>

ከዛሬው የመቀለ ውሎ ልንረዳቸው የምንችላቸው አራት ነገሮች...

                                                                              በዮናስ ሃጎስ

1) ተራሮችን ያንቀጠቀጠው የትግራይ ትውልድ አሁን ደብዛው ጠፍቷል። የትግራይ ሕዝብ ወይ ሰልችቶታል አሊያም በከፍተኛ ፍርኃት ውስጥ ነው የሚኖረው ወይንም የሕወሐት ደጋፊ ነው። ሮማናት አደባባይ ከተሰበሰበው ወፈ ሰማይ ወጣት ውስጥ አንድም እነ አምዶምን ልቀላቀል ብሎ ደፍሮ የወጣ ወጣት አለመኖሩ እጅግ በጣም ያሳዝናል። የትግራይ ወጣት ለኳስ ብቻ ሲሆን ይሆን እንደዛ የሚያብደው? መቀለ ሮማናት አደባባይ ከወታደሮች ጀርባ ቆመው እነአምዶምን ልክ ከሌላ ዓለም የመጣ ፍጡር አስመስለው ሲታዘቡ በነበሩ የትግራይ ወጣቶች በጣም አፍሬባቸዋለሁኝ።
*

2) ሕወሐትና የትግራይ ሕዝብ አንድ አይደሉም። ሕወሐት በመጀመርያ የሰልፉ ዓላማ ኦሕዴድ ላይ ያነጣጠረ ስለመሰላት ሰልፉ እንዲካሄድ ፈልጋ ነበረ። እነአምዶም  (አረናዎች ብዬ አፌን ሞልቼ ያልጠራሁት ባለፈው አረና አደረገው በተባለው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኘው ቁጥር ሩቡን የማይሞላ ሰው ነው በዛሬው ሰልፍ ያየሁትና ሁሉንም ለማካተት ይከብደኛል) የሰልፉ ዓላማ የትግራይ ሕዝብ በሕወሐት ላይ ያለው ምሬቱን የሚገልፅበት እንዲሆን ማድረግ መፈለጋቸው ሲሰማ ሰልፉን ከማገድ ጀምሮ እነ አምዶምን ትላንት ማታ ለተወሰነ ሰዓታት በማሰር መፈክራቸውን ቀዳደው ጥለውባቸዋል። ዛሬ ጠዋትም ሮማናት አደባባይን ከሰልፈኛውም ሆነ ዳር ተመልካቹ አስቀድሞ የሞላው በወታደር ነው። እዚያ አደባባይ ዳር ቁሞ ሲመለክት ለነበረ ለእያንዳንዱ ወጣት አንድ ፖሊስ እስኪመስል ድረስ ሮማናት በወታደሮች ተጥለቅልቃ ነው የዋለችው። ሕወሐት እንደሚፎክረው ሕዝቡ የኔ ነው ቢል አንድም ወታደር ማሰማራት ባላስፈለገው ነበረ።
*
3) ትግራይ በዚህ 26 ዓመታት ውስጥ ጀግኖች አፍርታለች ከተባለ በአንደኛው ተርታ ላይ ሊቀመጥ የሚገባው Amdom Gebreslasie ነው። በዚያ ሁሉ ወታደር ፊት ሜጋፎን ይዞ መፈክር እያሰሙ ከኋላ ጥቂትም ሰዎች ቢሆኑ ትንሽ ናቸው እኮ ብሎ ሳይንቅ መምራት መቻል በእውነት ትልቅ ጀግንነት ነው። ‹ሰልፉ የስኳር ወረፋ ሰልፍን አያክልም› ብለው የሚሳለቁ ሰዎች ይህን መንግስት በጣም ፈርተው ባህር ተሻግረው ርቀው የተቀመጡ መሆናቸውን ሳስበው እገረማለሁኝ። አዎ የትግራይ ሕዝብ ወይ ከመጠን ያለፈ ፍርኃት ውስጥ ነው አሊያም ስልችት ብሏል። ግን እነአምዶምና ተከታዮቹ በትግራይ ውስጥ ሊካሄድ ስለሚገባው ለውጥ ፋናወጊዎች ለመሆን ራሳቸውን ለአደጋ አሳልፈው ሰጥተዋልና ይህን ተግባር ለማንቋሸሽ መሞከር ካንድ ሕሊና ካለው ሰው የሚጠበቅ ነገር አይደለም።
*
4) አረና የሚፎክረውን ያህል የሕዝብ ድጋፍ ቀርቶ የራሱን አባላቶች እንኳን እዚህ ሰልፍ ላይ ለማየት አልታደለም። ባለፈው አብርኃ ደስታ ሊቀመንበር ተደርጎ በተመረጠበት ስብሰባ ላይ እንኳን የተገኘው ተሳታፊ በጣም ብዙ እንደነበረ አስታውሳለሁኝ። ከነዚያ ሁሉ አባላት ዛሬ ሮማናት አደባባይ የተገኙት ሰባት አባላት ብቻ መሆናቸውን አረና ሕዝቡን በማደራጀትና በማንቃት በኩል ምንም ዓይነት ስራ እንዳልሰራ ነው።
***
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ነፃ የምትወጣው ወያኔን ፈርተው ባህር ተሻግረው ከኪቦርድ ጀርባ በተቀመጡ ልጆቿ ሳይሆን እንደነ አምዶም ትንሽ ነን፤ ሰዉ ምን ይለናል፤ ፖሊሶቹ ትላንትም አስረውን ነበረ… ምናምን ሳይሉ በፀናት በሚቆሙ ልጆቿ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic