>

ግራ ገባን እኮ (አፈንዲ ሙተቂ)

ማዕከላዊ መንግሥቱ ለተቃውሞ ብተና ፈጥኖ ደራሽ የፖሊስ ኃይል መላኩን ትቶ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የመከላከያ ሰራዊት ይልካል።

የመከላከያ ሰራዊት ተብዬው ደግሞ ወደ ጠላት ሀገር የተላከ ይመስል የራሱን ህዝብ በጥይት ይጨፈጭፋል።

በመንግስት አካላት ዘንድ ያልታጠቀ ሰልፈኛን በጭስና በውሃ መበተን አልለመድ ብሏል።

አክቲቪስት ተብዬው ሶስት አይነት መረጃ እያሰራጨ ወጣቱን ውዥንብር ውስጥ ይከተዋል። ወጣቱ ለተቃውሞ ሲወጣ ደግሞ በሁለት ቡድን ይከፈልና አንደኛው ቡድን ከአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ ጋር ወግኖ ሰልፍ እንዳይደረግ ይለማምናል። ሌላኛው ቡድን “ትግሉ ተፋፍሞ መቀጠል አለበት” እያለ ሶሻል ሚዲያውን በትኩሳት ይንጠዋል። ሁሉም እንዳልነበረ ሆኖ ሲጠናቀቅ ግን ለሟች ሙሾ እያወረደ የአቶ ለማ ካቢኔንም ሆነ ገዳዮቹን ያወግዛል። “ኦፒዲኦ ድሮውንስ ተላላኪ” ወደሚለው የቀድሞ ሙዚቃው ይመለሳል።
—–
በዚህ መሀል ህዝብ አለቀ! በተለይም የደሀው ልጅ ተጨፈጨፈ።
—–
መከላከያ ነኝ ብሎ ሰው መጨፍጨፍም ሆነ አክቲቪስት ነኝ እያሉ ህዝብን ማስጨረስ መወገዝ አለባቸው። ኦፒዲኦም ራሱን ሳያጠናክር በጥቂት ወራት ውስጥ ያከማቸውን ትንሽዬ ጡንቻ እያሳየ ወጣቶች በርሱ ተማምነው ከመከላከያው ጋር ግብግብ እንዲገጥሙ ሰበብ መሆን የለበትም።
—–
በድጋሚ ፈጣሪ የወጣቶቻችንን ነፍስ ይማርልን።

Filed in: Amharic