ ሰላም !

Filed in: Amharic