>
5:13 pm - Friday April 19, 9816

የትግራይና የተቀረችው ኢትዮጵያ ወጣት ለቅሶ ለየቅል ነው (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የትግራይ ወጣቶች ጥያቄ ምንድን ነው? ምንድን ነው የሚፈልጉት? ቢቢሲ አማርኛው የትግራይ ወጣቶች ከህወሀት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ይሆን ሲል የጠየቀበትን ዘገባ አነበብኩት። በቅድሚያ የትግራይ ወጣቶች የሚለው አገላለጽና በዘገባው አስተያየታቸውን የተጠየቁትን ግለሰቦች ስናይ ”ከትግራይ” ይልቅ ”የህወሀት ወጣቶች” የሚለው ሀረግ ይበልጥ የሚገልጻቸው ይመስለኛል። የህወሀት አባል ያልሆነ ለዚያውም በከፍተኛ ቦታ የደረሰ ወጣት ማግኘት ይቻል ይሆን?

ወደ ፍሬ ነገሩ ለመግባት ያህል ዘገባው የትግራይ ወጣቶች በህወሀት ደስተኞች አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ የታሰበበት ነው። አስተያየት ከሰጡት መሃል በተለይ ሀገር ቤት ያሉት በተሻለ መልኩ ቅሬታ ያሉትን ያቀረቡ ይመስላል። ዋናው ጉዳይ የትግራይ ወጣቶች ጥያቄ ምንድን ነው? የሚል ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊና አንጻራዊ ሁኔታ የትግራይ ወጣቶች የመኖር ህልውናቸው አደጋ ላይ አልወደቀም። በማንነታቸው ጥቃት የሚሰነዝር፡ የሚገድልና የሚያስር ስርዓት አልመጣባቸውም። በአንጻራዊ መለኪያ የትግራይ ወጣቶች የተሻለ የትምህርትና የስራ እድል የሚያገኙ ናቸው። መረጃዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት በየትኛውም መስክ የትግራይ ወጣቶች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት የተሻለ እድል እንዲያገኙ ተደርገዋል። ህወሀት የትኛውንም ያህል ክፉ ቢሆን ለትግራይ ወጣቶች የሚጨክን አንጀት እንደማይኖረው የአደባባይ እውነታ ነው። ይህ ማለት ግን የትግራይ ወጣቶች ምንም ጥያቄ አይኖራቸውም ማለት አይደለም።

የትግራይ ወጣቶች እስር ቤት የሉም። የአማራና የኦሮሞ ወጣቶች ግን በየማጎሪያ እስር ቤቶች ናቸው። የትግራይ ወጣቶች ከሌሎች አንጻር ለስደት የሚዳርግ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ(?) ጫና የለባቸውም። በተለይ በፖለቲካው ምክንያት ሀገሩን ጥሎ የሚሰደድ የትግራይ ወጣት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። የአረና ወጣቶች ምናልባት የሚደርስባቸው ጫና ሊኖር ይችላል። ይህ ግን ከሌላው አንጻር ከቁጥርም የሚገባ አይደለም። የትግራይ ወጣት በተሻለ የትምህርት ስርዓትና ጥራቱን በጠበቀ ትምህርት ቤት ተምሮ ወደ ውጭ የትምህርት እድል አግኝቶ እንዲሄድ እድሉ ይመቻችለታል።

የትግራይ ወጣቶች በህወሀት ሊከፉ ይችላሉ። በዚህኛውም ዘገባ እንደገለጹት ህወህት ወጣቱን የትግራይ ልጅ ረስተውታል ነው። ሌላው የኢትዮጵያ ወጣት እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ቅንጦት ሊሆንበት ይችላል። እናቱ ገበያ የሄደችበትና የሞተችበት እኩል አያለቅስም። የትግራይና የተቀረው የኢትዮጵያ ወጣት ለቅሶም ለየቅል ነው። የኢትዮጵያ ወጣት ስርነቀል ለውጥ ይፈልጋል። ህወሀት ከስልጣን ወርዶ በሌላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲተካ በጽኑ ይሻል። የትግራይ ወጣቶች ጥያቄአቸው የስርዓት ለውጥ አይደለም። ህወሀት ዘላለማዊ መንግስት ቢሆንላቸው ይመርጣሉ። ዘውትር በቴሊቪዥን መስኮት የሚያይዋቸው የትግራይ ባልስልጣናት ከፊታቸው ዞር እንዲሉ አይፈቅዱም። በሽታ ቢኖርባቸውም እንኳን እንዲፈወሱ እንጂ እንዲገድላቸው አይፈልጉም::

በተለያዩ አጋጣሚዎች የትግራይ ወጣቶችን የልብ ትርታ ለመታዘብ የቻልን ይመስለኛል። ጥያቄአቸው የትግራይ መልማት ነው። ይሄ በራሱ ችግር የለውም። በሌላው ኪሳራ መሆኑ ነው እንጂ። አድሎአዊ የሀብትና የልማት ስርጭት መኖሩን እያወቁ ”ትግራይ ተበደለች” የሚል መፈክር ተለይቶአቸው አያውቅም። የህወሀት በዘር ላይ የተመሰረተውን አይን ያወጣ ዘረፋ ሲቃወሙት ሰምተን አናውቅም። ሲከላከሉለት እንጂ። ህወሀት ለእነሱ ጥሩ አባት ነው። አባት ደግሞ አንዳንዴ ሊያጠፋ ይችላል። ቢያጠፋም አትጠላውም። ለሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት ህወሀት ክፉ የእንጀራ አባት ነው። ዘውትር ዱላ ይዞ የሚገርፍ፡ ብሎም የሚገድል።

Filed in: Amharic