>

"አዲስ አበቤ ለምን አልተነሳም?" "ሰፋሪ!" "መጤ!"፣"ቤት አልባ!"፣"የደም ከተማ!" (ኤርሚያስ ለገሰ)

 አሁን አሁን በድፍረት መጠየቅ ያለብን ቁልፍ ጥያቄዎች ከፊታችን እየተጋረጡ ነው። የአገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበናል የምንል ሁሉ ምላሽ ያላገኘንለትን ጥያቄ ማንሳት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ደርሰናል። የኦሮጌ ስርአት ፍፃሜ እና የአዲስ ስርአት መባቻ ላይ እንደመገኘታችን መጠን ምላሽ ባላገኙ ጥያቄዎች መወጠሩ ነባራዊ ነው። ይገባልም።

እናም ለዛሬ ውሎዬ የማሰላስላቸው አምስት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛ:- ” አዲሳአባ ዙሪያ በህዝባዊ እምቢተኝነት ማእበል ተጨናንቆ ለምን አዲስአበቤ ግልፅ አመፅ አልጀመረም??” እደግመዋለሁ ” አዲስአበቤ ለምን አልተነሳም?” ” ሰፋሪ!” ” መጤ!”፣ ” ቤት አልባ!” ፣ ” የደም ከተማ!” ፣ ” ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ!” ፣ ” ኢትዮጵያ ትበተን!” ፣ ” ሰልፍ ዴተርሚኔሽን!” የሚሉት የበታችነት ስሜት የወለዳቸው መፈክሮች ተፅእኖ አሳድረው ይሆን? በቁጭት እና ንዴት ውስጥ ያለው አዲስአበቤ የሚጠየፈውንና ለአንድም ቀን በሕይወት እንዲቆይ የማይፈልገውን አገዛዝ ለመገርሰስ ለምን ሆ! ብሎ አልተነሳም? መጪው ጊዜ ያስፈራው ይሆን?

ሁለተኛ: – የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለምን በፈረቃ ይካሄዳል? አንደኛው ጋር ሲግል ሌላኛው ጋር ይሞቃል። አንደኛው ጋር ሲሞቅ ሌላኛው ጋር ይቀዘቅዛል። ለምን አብረው መሞቅ ተሳናቸው? ለምን አብረው መጋል አልቻሉም? በጋራ ተባብሮ ለመነሳት ያስቸገረው ነገር ምንድነው?

ሶስተኛ: ለምን ከሱማሌ የተፈናቀሉ ከ600 መቶ ሺህ ያላነሱ ኦሮሞዎችን ወደ እትብታቸው ወደ ተቀበረበት አሊያም ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ወደ ኖሩበት ቀዬ መመለስ አልተቻለም? ህዝቡ ወደ መንደሩ ለመመለስ ያለውን ጉጉት በአደባባይ ገልጾ ሲያበቃ እርምጃ መውሰድ የተሳነው ማነው? የአብዲ ኢሌ ካቢኔ( የሕውሓት ጦር ጄኔራሎች) እና ጫፍ የረገጡ የኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኞች (DNA ፓለቲከኞች) ህዝቡ ወደ መንደሩ እንዲመለስ ይፈልጋሉ ወይ? የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊው እንደነገሩን ከማረጋጋቱ ቀጥሎ የቅድሚያ ስራው ነዋሪውን ወደ ቦታው መመለስ ነበር (“የግል አስተያየት” ካልተባለ በስተቀር!)… እናም ለምን የዶክተር ነገሬ ሌንጮ ቃል ወደ ተግባር መቀየር አልተቻለም? ነገሬ ሌንጮ ከዚህ በላይ ከመዋረዱ በፊት ለምን የውሸት የሥልጣን ቦታውን አይለቅም?

አራተኛ:- አባዱላ የህዝቤ ክብር ተነክቷል ያለበትን ዲስኩር ፈታ ፈታ አድርጐ የሚያብራራው መቼ ነው? የአባዱላ ” ሕዝብ!” ማነው? ክብሩ የተነካው ከመቼ ጀምሮ ነው? ክብሩን የነካው ማነው? አባዱላ ክብር ነኪውን ምን ሊያደርገው አስቧል?

አምስተኛ:- ድሬደዋ ላይ ያንዣበበው አደጋ ለመፈንዳት በተቃረበበት ሁኔታ ለምን ልዪ ትኩረት ተነፈገው? የአሁኑ ዙር ተረኛ ገዥ የሆነው የሶማሌ (የአብዲ ኢሌ ፓርቲ) ለቀጣዩ የለማ መገርሳ ድርጅት ( ኦህዴድ) ያስረክባል ወይ? ወይንስ አሁንም ህውሓት በገለልተኝነት ሂሳብ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ተመልሶ መጥቶ ያስተዳድራል? በአጭሩ ” ድሬዳዋ የማን ናት?

Filed in: Amharic