>

የአክሱም ጫፍ አቁማዳ (ደበበ ሰይፉ)

ትግራይ ላከ ወሎ ጋ አበድሮኝ ብሎ አንድ ቁና ጤፍ
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን ባህሉን መዝለፍ
ቆሌውን መንቀፍ
ላከ ወደሸዋ ምናልባት ቢሰጠው ለሰው እሚተርፍ።
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን ወደ ሐረር ዞረ
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ
ባሌም ወደአርሲ አርሲ ሲዳሞን
ሲዳሞም ተክዞ፣ ግን የለኝም ብልስ ማን ያምነኛል ብሎ
ወደ ጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅሎ።
ጋሞን ብርድ መታው ሐዘን ገባውና
የራሱን ምንዳቤ የግል ስቅየቱን ችሎት በጥሞና
በጋቢ ጀቡኖ የልቡን ጠባሳ ሲኖር እንደ ደህና
ዛሬ የወንድሙን የእርዳኝ አቤቱታ መስማት አልቻለና።
አውጥቶና አውርዶ ላከ ወደ ከፋ እጅግ አስተዛዝኖ
ከሀፍረት ያድነኛል ከረሃብ ያወጣኛል ሲል በአያሌው አምኖ።
ከፋ እንደደረሰው በድንገት አቁማዳው በነብሱ ዋይታ
ሐራራው ተሰማው የሥጋው ድንፋታ
ብልሀት አዛጋ ቆይቶ ቆይቶ የተስፋ ጠል ቀዳ
ሊልክ ከኢሉባቦር አበድረኝ ብሎ እህል በአቁማዳ።
ጭምት ኢሉባቦር ይኖር የነበረ የቤቱን ጉድ ጓዳ በሞኛሞኝ
ገላው ቆዳው ውስጥ ወሽቆ
ጠየቀ ወለጋን ሐፍረቱን ደብቆ ኩራቱን ዘቅዝቆ
ኬት አመጣ ብሎ ወደኔ ላከብኝ እያለ ወለጋ እጅጉን ተደሞ
ሄደ ወደ ጎጃም ዛሬን ሁነኝ ብሎ ሊማፀነው ቆሞ።
ጎጃምም ተሰምቶት ሰቀቀን ሐዘኑ ደረት እየመታ፣ ቅኔ እያወረደ፣
እንባ እያፈሰሰ
ወግና ኩራቱን በየቦዳው መሀል እየነሰነሰ
ዐባይን ተሻግሮ ከጎንደር ደረሰ።
ፋሲል ላይ ተነጥፎ ጎንደርም ሐዘን ላይ ነበረ ተቀምጦ
ተድላ ልጁ ሞቶ ገናን ክንዱ ታጥፎ በዘመን ተድጦ
ጎጃም መጣ ሲሉት የእዝን የተመኘን ልቡን በታዘበ
የኩራት ካባውን ሊጥል ባንጓበበ
የወንድሙ መምጣት እቅጩ መንስዔ መሆኑን
ሲረዳ ረሀብ አበሳ
ጥንትም አልሆነኝም ከእንግዲህ ይበቃኛል ለይሉኝታ አልሳሳ
ብሎ ከኤርትራ እህል ለመበደር በርትቶ ተነሳ።
የዘመዱ እጦት ነበርና እጦቱ በዝቶ ሰቀቀኑ
ኤርትራ ታመመ ደም ጎረፈ ከዓይኑ፡፡
ወደ ትግራይ ላከ መላ ባገኝ ብሎ ከአደራ ደብዳቤ
(እባክህ ላክልኝ አንድ አቁማዳ እህል ልሞት ነው ተርቤ።)
ትግራይ አስተውሎ አቁማዳው የራሱ መሆኑን ለይቶ
ረሀብ ዕጣቸው የሁል ወንድሞቹ መሆኑን አካቶ
ሐዘኑ አነቀው፤ ትንፋሹ መረረው፣ ትካዝ ሆዱ
ገብቶ።
“እኔና ወንድሞቼ” አለ በለዘብታ
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፤
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን . . . ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን።
ለኋላ ትውልዶች ተረት እንዳይመስል ይህ ብካይ
እሮሮ
ይህ ጠፍ ስብእና ይህ ስቁይ አእምሮ
እንዳኖረው ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለ ስፍራ
መጥቆ እንደባንዲራ
ምንም ባዶ ቢሆን በውስጡ አይጠፋና የታሪክ
አዝመራ።”
ይህንን ተናግሮ ከአክሱም ሐውልት ዘንድ
ትግራይ ተጠግቶ
አንዴ እየፀለየ አንዴ እየዘመረ ያለመጠን ተግቶ
ጫፉ ላይ ሰቀለው ያን አቁማዳ አውጥቶ።

° ደበበ ሰይፉ  1967 (ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ/ የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2) መጽሐፍ 1992ዓ.ም የታተመ ።

Filed in: Amharic