>

የታሪክ ምፀት ይሉሃል ይሄ ነው:: መድረሻ ያጡ ጠጉረ ልውጦችን ያስጠጋ የነበረ ህዝብ ዛሬ ራሱ መድረሻ አጥቷል (በዕውቀቱ ስዩም)

በዚህ ታሪካዊ ምስል ላይ የሚታየው የመጀመርያው የከተማ ባቡር አስመጭ ሰርኪስ ተረዝያን ነው::

ኢትዮጵያ: ከእልቂት አምልጠው የሙጥኝ ላሏት የአርመን ስደተኞች ዜግነት ትሰጥ ነበር :: አንዱ የዜግነት ተቀባይ አቶ ሰርኬዝ ሲሆን በፓስፖርቱ ላይ የሚከተለው ፅሁፍ ሰፍሯል:-

“ሞአ አንበሳ ዘ እምገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሄር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ 
ሰርኪስ ተረዚያን አገሩ አርመን የተወለደበት ከተማ አረብአገር : እድሜው ሰላሳ ዘጠኝ አመት: ቁመቱ መካከለኛ : ጠጉሩ ከርዳዳ ላዛ: ፊቱ አጭር: በግራ አገጩ ለምፅ ያለበት ነው:: ለመንግሥቴ ለኢትዮጵያ ሎሌ ሆኖ ብዙ ቀን አገልግሎኛልና ከንግዲህ ወዲህ ቁጥሩ የሀበሻ ሰው ነው:: በሚሄድበት አገር ሁሉ ክፉ ነገር እንዳያገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ዜጋ መሆኑን ለማስታወቅ ይህን ባስቡርት ሰጥቸዋለሁ”

(የፓስፖርቱን ወሪጂናል ባሰተያየት መስጫ ሳጥኑ ውስጥ ይመልከቱ)

የታሪክ ምፀት ይሉሃል ይሄ ነው:: መድረሻ ያጡ ጠጉረ ልውጦችን ያስጠጋ የነበረ ህዝብ ዛሬ ራሱ መድረሻ አጥቷል::

ሰርኪስ ያስመጣው ባቡር ስሙን ወርሶ “የሰርኪስ ባቡር “ይባል ነበር:: ባቡሩ በዛሬው አይን ሲታይ ካንድ ግዙፍ ቡልዶዘር አይበልጥም :: ያም ሆኖ በጊዜው እንደ ብርቅ እንደ ትንግርት ይታይ ነበር::

የሰርኬስ ባቡር ትንሽ እንዳገለገለ ተሰናክሎ ተገትሮ ቀረ:: ባለ ባቡር የነበረው አርመናዊም ባለበቅሎ ሆኖ ቀጠለ:: የሰርኪስ ባቡር የፍጥነት ምሳሌ መሆኑ ቀርቶ የቁሞ ቀርነት ምሳሌ ሆነ:: የዚያን ዘመን ያራዳ አዝማሪ:-

ብነግርሽ ብነግርሽ አታጠናቅሪ
እንደ ሰርኪስ ባቡር ተገትረሽ ቅሪ

ብሎ መዝፈኑ ተመዝግቧል::

አሁን እዚህ ዘመን ላይ ቆሜ ሳስበው “ተገትረሽ ቅሪ “ተብላ ባዝማሪው የተረገመችው ማን ትሆን? ያዝማሪው ፍቅረኛ ? ወይስ ያዝማሪው አገር?

Filed in: Amharic