>

አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ በዚህ ሰአት (መስቀሉ አየለ)

ገና ለጋ ሳለ በማርክሲዝም አስተሳሰብ ርቆ የሄደው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኢንጂነሪንግ ተማሪ የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ ከኢህአፓ ትግል መክሸፍ በኋላ እንደማንኛውም የዘመኑ ወጣት በሱዳን በኩል ወደ አውሮፓ በማቅናት ዱር ቤቴ ብሎ ወደ ኤርትራ በራሃ እስከወረደበት ግዜ ድረስ በዚያው ቆይቷል።

ሆኖም ግን አንዳርጋቸው በአውሮፓ የዩኒቨርሲቲ ቆይታው በወጣትነቱ ከተማረው የኢንጂነሪንግ ትምህርት በማፈንገጥ ነፍሱን ሲበላው ለከረመውና የርሱን ትውልድ በዚያ ደረጃ እንደዛ አድርጎ ያሰከረው ነገር ምን እንደሆነ ሚስጥሩን ፍለጋ ቢረዳኝ በሚል ፍልስፍና ተማረ። ሆኖም ግን ትምህርቱን ከጨረሰም ቦሃላም እንደ ማንኛውም ስደተኛ ቤትና ትዳር ወደሚል የግል ሩጫ ሳያዘነብል ከሰው ገለል ብሎ ብሎ ብዙ በማንበብና ብዙ በማሰብ በተመስጦ ውስጥ ቆይቷል።

ግለ ታሪኩ እንድሚያስረዳው አንዳርጋቸው በብዙ መልኩ አውሮፓ ውስጥ የተባህትዎ ኑሮው የእርሱ መገለጫው እንደነበርና ለዚህም አስረጅው ነገር ከባእቱ ሳይወጣ እረጅም ግዜ የሚያሳልፍ ፣ ብዙ ባለመብላት ይልቁንም ከእፍኝ ቆሎ ጋር ትንሽ ቡና በመጠጣት ሰውነቱን ድካም ሳይሰማው ብዙ የሚያነብና ብዙ ከመናገር አርምሞን የሚመርጥ ሰው ነበር።

በዚህም የተነሳ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ሳይወሰን ዘ ስካይ ኢዝ ዘሊሚት በሚል ስሌት ፈርጀ ብዙ እውቀቶችን ለማዳበር የቻለ ሰው ነው አንዳርጋቸው። አንዳርጋቸው ጽጌ ሁሌም ተማሪ፣ በየትኛውም የእውቀት ዘርፍ ላይ መናገር ሲጀምር የሚያስደምም አንደበተ ርትኡ፣ ከምንም በላይ ከሰዎች በታች ዝቅ ብሎ ማንንም ለመስማት ትእግስት ያለው ነገር ግን አንድ ግዜ ላሰመረበት መስመር የማይደራደር እንደ ፌሮ የማይታጠፍ የመርኽ ሰው በሉት እልከኛ ነው።

አንድ ምሳሌ ላንሳ፤

አንዳርጋቸውን በአንድ ወቅት አንድ የሆነ አፍሪካ አገር ውስጥ አግኝቸው በራሱ አንደበት እንዳጫወተኝ ሲጋራ ያጨስ እንደነበር፤ ያም ሆኖ ግን ይህንን ስሜቱን እንደማይወደው ለዚህም እንዲረዳው ወደ ህክምና ማእከል ሄዶ ሲጋራ ለማቆም የሚያስችል ልዩ ልዩ ቴራፒ ለመውሰድ ሞክሮ አንዱም አይነት መንገድ ሊሰራለት እንዳልቻለ ፤ ነገር ግን ባንድ ምሽት ላይ አንዲት ኩነት እንደተፈጠረች እንዲህ ሲል አጫወተኝ። ግዜው አለ አልጎርደን ብራውን የተባለ የቀድሞው የብሌየር ዘመን ቻልስለር የበጀት ሪፖርት የሚሰጥበት ቀን ነበር። በበጀት ሪፖርቱ ዙሪያ ለቻንስለሩ ከቀረቡለት ጥያቄዎች አንዱ የሲጋራን ታክስ የሚመለከት ሲሆን ጋዜኛው እንዲህ ሲል ጠየቀ፣

“ሚር ቻንስለር እርስዎ ወደ ዳውኒንግ ስትሪት ከመጡ ግዜ ጀምሮ የሲጋራ ዋጋ በመቶዎች ፐርሰንት እጥፍ እያደገ ነው፣ ለዚህ ምላሽዎ ምን ይሆን?” የሚል ነበር።
ቻንስለር ብራውን፤ “አየህ እኛ በሁለት መቶ ያህል አገሮች ለምናካሂደው የውጭ ፖሊሲ (በየሃገሩ ያሉትን ኤምባሲዎቻችንን እና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶቻችንን ) እንዲሁም ሌሎች የሁለት አንስተኛ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት በጀት ሙሉ ለሙሉ የሚሸፈነው ከሲጋራ በሚገኝ ታክስ ነው በመሆኑ አማራጭ የለንም” ብሎ ቁጭ አለ።

ጋዜጠኛውም በማስከተል ገና ለገና “ሰው ሲጋራ ያጨሳል ብላችሁ ይህን ያህል በመቶ ቢሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር በጀት ስትይዙ ሰው ሁሉ ተነጋግሮ ሲጋራውን ማጨስ ቢያቆም ምን ሊውጣችሁ ነው?” ሲል ይጠይቃል፤ ነገር ግን ቻንስለሩ መልሳቸው አጭር ነበር። “አያቆምም!!!” የሚል፤ “ለዚህም” አሉ ቻንስለሩ፣ “ለዚህም በደንብ ወጥነት ያለው (ፓተርንድ) የሆነ መረጃ አለን። ማጨስ የጀመረ ሰው ማለት በራሱ ላይ ስልጣን የሌለው እስቱፒድ ነው ..” የሚል ነበር። ይኽን በቀጥታ ለእግሊዝ ህዝብ ሲተላለፍ የነበረ ቃለ ምልልስ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ሲከታተል የነበረው አንዳርጋቸው የመጨረሻውን መልስ ሲሰማ ፈገግ ነበር ያለው። እጁንም ወደ ደረት ኪሱ ሰደድ ሲያደርግ አስር ያህል ሲጋራ የያዘ አንድ የሲጋራ ፓኮ ነበረው፤ አውጥቶም ቅርጥፍጥፍ አደረገና ከፊት ለፊቱ ባለው የብርጭቆ ውሃ ውስጥ ነከረው። “በእርግጥም..!!!” አለ አንዳርጋቸው “ከእንግዲህ የኽን ቃለምልልስ ሰምቸ የሲጋራን ዘር ዳግም ወደ አፌ ብመልሰው አንተ እንዳልከው በእርግጥም እስቱፒድ መሆኔን በእራሴው ግዜ አረጋገጫለሁ ማለት ነው” አለ። ነገሩ ወዲህ ነው፤ የሚገርመው ነገር ከዚያች ቀን ጀምሮ የአንዳርጋቸው ጽጌ ሲጋራ ማቆም መቻሉ ብቻ አልነበረም። እርሱ ሲጋራውን ሲያቆም ማዛጋት፣ ማፋሸግ እራስ ምታትም ሆነ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት ሳያስፈልገው እንደማንኛውም ሱስ እንደሌለበት ሰው እንዲሁ ጽድት ባለ መንፈስ ከብሩህ ፈገግታ ጋር ነበር ከእቅልፉ የነቃው። በዚህም አንድ ሰው ከውስጡ ሲወስን ምን ያህል አቅም መፍጠር እንዲሚቻለው ቀላሉ ማሳያ ሆኖ አልፏል።

እንዲህ ያሉት በመርህ የመጽናት ባህሪዎቹ ለአንዳርጋቸው በጸጥታ ውስጥ በኖረባቸው የጽሞና ግዜያት ያዳበራቸው የሞራል መሰረቶቹ ናቸው። በዚህ የተነሳ ማንም ሰው አንዳርጋቸውን ቀርቦ ለማወቅ እድል ቢገጥመው እርሱ ማለት ከራሱ ጋር የታረቀ፣ ፍጹም ሰላማዊ፣ እንደ ሱናሜ በሚገነፍል ማእበል ላይ ተረጋግቶ መራመድ የማይሳነው፣ የማይሞቀው የማይበርደው፤ በአለም ሳለ እራሱን የካደ ትሁት ሰው ነው።

ዛሬ አንዳርጋቸው ጽጌ በፍልስፍና ውስጥ ያዳበረውን ወደ ውስጥ የማየት ክህሎት በሌላ ገጽታው በመመርመር ያሳልፋል። ወያኔዎች ባዘጋጁለት ከመሬት በታች በተሰራች በጣም ጠባብና አየር አለባ መስኮት አልባ ክፍል ውስጥ የብሉያትን እና የሃዲስ ኪዳንን እንዲሁም የነገረ መለኮትን ትርጉዋሜዎች አዳርሷል። ሰባቱን አጽዋማት ሲጾም በቀን አንድ ግዜ ምግብ ይቀምሳል።የያኔው የማርክሲስት ባህታዊ ፍልስፍና እና ነገረ መለኮት ሳይጣረሱ የት ላይ እንደሚገናኙ ዛሬ በስልሳዎቹ መጀመሪያ እድሜው ላይ ነጥቡን አግኝቶታል።ይዅውም በፍልስፍና ፒውር ሰብጀክቲቪቲ የሚባለው በመጸሃፍ ከንጻሃ ስጋ ወደ ንጻሃ ነፍስ፤ ከንጻሃ ነፍስ ወደ ንጻሃ ልቡናና፤ ነጽሮ ስላሴና አይምሮ መንፈሳዊ እያሉ ባለቤቱ ክርስቶስን እስኪያክሉት በመንፈስ ማደግ ነው። ዛሬ አንዳርጋቸው በዚያ ጎዳና ላይ ነው። ማን ያውቃል፤ እንደ ጳውሎስ ቀናኢ ነገር ግን በራሱ መንገድ ይጏዝ የነበረ፤ በዚያው ልክ ከሰማይ በታች ለሰው ልጆች ሰላም የማይገደው ነገር የሌለና ለዚህም እርሱ በወቅቱ በገባው መስመር ፤ለራሴ ሳይል ከልጅነት እስከእውቀት እራሱን አሳልፎ የሰጠለት ይኽ የእንጨት ለቃሚ ልጆች ጎስቋላ ህይወትን የመታደግ ትግል፤ እንዲሁም የደም ንኪኪው ካለባቸው የሰቃሊያነ ክርስቶስ ተረፈ አይሁድ እጅ ከወደቀበት ቀን ጀምሮ በእያንዳንዷ ደቂቃ የከፈለውን ስቃይ ከጾም ከጸሎት ከንሳሃ ቆጥሮለት እርሱ ብቻ ባወቀው የገለጠለት ወይንም የተገለጠለት ነገር አለመኖሩን ማን ያውቃል?፣ ቅዱስ አውግስጢኖስ “ቤተከርስቲያናችን በቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ቅዱስ ጳውሎስን ያህል ሃዋርያ አገኘች” ሲል ቅዱስ ጳውሎስን ኋላ ለደረሰበት የብቃት ደረጃ የጠራችው ቀዳሜ ሰማእት ቅዱስ እስጢፋኖስ በዲንጋይ ሲወገር በጸአት ነፍሱ ግዜ “ጌታ ሆይ ይቅር በላቸው ብሎ የጸለያት ጸሎት ነበረች” ማለቱ ነበር። የመድሃኒዓለም ስራው ሰዎች ለክፋት የሚያደርጉትን ክፉ ስራ ሁሉ ወደ በጎ መለወጥ ነው፣ ውሃውን ወደ ወይነጠጅ እንደለወጠው፤ አንዳርጋቸው ጽጌ ወስመ ጥምቀቱ ዘእየሱስ ዛሬ በመንፈስ ከፍታ ላይ ሆኖ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ጥቃቅኖቹን ጭንጋፎች በማይክሮስኮፕ ያያቸዋል።

Filed in: Amharic