>
5:14 pm - Thursday April 20, 0902

". . . ከእለታት ባንዱ ለት፣ ደም በደመነበት በነውጠኛው ጊዜ . . ."(በውቀቱ ስዩም )

ከእለታት ባንዱ ለት፣ ደም በደመነበት
በነውጠኛው ጊዜ
የጎጃሙ መስፍን ራስ አዳልና፣ የላስታው ጎበዜ
ገብር . . . አልገብርም ይዋጣልን ብለው
ለመግደል ለመስለብ እጅግ የቋመጠ ሰራዊት መልምለው
ጠመንጃ ወልውለው፣ ሰይፋቸውን ስለው
ጨሬውን አሹለው ዛቻ ተለዋውጠው፣
ለመተናነቂያ የማይቀር ቀን ቆርጠው
ለፍልሚያ፣ ለግልቢያ የተመቸ ስፍራ ድልድል ሜዳ መርጠው
በተፋጠጡበት በውጊያ ዋዜማ
አንድ ብልጥ ደብተራ ዜናውን የሰማ
እንደባህታዊ ወይባ ዳባ ለብሶ
የላስታው ጎበዜ ወደሰፈረበት ጋለበና ደርሶ
የርሶ ሰራዊት
በአዳል ጭፍራዎች ላይ እንደሚበረታ
በህልሜ አሳይቶኛል የአባቶችዎ አምላክ ትናንትና ማታ
ብሎ ተናገረ . . . ተናግሮም አልቀረ
ወደዚያኛው ጎራ ገስግሶ ሄደና
ጌታው ራስ አዳል ድል አድራጊው ጀግና
ህልሜ ወለል አርጎ እንደገለጠልኝ፣
የነገው ድል ነሺ እርስዎ ነዎትና
እኔን ነቢይ አርጎ ለላከልዎ አምላክ ያቅርቡ ምስጋና
ይህንን የሰማ ጓደኛው ቢደንቀው
እንዲህ ሲል ጠየቀው
ነገር እንደማብረድ፣ ሰላም እንደማውረድ፣ እንደመገላገል
ምን ይሉት ፈሊጥ ነው፣ እሳትና ጭድን በተራ መሸንገል?
በቃልህ ተማምኖ ታግሎ የተረታ
የት ትገባ ይሆን እንደዘበትህበት የባነነ ለታ?
ይህንን ወቀሳ አድምጦ ደብተራው
ቃሉን አሰማምሮ መለሰ በተራው
በወትሮ ልማዱ፣ ሰው መተራረዱ ፈጽሞ ባይቀርም
አንዱ ተሸንፎ ፣ አንዱ እንደሚያሸንፍ አያጠራጥርም
ያሸነፈው መስፍን በትንቢቴ ታምኖ ደስ ብሎት ሲሾመኝ
የተሸነፈው ግን ያልሁትን አስቦ እኔን መቅጣት ቢመኝ
ከምኞት ባለፈ ከቶ ምን ያመጣል
የተሸነፈ ሰው ስልጣኑን ያጣ ቀን ሁሉን ነገር ያጣል
በዚች ዕውር ምድር መሸነፍ ነው ወንጀል
ይህንን አውቃለሁ
የተረታ ድኩም ራሱን ሊያጽናና፣ እውነት ያሸንፋል ሲለኝ እስቃለሁ
ይልቅ አሸናፊው እውነትን ያበጃል፣
ባምሳሉ ጠፍጥፎ ሲሻው ያወርሳታል
ለቀጣዩ ትውልድ፣ በጽላት ላይ ጥፎ
ምድር ገበያ ናት፣
አንዱ ያንዱ ሸቀጥ፣ አንዱ ያንዱ አሞሌ
ሐቅም የላት አቅም፣ ሆና ትኖራለች የአሸናፊው ሎሌ
የአዳም ልጆች ልብም ፤
ጠንሳሽ የሚጠብቅ የጠብ ድፍድፍ በርሜል
ግልብ ሰው ብቻ ነው፣ ሰላምን በስብከት አሰፍናለሁ የሚል
አጉል ከምትለፋ በዚች የጠብ አለም ጠብን ልታስወግድ
ቂሎች ሲፋለሙ በደማቸው አትርፍ ፣ ባጥንታቸው ነግድ ።

Filed in: Amharic