>

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያ በኢትዮጵያ የኃሳብ ሰማይ ላይ ጎልተው የሚታዩ አብሪ ኮከብ ናቸው (አቻምየለህ ታምሩ)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያ በኃሳብ ላይ የጸና ሙግት አመንጭነታቸው ምሁራዊ አስተዋጽኦ ካደረጉበት ካለፉት ስድስት አርስት አመታት በላይ አልፎ ወደፊትም የሚኖር የዘላለም ስም አስገኝቶላቸዋል። «ፕሮፍ»  በኢትዮጵያ የኃሳብ ሰማይ ላይ ጎልተው የሚታዩ አብሪ ኮከብ ናቸው። ባጭሩ መስፍን ወልደ ማርያም የሚለው ስም በድንቁርና ሳይሆን በእውቀት በሚደረግ የኢትዮጵያ ጉዳይ ሙግትና ክርክር ሁሉ ሲነሳ የሚኖር የዘላለም ስም ሆኗል።

በእኔ እምነት የዘመኑ ወጣቶች «ፕሮፍ» እያልን የምንጠራቸው ፕሮፌሰር መስፍን እኔን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶች ባገራችን ጉዳይ ላይ ያገባኛል እንድልን ብቻ ሳይሆን አለምን የምንረዳበት የተለየ መነጸር ጭምርም እንዲኖረን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የቀለም ቀንድ ናቸው።

ስለፕሮፌሰር መስፍን አስተዋጽኦ በማውሳት ጽሁፌን መጀመሬ ማስተዋወቅ ስለማያስፈልጋቸው ጉምቱ ምሁር ለማስተዋወቅ ፈልጌ ሳይሆን ወረድ ብዬ በምጽፈው አስተያየት ውስጥ እሳቸው ከትናንት በስቲያ ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ያነሷቸው አንዳንድ አስተያየቶች ዙሪያ በታሪክ ተመዝግቦ ከሚገኝውና ካነበብሁት እውነታ ጋር አብረው የማይሄዱ ጉዳዮችን ስለታዘብሁ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል ስለ አንዱ ለማቅረብ መነሳቴ አስተዋጿቸውን በመዘንጋት አለመሆኑንና አክብሮቴ በኃሳብ ባለመስማማት ውስጥም ሙሉ እንደሆነ ለማስታወቅ ነው።

አተያየት እንድሰጥ ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ከሆኑኝ መካከል አንዱ ፕሮፍ ራሳቸው ከትናንትና በስቲያ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት «ሰዎች የሰሩት ጥሩ ነገር መነገር አለበት» በሚል ያነሱት ተገቢና ትክክለኛ አስተያየታቸው ነው። ፕሮፍ ባነሱት ኃሳብ ላይ ተገቢ አስተያየት መስጠት በራሱ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ስለሆነ ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በኃሳብ ከመሟገት ባሻገር ጥሩ ሰርተው በበጎ ሳይነሱ ያለፉ ሰዎችን አስተዋጽኦ ትክክለኛ ቦታ በማስያዝ ረገድ አጋጣሚው የማይናቅ ሚናም ይኖረዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ከትናንትና በስቲያ የኢሳቱ ቃለ ምልልሳቸው በጠቅላይ ሚንስትር እንዳልካቸው መኮነን ንግግር ተከፍቶ ስራውን የጀመረው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ያዘጃገው አዲስ ረቂቅ ሕገ መንግሥት «ለሕዝብ የበለጠ ስልጣን ስለሚሰጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላልወደዱት ወደቀ» ሲሉ ተደምጠዋል። በርግጥ ፕሮፍ በንግግራቸው ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ውድቅ እንዲሆን የተደረገው [ኋላ ላይ የመጣው] መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ስላልወደደው ነውም ብለዋል። የፕሮፌሰር መስፍን አስተያየት «ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ያልጸደቀው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ስላልፈለገው ነው» የሚል ብቻ ቢሆን ኖሮ የሰጡት አስተያየታት በጉዳዩ ዙሪያ በታሪክ ተመዝግቦ ከሚገኘው እውነት ጋር የሰጡት አስተያየት አንድ አይነት ስለሆነ ባነሱት ጭብጥ ዙሪያ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ሊነሳባቸው አይችልም ነበር።

ሆኖም ግን «ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ለሕዝብ የበለጠ ስልጣን ስለሚሰጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላልወደዱት ወደቀ» በሚል ፕሮፍ ያደረጉት ንግግር በታሪክ ተዘምግቦ ከሚገኝው እውነት ጋር ስለሚቃረንና ፈረንጆቹ «ከፈረሱ አፍ» እንደሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን ከተናገሩት አስተያየት በተቃራኒ የነበረውን የወቅቱን እውነት በአካል ተገኝተው፣ በአይናቸው ተመልክተው፤ የታሪኩ አካል ሆነው ከነገሩን የአይን ምስክሮች መካከል የሆኑት የወቅቱ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከተውልን ማስታወሻ አኳያ ፕሮፌሰር መስፍን በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት ለመግዛት ያዳግታል።

እነ ሐዲስ አለማየሁ፣ ይልማ ዼሬሳ፣ አበበ ረታ፣ ዶክተር አብርሃም ደሞዝ፣ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፣ ሐጅ መሐመድ ሳኒ፣ ፊታውራሪ ሐዳድ ካራር፣ ቀኝ አዝማች አብዱል አዚዝ ሼክ መሐመድ፣ ወዘተ አይነት ኢትዮጵያ ያሏት ምሁራን ተሰባስበው አእምሯቸው ጨምቀው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመጨረሻ ዓመት ስላዘጋጁት የኢትዮጵያ አዲስ ረቂት ሕገ መንግሥት፣ የሕገ መንግሥቱ ዝግጅት ጉባዔው አባላት የነበሩት እነ አቶ ተፈራ ደግፌ፣ ዶክተር አክሊሉ ሐብቴ [በሕይወት ያሉ] እና አቶ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ጽፈው ማስታወሻ ትተው አልፈዋል።

አቶ ተፈራ ደግፌ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. ባሳተሙት «Minutes of an Ethiopian Century» በሚለው መጽሀፋቸው ከገጽ 333-338 በከተቡት እና አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ «የሕይወቴ ታሪክ» በሚል ጽፈው በ2008 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው ከገጽ 255-274 ላይ በጻፉት ትዝታቸው ስለ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ዝጅግት ጅማሮ፣ ሂደትና ፍጻሜ በስፋት አውስተው ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚና ከተናገሩት በተቃራኒው አዲሱ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ፓርላማው ለእረፍት ሳይበተን እንዲታወጅ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ አውስተዋል። አሁን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም «ለሕዝብ የበለጠ ስልጣን ስለሚሰጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላልወደዱት ወደቀ» ሲሉ የሰጡት አስተያየት የተሳሳተ መሆኑን በዶሴ ማሳየትና ቃል በቃል በተለይ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔው ሰብሳቢ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ የሰጡትን ምስክርነት ወደ ማቅረብ ልሸጋገር።

እዚህ ላይ የአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያን ምስክርነት ከማቅረቤ በፊት በየካቲት 1966 ዓ.ም. የተከሰተውን የሕዝብ ጥያቄ ተከትሎ የወቅቱ መንግሥት ማለትም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ስለወሰደው እርምጃ በመጠኑ ላውሳ። ታሪክ እንደሚነግረን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሰልፍ፤ የታክሲ አሽከርካሪዎች በነዳጅ ላይ የተጣለውን ጭማሪ በመቃወም ያደረጉትን የስራ ማቆም አድማና አዲስ አበባና ደብረ ዘይት የነበሩ ወታደሮች ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተ ወልድ ካቢኔ ስራውን ለቅቋል። ይህ እንደሆነ ወዲያው በምትኩ በልጅ እንዳልካቸው መኮነን ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራ አዲስ መንግሥት ተቋቋሞ የመንግሥትነቱን ስልጣን ተረከበ። የጠቅላይ ሚንስትር አክልሉ ሃብተ ወልድ መንግሥት ከስልጣን በለቀቀ በስድስት ቀናት ውስጥ ማለትም በ ካቲት 26 ቀን 1966 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቴሌቭዥን ቀርበው የሚከተለውን ንግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አደረጉ፤

«በንጉሠ ነገሥት መንግሥት አቋማችን ውስጥ በሚገኙ ልዩልዩ የሥራ አካሎች መካከል ያለው ሕጋዊ ግንኙነት የተብራራና የተስተካከለ እንዲሆን አሁንም ሕገ መንግሥቱ በጠቅላላቅ እንዲሻሻል ስናደርግ ለአገራችን ዘላቂ ጥቅም የሚሰጥ ሆኖ፤1ኛ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራው ለፓርላማ አላፊ የሚሆንበትን፤ 2ኛ፡ ለሕዝባችን ብሔራዊ መብት በበለጠ ሊጠበቅ የሚችልበትን፤ 3ኛ፡ የፍርድ ሥነ ሥርዓት በሚገባ ተደራጅቶ በተፋጠነ መንገድ ፍትሕ ሊያገኝበት የሚችልበትን፤ 4ኛ፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ሀብትና ቅርስ በሚገባ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ ተሠይሞ አጥንቶ እንዲያቀርብ ይደረጋል።»

ይህንን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሕዝብ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያ ያሏት ምሁራን ከያሉበት ተሰባስበው፤ እነ ዶክተር ፋሲል ናሆም፣ አቶ ዘገዬ አስፋውና በድምሩ 15 የሚሆኑ ከፍተኛ የሕግ ባለሞያዎች ጭምር የተካተቱበት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን በሕግ ተቋቁሞ ከፍተኛ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔው መጋቢት 20 ቀን 1966 ዓ.ም. በመሰየም ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ተግባሩን ጀመረ።

ይህ የሕገ መንግሥት ጉባዔ በስድስት ወር ውስጥ ረቂት ሕገ መንግሥት አዘጋጅቶ ለፓርላማ እንዲያቀርብ ቢታዘዝም በከፍተኛ የጉባዔው አባላት ጥረት ሌት ተቀን ሰርተው ስራው በአራት ወር ውስጥ ተጠናቅቆ ሐምሌ 30 ቀን 1966 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ ሚካኤል እምሩና ለደርግ አባላት ተረከበ። ይህ ረቂት ሕገ መንግሥት የንግግር ነጻነትን [Freedom of Speech] የሚያጎናጽፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረትን የሚፈቅድ፤ የሞያ ማህበራትን መደራጀት ሕጋዊ የሚያደርግና ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ካንድ በላይ ብሔራዊ ቋንቋ ኢትዮጵያ እንዲኖር የሚፈቅድ ሕገ መንግሥት ነበር።

የሕገ መንግሥቱ ጉባዔ አባላት ደርጎች የጋረጡባቸውን ችግር ሁሉ አልፈው ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን ለመንግሥት ካስረከቡ በኋላ በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሕዝብ እንዲወያይ በሚል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጪውን ሸፍኖ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 50 ሺህ ኮፒ የረቂቅ ሕገ መንግሥቱን ቡክሌት አትሞ ሕዝቡ በአንድ ብር የረቂቅ ሕገ መንግሥት ቡክሌቱን እየገዛ አንብቦ አስተያየት እንዲሰጥና ከሽያጩ የሚገኘውም ገቢ በወቅቱ በርሃብ ለተጠቃው ሕዝብ እህል መግዣ እንዲውል ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ወሰኑ። ታዲያ ምን ያደርጋል! ለስልጣን የተሰለፉት ደርጎች ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን አግደው፤ ብርሃንና ሰላም ያተመውን 50ሺህ ኮፒም በማቃጠል ለተራበው ሕዝብ ባስቸኳይ ይደርስ ዘንድ በወቅቱ ገበያ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴና ማሽላ መግሻ የተመደበውን 50ሺህ ብር የሚያወጣ ሰነድ በእሳት ዶግ አመድ አድርገው አወደሙት። ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚነግሩን ይህንን ያደረጉት ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ሻምበል ሲሳይ ሐብቴና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ ናቸው።

ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ በፈጀው የአራት ወር የዝግጅት ጊዜ ውስጥ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባኤው ሊቀ መንበር አቶ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ እዮቤልዩ ቤተ መንግሥት እየተጠሩ ሶስት ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ማነጋገራቸውን ጽፈዋል። በነዚህ ግንኙነቶች ሁሉ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ያነሱት የነበረው ፕሮፌሰር መስፍን «ለሕዝብ የበለጠ ስልጣን ስለሚሰጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላልወደዱት ወደቀ» እንዳሉን ሳይሆን በተቃራኒው ፓርላማው ለእረፍት ሳይበተን ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ለፓርላማ ቀርቦ በቶሎ እንዲታወጅ ጥናትና ዝግጅቱን በቶሎ እንዲጨርሱ ነበር።

የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔው «አብዮተኛ ነን» የሚሉ ሁሉ ከያቅጣጫው የሚሰነዘሩባቸውን ሁሉ ጫና ተቋቁመው ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን በሐምሌ ሰላሳ 1966 ዓ.ም. ለልጅ ሚካኤል መንግሥትና ለደርጎች አስረክበው እንዲታወጅ ቢጠይቁም ሻለቆችና የበታች መኮንኖች የሆኑት ደርጎች ግን የኦክስፎርድና የየል ምሩቃንን «በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ በመታወጁ ላይ አትቸኩሉ» በሚል እያሸማቀቋቸው ቆይተው መጨረሻ ላይ የሕገ መንግሥት ዝግጅት ጉባዔው አባላት የሆኑትን ጉምቱዎችን እነ ልጅ ይልማ ዼሬሳን፣ አምባሳደር ግርማቸው ተክለ ሐዋርያትንና አቶ አበበ ረታን ከመካከላቸው አስረው 30 ታላላቅና ከልዩ ልዩ የማህበረሰባችን ክፍሎች የተውጣጡ አዋቂ ኢትዮጵያውያንና 15 ከፍተኛ የሕግ ባለሞያዎች ለአራት ወር ቀን ተሌት የደከሙበትን ሕገ መንግሥት መና አድርገው አስቀሩት። የተበተነው ፓርላማ ረፍቱን ጨርሶ በመስከረም ወር ሲለመስ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን አጽድቆ እንዳያውጅ በመስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም. መንግሥት ገልብጠው ፓርላማውን መበተናቸውንና ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን ማገዳቸውን አወጁ። በምትኩ አዋጅ ቁጥር አንድ እዝባር 1967 ብለው ባወጡት የማርሻል ሕግ ለአስራ ሶስት አመትት ያህል [ ኢሕድሪ የሚባለውን ጭንብል እስኪያጠልቁ ድረስ] የነበረውን ሕጋዊ ስርዓት በወታደራዊ አዋጅ አግደው ጥሩንባ እየነፉ ሲገድሉን ባጁ።

«አድሃሪ» የተባሉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕጋዊ ስርዓት እንዳይፋለስና ከሐምሌ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ሕዝብ ከጠየቀው ጥያቄ አኳያ ፍትህ አጥቶ እንዳይበደልና እንዳይጉላላ ፓርላማው ለእረፍ ሳይሄድ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ እንዲታወጅ ሲያዘዙ «ተራማጅ» የተባለው «አብዮተኛው» መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግን ተቀናቃኞቹን ሁሉ ያለ ፍርድ ረሽኖ ጨርሶ ብቻውን ያለ ተቀናቃኝ ገኖ እስኪወጣና ኢሕድሪ የሚባለውን የማታለያ ጭንብል አውጆ የይስሙላ ሕገ መንግሥት እስኪያቆም ድረስ ለአስራ ሶስት ዓመታት ያልህ ያለ ሕገ መንግሥት በቀይ ሽብር አዋጅ ስርዓት አልበኝነትን አስፍኖ እንዳሻው ሲገድልና ሲረሽን ኖረ።

ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስና የረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ጉባኤ ሊቀ መንበር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢሳት የተናገሩትን ሙሉ በሙሉ ውድቅ በሚያደርግ አኳኋን «የሕይወቴ ታሪክ» በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 274 ላይ፤

«. . . ንጉሠ ነገሥቱ ልዑል ራስ እምሩን፣ ደጃዝማች ከበደን፣ እኔን [ተክለ ጻዲቅን ማለታቸው ነው] እና በላቸውአራትን [በላቸው አስራት የወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩ ናቸው] አስጠርተው <በቶሎ የሚታረም እንዳለ አርማችሁ (ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ማለታቸው ነው) ለፓርላማ ቀርቦ ይታወጅ> ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ወዲያው እየተከታተለ የፓርላማው ሰብሳቢና አንዳንድ አባሎች መታሰር ጀመሩ፤ ቀጥሎም ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን መውረድና የደርጉ ሥልጣን በጨበት ሁሉንም ተስፋ ዘጋው።» ይላሉ።

እንግዲህ! ከዚህ የተክለ ጻድቅ ምስክርነት የምንረዳው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥቱ እንዲታውጅና በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ እንጂ ፕሮፌሰር መስፍን «ለሕዝብ የበለጠ ስልጣን ስለሚሰጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላልወደዱት ወደቀ» ብለው እንዳቀረቡት አይነት አስተያየት ተመዝግበው በሚገኙ ቀዳሚ የታሪክ ምንጮች ውስጥ አይገኙም።

ልብ በሉ! ተከለ ጻድቅ መኩሪያ የሕገ መንግሥት አዘጋጅ ጉባዔው ሊቀ መንበር ናቸው። ይህ ማለት የሕገ መንግሥት ጉባዔ ሊቀመንበሩ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን በሚመለከት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስለነበራቸው አስተያየት የሰጡት ምስክርነት authority ነው ማለት ነው። ለምን ቢባል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠርተው ረቂቅ ሕገ መንግስቱ «በቶሎ የሚታረም እንዳለ አርማችሁ ለፓርላማ ቀርቦ ይታወጅ» አሉን ሲሉ ተክለ ጻድቅ የጻፉት የስሚ ስሙ የሰሙትን ወይንም ከውጭ የተባለውን ሳያጣሩ በመድገም ሳይሆን የነገሩን በዋናነት ቀዳዊ የአካልና የታሪክ ምስክር ሆነው ለሳቸው ለራሳቸው ለሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ሊቀመንበሩና ለፍትህ ሚንስትሩ በቤተ መንግሥት አስጠርተው ያሏቸውና ነውና።

ስለዚህ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ሊቀመንበሩና ቀዳሚ የታሪክ ምስክሩ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደነገሩን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥታቸው ጠርተው ረቂቅ ሕገ መንግስቱ በቶሎ የሚታረም ነገር እንዳለ ታርሞ ለፓርላማ ቀርቦ ይታወጅ አሉ እንጂ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ስላልወደዱት እንዲወድቅ አላደረጉም። ይህ ብቻ ሳይሆን እነ ተክለ ጻድቅ በቶሎ ጨርሰው እንዲታወጅ የጠየቁት ይህን የሕገ መንግሥት ረቀቅ እንዲዘጋጅ የሆነው ሕዝብ በሰልፍ ወጥቶ በጠየቀ በቀናት ውስጥ ራሳቸው ንጉሱ [ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ] የካቲት 26 ቀን 1966 ዓ.ም. ለሕዝባዊ ጥያቄው በሰጡት ምላሽና ባስተላለፊት መመሪያ መሰረት ነው። እውነታው ይሄ ነው።

Filed in: Amharic