>

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከተከሰሱበት ክስ በነፃ ተሰናበቱ!! (ይድነቃቸው ከበደ)

በባለፈው አመት አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል ተብለው በተመሰረተባቸው ክስ ለ9 ወር ያህል ታስረው እንደነበር የሚታወስ ነው። በተመሰረተባቸው ክስ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና (በይግባኝ) አሲዘው ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ከአገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ተጨማሪ ትእዛዝ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።

ከእስር ከተፈቱ ከሦስት ወር በኋላ በዛሬው እለት ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም በተከሰሱበት ክስ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም ፣ፍርድ ቤቱ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ የተከሰሱበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተሻረ በመሆኑ ፣ በወንጀለኛ ሕግ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ከተከሰሱበት ክስ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን ፤ በሕጉ ላይ እንደተገለጸው ” የተሻረ ሕግ ይሰራ በነበረበት ጊዜ የተፈጸመ ወንጀል ሲኖር እና በዚህ ህግ እንደወንጀል ያልተቆጠረ ሲሆን ሊያስከስስም ሆነ ሊያስቀጣ አይችልም ክሱም ተጀምሮ እንደሆነ ይቅረጣል” በማለት በሕግ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህም መሰረት አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን ፣ ፍርድ ቤቱ ለዋስትና ያስያዙት ገንዘብ እንዲመለስ እና ከሃገር እንዳይወጡ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል ። 

 
Filed in: Amharic