>

የሼሁ 'መታሰር'? (መሳይ መኮንን)

በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መድረኮች ላይ ሚናቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ነጋዴ፡ ባለሀብት ብቻ ተብለው የሚገለጹ አይደሉም። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በማሾር፡ ባልስልጣናትን ከእግራቸው ስር በማድረግ እንደፈለጋቸው፡ እንዳሻቸው ሲሆኑ የከረሙ ናቸው። ሼሁ ከኢኮኖሚው ጡንቻቸው ባልተናነሰ በፖለቲካው ውስጥ ያላቸው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ለነገሩ የኢኮኖሚው ጥንካሬ ያለፖለቲካ ጉልበት ብዙም ውጤታማ አይሆንም። በአጭሩ ሼህ ሁሴን አላሙዲን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አቅም ካላቸው ተረታ የሚመደቡ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ታስረዋል በተባሉት የሳዕዲ አረቢያ ቱጃሮች ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰው እሳቸው ስለመሆናቸው እርግጠኛ የሚያደረግ መረጃም ሆነ ማስረጃ አልወጣም። የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባም የአረብ ሚዲያዎችን ዋቢ ከማድረግ ያለፈ በራሱ ዜናውን ለማረጋገጥ የቻለበት መንገድ የለም። ፎቶግራፋቸው ከታሰሩት ውስጥ አብሮ የሚገኝ በመሆኑ እውነተኛነቱን የሚያጠናክር ይመስላል። አንዳንድ ፍንጮችም ያንን ይመሰክራሉ። በእሳቸው ቀለብ ከሚሰፈርላቸው ሰዎች አንዱ ‘ጋዜጠኛ’ ሺሁ ተጠርተዋል ሲል ገልጿል። ‘ተጠርተዋል’ የሚለውን ታስረዋል በሚለው ተርጉመን አንብበነዋል።

የታሰሩት ከፍተኛ ቱጃሮችና ባለስልጣናት ናቸው። ከባለስልጣናት የንጉሱ የኢኮኖሚ አማካሪና የባህር ሃይል አዛዡ ከስልጣናቸው መነሳታቸው ታውቋል። መታሰራቸው ግን አልተረጋገጠም። ልዑል ወሊስ ቢን ጣላል ከታሰሩት 11 ልዑላንና 38 ባለሀብቶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጥ ይገኙበታል። ልዑሉ የሀብታቸው መጠን 17ቢሊየን ዶላር ደርሷል። በታላላቅ የሚዲያ ተቋማት፡ በባንኮችና ኢንሹራንሶች፡ በቲውተር ኩባንያና በበርካታ የምዕራቡ ዓለም ግዙፍ የንግድ ኢምፓየሮች ውስጥ ጠቀም ያለ አክሲዮን ያላቸው ቱጃር ናቸው።

ሳዑዲ አረቢያ የወሰደችው እርምጃ ዋጋ ያስከፍላት ይሆን? ሙስናው ከንጉሱ ቤተሰብ ደጃፍ መድረሱ ምን ለውጥ ያመጣል? በሂደት የሚታይ ነው።

ሳዕዲ አረቢያ ያሉ ወዳጆቻችን እንዳጫወቱን ሼህ ሁሴን አላሙዲን ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ከንጉሱ መንደር የሚሰሙት ድምጽ የተመቻቸው አይደለም።በህወሀት መንግስትና በሳዕዲ አረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰብ መሃል ሆነው ሲያገናኙ፡ ሲያደራድሩ፡ የሚታወቁት ሼሁ በተለይ ከሳዑዲ ስታር ኩባንያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ኪሳራ ግንኙነታቸውን ሳያሻክረው እንደማይቀር ይገመታል። ይሁንና ሼሁና የንጉሱ ቤተሰብ ወደለየለት ጥል የከተታቸው ጉዳይ የሼሁ በሳዑዲ አረቢያ ያላቸው የንግድ እንቅስቃሴ ችግር መግጠሙ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሼህ ሁሴን አላሙዲ ትልልቅ የሳዑዲ መንግስት ፕሮጀክቶችን ይሰራሉ። ያላቸው ግንኙነት ሊዚህ ጠቅሟቸዋል። ምናልባትም ከሙስና ጋር በተያያዘ ከታሰሩም በእነዚህ ፕሮጀክቶች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የክፍያ መዘግየት ሰበብ ተደርጎ ሼሁ የሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች ቆመዋል። ትራንስ ዴዘርት የተሰኘው የሼሁ ኩባንያም ከመዘጋት አፋፍ ተጠግቷል። እንቅስቃሴአቸው እንደቀድሞ ሊሆን አልቻለም። ይህን የተረዱት ሼህ ሁሴን አላሙዲን ትኩረታቸውን ወደሌሎች አከባቢዎች ማድረግ እንደጀመሩ ይነገራል። የተወስኑ ሀብቶቻቸውን ከሳዑዲ አረቢያ በማሸሽ ወደ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገሮች መውሰድ ጀምረዋል። ይህ እንቅስቃሴአቸው ይበልጥ ጥርስ እንዲነከስባቸው አድርጓል።

ሼሁ በህወሀትና በሳዕዲ መንግስታት መካከል ድልድይ መሆናቸው ጋር ተያይዞ በቅርቡ የተፈጠረው የአረብ ሀገራት የጦዘ ፍጥጫንም የሚጠቅሱ ወገኖች አሉ። በኳታርና በአምስት የአረብ ሀገራት መካከል በቅርቡ የተከሰተው የከረረ ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት የሼሁን ግንኙነት ሳያበላሸው አይቀርም። የህወሀት መንግስት ከኳታር ጋር ግንኙነቱን ማጥበቁ፡ አልጀዚራ አዲስ አበባ ጽ/ቤት እስከመክፈት መድረሱን የሚጠቅሱ ወገኖች ይህ አካሄድ የህወሀት መንግስት የልብ ወዳጅ በሆኑት ሼሁ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፈጠሩ ይነገራል። ሳዕዲ አረቢያ፡ ሼሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያደርጉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በፊትም ደስተኛ አይደለችም የሚል ሹክሹክታ ይሰማል።

ሼህ ሁሴን አላሙዲን ከበፊት ጀምሮ ከሳዑዲ አረቢያ የንጉሳውያን ቤተሰብ የማይወደድላቸው ባህሪም እንዳላቸውም ይነገራል። በተለይም ከጾታዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚታሙበት ባህሪያቸው ለሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰብ ፈጽሞ ምቾት የሚሰጥ አልነበረም። በሙዚቃ ኮንሰርቶችና ሌሎች የእስልምና እምነት የሚከለክላቸውን ነገሮች ሼሁ በአድባባይ የሚያደርጉት መሆናቸው ከፍተኛ ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል። ይህም በቋፍ ላይ ለነበረው ግንኙነታቸው እንደአንድ ሰበብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ዛሬ በሳዑዲ አረቢያ ታሰሩ የተባለው እውነት ከሆነ የህውሀት መንግስት አቋም ምን ሊሆን ይችላል?በአሰላለፍ ሼሁ የመለስ ዜናዊ ቡድን ውስጥ የሚገኙ እንደሆነ ይነገራል። ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የሼሁ እንቅስቃሴም በአደባባይ ጎልቶ የማይታየው ሌላኛው የህውሀት አንጃ የበላይነት በመያዙ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ሼሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ድምጻቸው እንደቀድሞው አይሰማም። በኦሮሚያ ክልል የወሰዷቸው አንዳንድ ግዙፍ መሬቶች እንዲነጠቁ መደረጉን እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ነው። ከሼራተን ሆቴል ጋር ተያይዞ የሚነሳባቸው የመሬትና የብድር ጉዳይ አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያባንናቸው መሆኑ አልቀረም። ህወሀት ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍልና በአጠቃላይ ሀገሪቱ የምትገኝበት የተመሰቃቀለ የፖለቲካ ገጽታ ለሼሁ የአደጋ ምልክት ነው።

ሳዑዲ አረቢያ አለተመቻቸውም።የኢትዮጵያ ሁኔታ አላማራቸውም።

የታሰሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ፖለቲካዊ አንደምታው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም ነበር። በእሳቸው ዳርጎት ለሚታዳደሩት በየትም ቢታሰሩ ዜናው ከባድ መርዶ ነው። በፖለቲካ ሽርክና በጥቅም ለተገናኙ የህወሀት መንግስት ባልስልጣናት ግን የሳዑዲው እስርም ሊያስደነግጣቸው ይችላል። በሀገር ቤት ቢሆን ደግሞ አብረው ተያይዘው ከርቸሌ መውረዳቸው፡ በህወሀት መንግስት ህልውና ላይም ጉልህ አደጋ መደቀኑ አይቀርም።

Filed in: Amharic