>

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ … (ዘካሪያ መሃመድ)

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዘመናት የሀገራችን ሕዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መስተጋብሮች ውጤት የመሆኗን ሐቅ በቀላሉ መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጦርነትን ጨምሮ በአካባቢው ሕዝቦች መካከል ለብዙ ዘመናት ሲካሄዱ ከነበሩ ዘርፈ ብዙ መስተጋብሮች በኋላ፣ እኛ ሳንፈጠር በፊት በዛሬው መልኳ ተሠርታ ጠብቃናለች፡፡ … የጥንት አያት፣ ቅም አያቶቻችን “የሠሯቸው ስህተቶች” ካሉ፣ እኒያን እያረምን፣ የጋራ ሀገራችንን በቅን ልቡና ለማቅናት መታተር እንጂ፣ በአያቶቻችን “ስህተቶች” ላይ መቸከል ያለብን አይመስለኝም፡፡ …

ዛሬ በዚህች ሀገር ውስጥ የምንኖር ከ80 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦች “ኢትዮጵያዊ” ተብለን በአንድ መጠራታችን፣ እንዲሁ በነሲብ የተገኘ፣ በአጋጣሚ የተፈጠረ አይመስለኝም፡፡ … ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ …

[……..… በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በተደረገ አንድ ጦርነት፣ የቋራው ካሳ ኃይሉ ጋሻ ጃግሬ የሆነ አንድ ወታደር የቅም-አያቴን አንገት በጎራዴ ቀንጥሶት ይሆናል፡፡ … እና ምን ይጠበስ?! … ቅም-አያቴም እኮ ጎራዴ ይዘው ነበር፡፡ … ግን፣ የአንድ ሁለቱን ቋንጃ ሰብረው፣ ከዚህ ወታደር ጋ እንደተፋጠጡ ተቀደሙ፡፡ … ይኸው ወታደር የቅም አያቴን አንገት መቀንጠሱ ሳያንሰው፣ … ኋላ ወደ መንደር ገብተው ሲዘርፉ፣ … ወደ አያቴ ጎጆ ዘልቆ ቆንዦዋን ምሽታቸውን “ተመኝቷት” ይሆናል፡፡ … በጦርነት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድርጊት መፈፀሙ ብርቅ ነው እንዴ?! … እና፣ ቅድመ አያቴ የተረገዙት ከዚህ ወታደር ላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለኝ?! … ምንም፡፡ … …]

ወዳጄ ልቤ፣ ከዚህ በላይ የነገርኩህ የቅም አያቴ ታሪክ ምናባዊ ነው፡፡… ነገር ግን፣ ባለፉት ብዙ ሺህ ዘመናት፣ ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላት የጋራ ሀገራችን በምትገኝበት ቀጠና፣ ስንት መቶ ጦርነቶች እንደተካሄዱ አስበው! … ትንንሾቹን እንኳ ትተን፣ አጼ አምደጽዮን ከመሃል ሸዋ እስከ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተቋቁመው የነበሩ ሱልጣኔቶችን ተራ በተራ ሲደመስስ፣ … ኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋዚ (ግራኝ) ከምሥራቅ ተነስቶ ያን ሁሉ ሀገር እያስገበረ እስከ ደንቢያ (ጎንደር) ሲዘምት፣ … ከእነርሱ ጋር ተሰልፎ የተዋጋው ያ ሁሉ ወንድ፣ … በእነዚያ ሁሉ ዓመታት “ከወንድነቱ እየጦመ” ነው’ንዴ ያሳለፈው?! … ማነው ያለው?! … ያኔም ይዘፈንላት የነበረች ስንቷ ቆንጆ ባገር ሞልታ?! …

እንግዲያው፣ እንደ ባሻ አሸብር፣ “የሞጃው ተወላጅ፣ የጠራሁት መንዜ” እያልሁ የምኮፈስ፣ እኔ ማን ነኝ?! … አንተስ ማነህ?! … ደቡብ ሸዋ ላይ ተቀምጦ ‘ጉራጌ’ ነኝ የሚለው እና ደጀን ላይ ተቀምጦ ‘የጠራሁ ጎጃሜ፣ የበላይ ዘር ነኝ’ እያለ የሚፎክረው የአባይ ዳር ኮበሌ፣ … የአንድ ሽማት ልጆች ስላለመሆናቸው ማን ነው በእርግጠኛነት፣ … በአስረጅ የሚናገር?! …

… ይህች የዛሬዋ ሀገራችን እምዬ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት የአካባቢው ሕዝቦች የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ውጤት ናት ስልህ፣ ጦርነትን ተከትሎ የሚመጣውን የዘማች ወታደሩ “ተፈጥሯዊ ጥያቄ”ም እያሰብሁ ነው፡፡ … እኛ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን የእነዚያ አያሌ ዘመናት ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ ድሎች፣ ሽንፈቶች እና የጦርነት አጋጣሚ … እንትኖች … ፍሬዎች ነን ማለቴም ጭምር ነው፡፡ …

ገጣሚና ፈላስፋው ሰሎሞን ዼሬሳ፣ “በሴት አያቶቻችን ደጃፍ ማን እንዳለፈ የሚያውቁት እነርሱና አንድዬ ብቻ ናቸው” ሲል ይህን ማለቱ ይመስለኛል፡፡ … እንደኔ፣ እውነት ብሏል፡፡ …… የሰላም እረፍት ያድርግለት፡፡ …

Filed in: Amharic