>
5:13 pm - Tuesday April 20, 5706

ሚዲያና ማኅበራዊ ኃላፊነት፤ (በውብሸት ሙላት)

የብሮድካስት አገልግሎት ሕግና አተገባበር ለፌ ወለፌነት፤

 

ሰሞኑን የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ራሱ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም የሚመለከት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት በፌስቡክ ገጻቸው የሚያሰራጯቸው መልዕክቶች እና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭት ዋነኛ አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎቹ የመንግሥትንም የግልንም የሚመለከቱ ናቸው፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚጠቀም እና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚጽፏቸውን ወይንም የሚጭኗቸውን ጽሑፎች፣ ምስሎች እና ድምጾች ለሚከታተል ሰው፣ አልፎ አልፎ ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮች ማስተዋል የሚቻል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣ በርካታ በጎ ዕሴቶችን በፍጥነት ሊያወድም እንደሚችል እሙን ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣ አድልኦ እና መገለልን ብሎም እጅግ አደገኛና ዘግናኝ ወንጀሎችን ሊያስከትል እንደሚችል ታሪክ ምስክር ነው፡፡

ከሰለባዎቹ አንጻር ሲታይ የጥላቻ ንግግሩ የሚፈጸመው ፣ ብሔርን መሠረት አድረጎ፣የሃይማኖት ተከታዮችን፣ ስደተኞችን እና ሌሎች ቡድኖች ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥላቻ ንግግር ምክንያት በተለያዩ አገራት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ተከስተዋል፡፡

የጥላቻ ንግግርም ቡድናዊ ቅርጽ ለመያዝ በእጅጉ የተጋለጠ ነው፡፡ ታሪክም ያሳየን ይሄንኑ ነው፡፡ በርካታ አገራት ከራሳቸውም ገጠመኝም ይኹን ከሌሎች የታሪክ ጠባሳ በመማር የጥላቻ ንግግሮችን የሚከለክሉ ሕግጋት አውጥተዋል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማትን አደራጅተዋል፡፡

በኢትዮጵያም በተለይ ብሮድካስተሮች የሚሰራጩ ፕሮግራሞችን በተመለከተ በቅድሚያ የመከታተልም እንደ ሕጉ መንቀሳቀሳቸውን የመከታተል ሥልጣንና ተግባር የተጣለበት ለብሮድካስት ባለሥልጣን ነው፡፡ ከሰሞኑም፣በግልም በመንግሥትም በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን የተላለፉ ፕሮግራሞችን መነሻ በማድረግ የተለያዩ ሐሳቦች በመገናኛ ብዙኃን ተላልፈዋል፡፡

የብሮድካስት ባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርም መገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ የማሻሻያ ፕሮግራሞች ማድረግ የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄንኑ አረጋግጠዋል፡፡ እንግዲህ ለእዚህ መነሻ ከሚሆኑት ምክንያቶች የሚያስተላልፉት ፕሮግራሞች ይዘት ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ይሁን ሌሎች ተቋማት የጥላቻ ንግግር ምንነቱን፣ ይዘቱን፣ መንስኤውን፣ መዘዙን እና ሌሎችም ጭብጦች ላይ በመመርኮዝ ጥናት ያጠናሉ፤የፍትሕ ተቋማትን እንደሌሎች አገራት የማሰልጠን፤ ሕዝብን የማንቃት ሥራ ቢፈጽሙ፣ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ሕዝቡም በሠላም እና በመቻቻል የመኖር ዕሴቱን ይበልጥ ያጎለብተዋል፡፡

ሚዲያዎች እና ሐሳብን የመግለጽ መብት፤

አንዳንድ ጊዜ ውዥንብር የሚመጣው ሐሳብን በነጻነት ከመግልጽና ገደቦቹን በቅጡ ካለመለየትም ስለሚሆን ከሕገ መንግሥቱ በመጀመር ተያያዥ መብቶችን ከገደቦቹ ለመለየት ይቻል ዘንድ የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ፡፡

በዋናነት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መነሻው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ አንቀጽ 29 ሙሉ በሙሉ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር የሚያያዙ መብቶችን እና ግዴታዎችን የሚገልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያው ንዑስ አንቀጹ ላይም ማንም ሰው የመሠለውን አመለካከት የመያዝ መብት ያለው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅ በመንደርደሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡

ከዚያ ውጭ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብና አመለካከት የመያዝ ወይም የመጣል መብትን በተመለከተ ጥበቃ ቢደረገለትም ባይደረግለትም ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የመሰለውን፣የአመነበትን፣ የፈለገውን ወዘተ አመለካከት ቢይዝ እና ሌላውን ቢተው ሌላ አካል በግዳጅ በተቃራኒው የሆነን ሐሳብና አመለካከት እንዲይዝ ወይንም እንዲጥል ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ ነው፡፡ በዋናነትም ውስጣዊ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መገድብ የሌለበት መብት ነው፡፡

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚያገለግሉ ከመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በተለይ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭቶች በተደራሽነታቸውም ይሁን በሚፈጥሩት ተጽእኖ ከሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች የላቀ ነው፡፡ ተጽእኖው አዎንታዊም አሉታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንኑ በመረዳት መንግሥትም ይሁን ሌሎች አካላት የመሰላቸውን አመለካከት ለማስተላለፍ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ከሚፈጥሩት ተጽእእኖ አንጻር አገራት ከሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በተለየ ሁኔታ ጥብው ሕግ አብጅተው፣ ደንብ ቀርጸው፣ አሠራር ዘርግተው እንደሚያስተዳድሩት የታወቀ ነው፡፡

የዩኔስኮ (UNESCO) የብሮድካስቲንግ የአሠራር መመሪያም የተጽእኖውን ደረጃ ካስረገጠ በኋላ ደንብ የማስፈለጉን ጉዳይ በተመለከተ ሁለት ዓቢይ መነሻዎች እንዳሉት ያስረዳል፡፡

የመጀመሪያው የሚገናኘው ከዴሞክራሲ ጋር ነው፡፡ አገራት የሚፈልጉትን ማኅበረሰብ ለመቅረጽ፣ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ይቻል ዘንድ ጥበቃም ደንብም ያስፈልገዋል፤የሚል ይዘት አለው፡፡ ሁለተኛው አመክንዮ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ ንግድም፣ኢንቨስትመንትም ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሳዎችን ለማሳለጥና ለማበረታታት ከሚኖረው አስተዋጽኦ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡

በመሆኑም፣ሁለቱም ምክንያቶች ይህንን ዘርፍ በአግባቡ መተዳደር ያለበት መሆኑን ለማስረዳት ይቀረቡ ናቸው፡፡ አሉታዊውን በመቀነስ አዎንታዊውን ለማጎልት የሚረዱ የሕግና የሥነ-ምግባር ደንቦችን መተግበርም ማስተዋወቅም የተጀመረው እነዚህ ሚዲያዎች ሲፈጠሩ ጀምሮ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት ዴሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ፣ መብቶች ስለሚገደቡባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን በአስረጅነት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ከእንዚህም ውስጥ አንዱ እና በሰፊው የሚታወቀው ‘የጉዳት መርሕ’ ነው፡፡ በዚህ መርሕ መሠረት መብት ሊገደብ የሚገባው የሌላን ሰው መብት የሚጎዳ ከሆነ ነው፡፡ የገደቡ ምክንያት ሌሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ የራስን ሐሳብ በሚያስኬደው መጠን እና ጥግ ድረስ ለመግለጽ እንጂ ሌላ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሰጥ ጥበቃ መሆን እንደሌለበት ይገልጻል፡፡

ሌላው፣የጥፋት መርሕ የሚባለው ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ ጥፋት ወይንም የወንጀል ባሕርይ ካለው ማለትም ንግግሩ የሚመለከተው ሰው መጠን፣የተነገረበት ወቅት እንዲሁም ፣የተናጋሪውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ማኅበረሰቡን ማስቀየሙን ወይንም ጥፋት መሆኑን ብሎም ከመገድብ በመለስ በሌላ መንገድ ማስቀረት የማይቻል ከሆነ ሊገደብ እንደሚገባው የሚያስረዳ መርሕ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ማድረግ ሌሎችን ይታደጋል፡፡

የብሮድካስት አገልግሎት በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 29 ላይ የተገለጸውን የዜጎችን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ ሁነኛ ዘዴ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም ሚዲያ ደግሞ ሊተላለፋቸው የማይችላቸው ገደቦች አሉበት፡፡ እነዚህ ገደቦችም በዋናነት በሕገ መንግሥቱ በዚሁ አንቀጽ ላይ ተዘርዝረዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡

የብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎችን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕግ የሚገደብባቸው ‘የወጣቶችን ደህንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብኣዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ ውጪ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ ሐሳብን በነጻነት በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይንም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ነው፡፡

ከላይ ከተገለጹት አራት መሠረታዊ ገደቦች በስተቀር በአገሪቱ በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው አካል ይዘቱን መሠረት ያደረገ ሐሳብን በነጻነት መግለጽን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም፡፡ አራቱ በተራቸው ወደበርካታ ዝርዝር ክልከላ ሊመነዘሩ ይችላሉ፡፡ ሲመነዘሩ ቢኖሩም ግን የግለሰብን መብት እና ሰብኣዊ ክብር፣እንደቡድን የወጣቶች አስተዳደግን የሚመለከት፣እንደተቋም ደግሞ ከጦርነት ቅስቀሳን የሚመለከቱ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡

ሕገ መንግሥቱ፣ የሚተላለፈው ሐሳብ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ የሐሳብን ነጻነት በሕግ መገደብ እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በኅትመትም ይሁን በሌላ መንገድ የሚገለጽ ሐሳብ መንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖር ወዘተ በማለት ወንጀል ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ሲከተለው ከነበረው ፖሊሲ አኳያ መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን ያህል ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም የሚገባውን አስተዋጽኦ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ይህ ከእንደገና ተመልሶ የፈጠረው ችግር መኖሩን መረዳት ቀላል ነው፡፡ በተለይ ሚዲያዎች መቻቻልን ከማጎልበት ዴመክራሲን ባህል ከማድረግ አንጻር የሚዲያዎቹ መኮስመን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉትን የተወሰኑ መልእክቶችን በቀላሉ መግራት ሳይቻል እንዲቀር አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች እና ሕጉ፤

የሬዲዮ ሥርጭት 75፣የቴሌቪዥን ደግሞ 50 ዓመታት አልፏቸዋል ከኢትዮጵያ ጋር ከተዋወቁ፡፡ በማናቸውም መለኪያ ቢመዘኑ የዕድሜያቸውን ያህል ዕድገት አላሳዩም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት እንጂ የግል ሬዲዮም ቴሌቪዥንም የለም ነበር፤በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው ሃይማኖታዊው የሉትራን ሬዲዮ (ብስራተ ወንጌል) በስተቀር፡፡

አሁን ላይ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝተው ሥራ ላይ የሚገኙ 20 የብሮድካስት ሚዲያዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር፣ ከውጭ የሚተላለፉትን የሃይማኖትና እና ሌሎች የመዝናኛ የብሮድካስት ሚዲያዎችን አይጨምርም፡፡ እንዲሁም፣በኤሌክትሮኒክ ብቻ የሚሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎቶችን አይዝም፡፡

ከሚፈጥረው ተጽእኖ አንጻር የብርድካስተሮች ለረጅም ዘመናት ሳይስፋፉ መቅረታቸው ጉዳታቸው ያው ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ መገንባት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚያም ነው የብሮድካት አገልግሎት አዋጁ ቁጥር 533/1999 ዓ.ም. ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ መርሆችን የዘረዘረው፡፡

አዋጁ በመርህነት ካስቀመጣቸው ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቅና ሚዛናዊ መሆን አንድኛው ነው፡፡ ለሥርጭት የሚቀርብ ማንኛውም ፕሮግራም ከይዘት አኳያም ይሁን ከምንጭ ትክክል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሚሰራጨው ፕሮግራም ዜና ከሆነም በቅድሚያ ዜነው እውነትም ትክክልም መሆን አለበት፡፡ ትክክልና እውነት መሆን ብቻ አይበቃም፤ሚዛናዊ እና ከአድልኦ የጸዳ መሆን አለበት፡፡ ብሮድካስተሮች እነዚህን መርሆችን የመከተልና የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ መፈጸም ያለባቸው ተግባራት ናቸው፡፡

በብሮድካስት አዋጁ ላይ የተጣሉበትን ግዴታዎች ያልተወጣ ወይንም የጣሰ ብርድካስተር ሥርጭት ከመስጠት በጊዜያዊነት ሊታገድ ይችላል፡፡ ከመታገድ አልፎም ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ ሊሰረዝም ይችላል፡፡ ፍቃድ የሚያሰርዙ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ተገቢነት ያላቸውን ምክንያች ብቻ ከአዋጁ አንቀጽ 30(4) ላይ እንጥቀስ፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው ብሮድካስተሮች የሚያሰራጩት ፕሮግራሞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ብሮድካስተር እንዳይፈጽሙ የተከለከሏቸው ተግባራት አሉ፡፡ የሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች ፍጹም መሆን የሌሉባቸውን ጉዳዮች ተዘርዝሯል፡፡

ማንኛውም ብሮድካስተር መፈጸም ከሌለባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰው ልጅን ሰብእና፣ነጻነት፣ሥነ-ምግባር እና እምነት የሚያንኳስስ እና የሚጻረር ፕሮግራም ማስተላለፍ የለበትም፡፡ የግለሰብን ሰብእና ነጻነት ፣ እና የቡድንንም ይሁን የግለሰብን እምነትና ያጎለበታቸውን በጎ ሥነ-ምግባሮች የማጣጣል ይዘት ያለውን ፕሮግራም ማሰራጭት ክልክል ነው፡፡

የሚተላለፈው ፕሮግራም በራሱ የመንግሥት ተቋማት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ከሆነም ፍጹም ክልክል ነው፡፡ ለአብነት የመንግሥት የጸጥታና የደኅንነት ተቋም ወይም መከላከያ ሠራዊቱን የሚመለከቱ መረጃዎች ሆነው መሰራጨታቸው አገሪቱን ስለሚጎዳ ከተከለከሉ እነዚህን ማስተላለፍ እንደማይቻል ከሕጉ መረዳት ይቻላል፡፡

ሌላው ማንኛውም ብሮድካስተር ማስተላለፍ የማይችለው ግለሰብን፣ቡድንን (ብሔርን፣ሃይማኖትን ወዘተ) እና ድርጅትን ስም የሚያጠፋ፣ በውሸት የሚወነጅል መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ስም ማጥፋት ሲባል የመረጃውን እውነትነት ብቻ የሚመለከት አለመሆኑን ነው፡፡ ቁምነገሩ መረጃው እውነት ቢሆንም እንኳን የቀረበበት ዓላማ፣የአሰራጩ ፍላጎት ሆን ብሎ ስም ለማጥፋት ከሆነም የማይፈቀድ መሆኑ ነው፡፡ እውነት ብቻው ከተጠያቂነት ላያድን ይችላል፡፡

በአዋጁ ላይ ሌላው በገደብነት የተቀመጠው ሕዝብን ከሕዝብ ወይም አንድ ብሔርን ከሌላ የሚያጋጭ እንዲሁም ጦርነተን የሚቀሰቅስ ይዘት ያለውን ፕሮግራም ማስተላለፍ አለመቻሉ ነው፡፡ እዚህም ልብ ልነለው የሚገባው ጉዳይ የሚተላለፈው ወይም የሚሰራጨው ፕሮግራም ይዘቱም ይሁን ምንጩ ትክክልና እውነት መሆን ወይም አለመሆን መለኪያ አይደለም፡፡ የተከለከለው፣ የሚተላለፈው ፕሮግራም አንድን ብሔር ከሌላ ሊያገጭ የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ሆኖም የሚያጋጭ ከሆነ፣ትክክለኛ መረጃም ሆኖ የእርስ በርስም ይሁን ከሌላ አገር ጋር ጦርነትን የሚቀሰቅስ ከሆነ ብሮድካስተሮች ማሰራጨት አይችሉም፡፡ እነዚህ ክልከላዎች የተቀመጡት አዋጁ አንቀጽ 30(4) ላይ ነው፡፡

ክልከላዎች ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጠቀሱት አራት ገደቦች በጣም የሰፉ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ አኳያ የሚገለጸውን ነገር ይዘቱ መሠረት በማድረግ ወይንም በመገለጹ ምን እንደሚያመጣ ከግምት በማስገባት የሚከለክል ሕግ እንደማይወጣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ እርግጥ ነው ብሔራዊ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮችንም ለገድብ በምክንያትነት አልተቀመጡም፡፡ በርካታ አገራትና በእኛም አገር በተለያዩ ሕች ላይ ግን በገደብነት ተቀምጠዋል፡፡

ክልከላዎቹ ሕገ መንግሥታዊ ይሁንም አይሁኑም፣ በመገደብና እና መረጃዎቹን ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ አንጻር አገራዊ ጥቅምና ጉዳታቸው የትኛው እንደሚያመዝን ጥናትና ምርምር ቢያስፈልገውም አሁን ባሉት ሕጎች ግን ክልከላዎቹ የጸኑ ናቸው፡፡

የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እንደ ገደብ፤

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሚገደብባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የትኛውም ዓለም አቀፍ ሰነድም ይሁን ብሔራዊ ሕግጋት ከሚጋሯቸው አንዱ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ነው፡፡ የጦርነቱ ፕሮፓጋንዳው የዕርስ በርስም ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ነገር ግን በተለያዩ ብሔሮች፣ጎሳዎች፣ሃይማኖተኞች ወዘተ መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያለማቋረጥ ማነሳሳትም እንዲሁ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የጦርነት ፕሮፓጋንዳን አያካትትም ማለት ነው፡፡

ለፕሮፓጋንዳ የሚውሉ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች በራሳቸው እንደ ጥቃት ከመሆን አልፈው አካላዊ ጥቃትን ጠሪ ናቸው፡፡ በድንገት በሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ቡድናዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ አስቀድሞ የተነዛው ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ከሆነም በድንገት የሚፈጠር ግጭትን በግለሰብ ደረጃ ብቻ መግታት አዳጋች ይሆናል፡፡

ከፊት ለፊቱ ሲታይ ፕሮፓጋንዳውን፣ማነሳሳቱን የሚፈጽሙት ሚዲያዎች ቢሆኑም፣ሚዲያዎቹ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዩጎዝላቪያና በሩዋንዳ የሆነውም እንዲሁ ነው፡፡

በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የፕሮፓጋንዳ ይዘት ያላቸውን መልእክቶች ውጤት አልባ ማድረግ የሚቻለው ተአማኒ፣ግልጽ፣የሐሳብ ብዙኃነት ማስተናገድን ባሕርይው ያደረገ፣ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ በማስፈን ነው፡፡ መዝጋትና መከልከል መፍትሔ አለመሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ማኅበረሰቡም የሚያገኛቸውን መረጃዎችን ዕውነትነታቸውን የሚያጣረበትን አማራጭ ማስፋት ነው፡፡

የብሮድካስት ሕጉ እና አተገባበር ለፌ ወለፌነት፤

ከላይ የተጠቀሱትን ክልከላዎች መተላለፍ ፍቃድን ያስነጥቃል፡፡ በወንጀልም ያስጠይቃል፡፡ ለደረስውም ጉዳት በፍትሐ ብሔር ካሳ መክፈልን ያስከትላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያገጭ ሐሳብ ወይም መልእክት ከተላለፈ በኋላ አንድም ጥላቻን በሕግ ብዙም መፋቅ ስለማይቻል፣እልቂት ከደረሰም በምንም መልኩ የሚካስ ስላልሆነ ከሕግ ባለፈም ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ኃላፊነት መላበስን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ሥራ ላይ ለማዋል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ያለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ስለሆነ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ የሚሠራጩትን የብሮድካስት አገልግሎቶች ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የመከታተል እና የመቆጣጠር ሥልጣን በሕግ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለሥልጣኑ የመቆጣጠር ሕጋዊ አድማሱ የሚቆመው ከኢትዮጵያ የሚሰራጩት ላይ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ መልክ የሚተላለፉትን የብሮድካስት አገልግሎቶች አይጨምርም፡፡ ከኢትዮጵያ ቀርጸውና እና አዘጋጅተው ከውጭ አገር የማሰራጪያ ጣቢያ የሚለቀቁትንም አይቆጣጠርም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ የብሮድካስት አገልግሎት ለመሥጠት ፈቃድ ሊያገኙ አይችሉም፤በሕግ ስለተከለከለ፡፡

እንግዲህ በሕግ የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካሰት ፈቃድ ሊሰጣቸውም፣አገልግሎት ሊሰጡም አይችሉም፡፡ በሕግ ክልክል ነው፡፡ በተግባር ግን በርካታ የሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለሥርጭቱ የሚሆኑት ቀረጻዎችም በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ከሌላ አገር ተሰራጭተው ተመልሰው ለኢትዮጵያውያን ይቀርባሉ፡፡ ሕጉ በአገር ውስጥ ፈቃድ በማውጣት የብሮድካስት አገልግሎት መስጠትን ቢከለክልም ዞሮ ዞሮ ሥርጭቱ ግን አለ፡፡ ከዚህ አንጻር ሕጉ ማሳካት የፈለገውን ግብ አላሳካም፡፡ በቁጥር ሲሰላም ሃይማኖታዊ ካልሆኑት ይበልጣሉ፡፡ ሕጉ እና እየሆነ ያለው እዚህ እና እዚያ (ለፌ ወለፌ) ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ደግሞ የብሮድካስት ሚዲያ የሚመራባቸው መርሆች አሉ፡፡ ሊከተላቸው የሚገባም የሥነምግባር እና የሕግ ኃላፊነቶችም አሉበት፡፡ መተላለፍ የማይችላቸው ገደቦችም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንም ይሄንኑ የማስከበር እና የመቆጣጠር በሕግ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

ይሁን እንጂ፣በ1999 ዓ.ም. የወጣው የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በተለያዩ ሞገዶች አማካይነት በተለመደው መንገድ የሚያሰራጩትን እንጂ በኢንተርኔት (በመካነ ድር/web site) አማካይነት የሚሰራጩትን የመከታተል እና የመቆጣጠር ሥልጣን ስለመኖሩ የተቋቋመበት አዋጅ አያመለክትም፡፡ በመሆኑም፣ በሕጉ ላይ ከታሰበው በተጨማሪ የሚሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎቶችን መከታተልና መቆጣጠር አይችልም፡፡ በተግባር ግን በርካታ ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ በእጅ ስልኩ ይከታተላል፡፡ ባለቤታቸው ከግለሰቦች ጀምሮ የፖለቲካ ድርጂቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሕጉ፣ ብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎች ሊያከብራቸው የሚገቡትን ሁኔታዎች ቢዘረዝርም ሕጉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው 20 የብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ የትየለሌ፣አዋጁ የሚመለከታቸው እንዲሁም ባለሥልጣኑ የሚከታተላቸው ሁለት ደርዘን የማይሞሉ፡፡ ሕጉ እና በተግባር እየሆነ ያለው እዚህ እና እዚያ (ለፌ ወለፌ)፡፡

ለኢትዮጵያዊያን እንዲሆኑ ታስበው የሚሰራጩት የብሮድካስት አገልግሎቶች በርካታ ቢሆኑም የብሮድካስት ባለሥልጣኑ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን አማካይነት ሊከታተላቸውና ሊቆጣጠራቸው የሚችለው ግን 20 ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ 20 ተቋማት የሚሰጣቿው አገልግሎቶች እንደ ሕጎቹ መሆናቸውን መከታተል ይችላል፡፡ ሕግ ከጣሱም አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በተመሳሳይ መስክ የተሰማሩ ነገር ግን ከሌላ አገር የሚሰራጩ እንዲሁም በኢንተርኔት የሚተላለፉት ላይ ግን ሥልጣን የለውም፡፡

የብሮድካስት አዋጁ ሲወጣ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰፍን በማሰብ በዓላማነት ይዟቸው የተነሳውን ግቦች ብሎም እንዲፈጠር የታሰበውን ማኅበረሰብ፣ እንዲከበሩ የተፈለጉትን ግዴታዎች በፍጹም ለማሳከት አይችልም፡፡ ከእሱ ቁጥጥር ውጭ በርካታ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች ስላሉ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የተቀመጡ ገደቦች የማይመለከታቸው አሉ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ከሕግ አንጻር ብቻ ሲታይ ነው፡፡

ከላይ የቀረበው የሕግ እና የተግባር ለፌ ወለፌነት እንዳለ ሆኖ በባለሥልጣኑ ሥር የሚገኙ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች አልፎ አልፎ ችግር እየተስተዋለባቸው ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቢኖር፣ ባለሥልጣኑ ስለችግሮቹ አስተያየት የሚሰጠው ከሕዝብ ብዙ ጩኸት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ዋና ተቆጣጣሪ እየሆነ የመጣውም ሕዝቡ ይመስላል፡፡ በእርግጥ ባለሥልጣኑ እስካሁን ዕርምጃ አልወሰድም፡፡ ያልወሰደበት ምክንያቶችን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ናቸው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት እና በተለያዩ የሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች እንደዘገቡት “የመጀመሪያው ጉዳይ የችግሩ ምንጭ ሚዲያው ሳይሆን ሌላ የተደበቀ ጉዳይ በመሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉም ሚዲያ በአመለካከት ረገድ ችግር ያላባቸው ስለሆነ … “ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የዋና ዳይሬክተሩ የመጀመሪያው ምክንያት በሕግም ይሁን በሌላ መለኪያ ዕርምጃ ለመውሰድ በምክንያትነት የሚያገለግል እንጂ ላለመውሰድ ሊሆን አይችልም፡፡ የትኛውም የሚዲያ ተቋም (የብሮድካስትም ጭምር) ፈቃድ ላገኘበት እንጂ ከዚያ ውጭ የሆነ ተግባር ውስጥ መሰማራት አይችልም፡፡ “ሌላ የተደበቁ ጉዳይ” ከፈጸመም የተቋቋመበትን ዓላማ እና ሕጉንም ስለሚጥስ እንዲያስተካከል ማድረግ የባለሥልጣኑ ግዴታ ነው፡፡

ሌላ የተደበቀ ጉዳይ መኖሩን ባለሥልጣኑ አውቆ ዕርምጃ አለመውሰድ ባለሥልጣኑ በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አለመወጣት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም፣ “ሌላ የተደበቀ ጉዳይ” ካለ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጭው አስተዳደራዊም ይሁን ሌላ ዕርምጃ አይወሰድበትም የሚል በአዋጁ ላይ የተገለጸ ነገር የለምና!

የዋና ዳይሬክተሩ ሁለተኛው ምክንያት ሁሉም ሚዲያዎች በአመለካከት ረገድ ችግር ስላለባቸው ነው ብለዋል፡፡ ከእዚህ አንጻር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያስተዋላቸውን ችግሮች ቶሎ እንዲቀርፉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን፣ባለሥልጣኑ አትኩሮት ማድረግ ያለበት ከሕግ አንጻርም ሊለካ የሚችለው የሚዲያዎቹ የአመለካከት ችግር መኖር ወይም አለመኖር ሳይሆን ያስተላለፉት/ያሰራጩት ፕሮግራም ይዘት ላይ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ መላቅጡ ባልለየ አሉባልታና የሴራ ፖለቲካ ትንታኔ በተለያዩ ሚዲያዎች እየታመን ባለንበት ወቅት እንዲሁም በቀላሉ የብሔር መልክ የሚይዙ ግጭት በአገራችን በተለያዩ ክፍሎች እየተፈጠሩ ባለበት ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ትኩረት ሕግ በማስከበር ወይም እንዲያከብሩ በማድረግ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንጂ ወደ ፊት ሥልጠና መስጠት ሊሆን አይችልም፡፡

Filed in: Amharic