>

የሊፎርት አራቱ ቢሆኖች… (በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

(ከዚህ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ምን ይከሰት ይሆን?)

መጀመሪያ ሕዝባዊ አመፅ። ቀጥሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ። አሁን ደግሞ ውስጣዊ የገዢዎች መነጣጠል (ወይም የሚመስል ነገር)። ቀጥሎ ወዴት እየሔድን ነው?

የሰሞኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት ላይ ሁነኛ ትንታኔ እስካሁን አልተደመጠም የሚል ቅሬታ አለ። ተቃዋሚዎች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች የሚያደርጉት ሽኩቻ ላይ አስተያየት መስጠትን አንድም ለነርሱ ሴራ እንደመታለል፣ አሊያም በደለኝነታቸውን እንደ መዘንጋት ይታይብኛል በማለት ዝም ጭጭ ብለዋል። በዚህ መሐል የኢትዮጵያን ፖለቲካ አብጠርጥረው የሚያውቁት የአካባቢው ፖለቲካ ተንታኝ ሪኔ ሊፎርት – ኦፕን ዴሞክራሲ ላይ በጻፉት ጽሑፍ – የፖለቲካ ሒደቶችን ከዘረዘሩ በኋላ፣ አራት ይሄ ቢሆን፣ ይሄ ይሆናሎችን ዘርዝረዋል። እዚህ በአጭሩ አቅርቤዋለሁ፦

ሊፎርት በቅድሚያ ብአዴን ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ‘ብአዴን ከማን ጋር ኃይሉን ያጣምር ይሆን?’ በማለት። በቅድሚያ ኢሕአዴግን በሦስት ይከፍሉታል፦ ብአዴን፣ ኦሕዴድ እና የዳር አገር “ኅብረት” (ሕወሓትና ደቡብን የሚጨምር) በማለት። በታሪክ አማራና ትግራይ ተቀናቃኝ ቢሆኑም ኦሮሞ መጣባችሁ ሲባሉ ግን ፀባቸውን ያቆሙ ነበር ይላሉ። “ይህን ትቶ ታዲያ ብአዴን ከኦሕዴድ ጋር ይተባበራል?”

አራቱ ቢሆኖች

፩ኛ፦ የሊፎርት አራት ቢሆኖች ውስጥ የመጀመሪያው ኢሕአዴግ በመጪው መጋቢት ወር የሚያካሒደውን ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቅ ከቻለ ነው የሚሳካው። ጉባኤውን ተስማምተው ከጨረሱት፣ በጣም አክራሪ ተቃዋሚያቸውን እና የዘውግ መሪዎችን ማሰለፍ ከቻሉ እንዲሁም ከራሚውን “የብሔረሰቦች ጥያቄ” ዐብይ ትኩረታቸው ማድረግ ከቻሉ ነው ብለዋል። ይህ የሚሆነው ግን ብአዴን እና ኦሕዴድ ኃይላቸውን አጣምረው ከደቡብ እና ትግራይ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት መካከል አጋር ማግኘት ሲችሉ ነው።

፪ኛ፦ “አንደኛው ካልተሳካ ሁለተኛው የዩጎዝላቪያን ዕጣ መከተል ነው” ይላሉ ሊፎርት ሁለተኛውን ቢሆን ሲያስቀምጡ። መፈራረስ ማለታቸው ነው።

፫ኛ፦ ሌላም ሦስተኛ የቢሆን ዕድል ግን አለ ይላሉ ሊፎርት። ይህም የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጥ አንፃራዊ የኃይል መመጣጠን ከተከተለ እና ባሉበት ከረጉ፣ ተቃዋሚዎች ገንነው ሊወጡ ይችላሉ። ዘውግ ዘለሎቹ ድርጅቶች አሊያም በዘውግ ከተደራጁት “መሻሻል” ፈላጊዎች፣ ወይም “ሥር ነቀል” ለውጥ ፈላጊዎቹ ተጠናክረው ሊነሱ ይችላሉ። እንዲህ ከሆነ አገሪቱ ባለችበት ተቀጥላለች። ዋናዎቹ ችግሮች ግን ባይባባሱ እንኳ ባሉበት ይቀጥላሉ።

፬ኛ፦ ይሄ ሁሉ ወታደሩ ክንፍ መፈንቅለ መንግሥት ካልሞከረ ነው። እንደ ሊፎርት፣ ወታደራዊ ክንፉ በመፈንቅለ መንግሥት የፌዴራል ስርዓቱን መልሼ ላዋቅር ካለ የዩጎዝላቪያ ዕጣ እዚህም ይመጣል። ‘ግን ደግሞ መፈንቅለ መንግሥቱ ቢመጣስ በአንዱ ክንፍ ነው ወይስ በጠቅላላው መከላከያ ፍላጎት?’ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።

እናንተስ የትኛው የሚከሰት ይመስላችኋል? የተለየ ቢሆንስ የምንለው ይኖር ይሆን?

Filed in: Amharic