>

በማያውቁት የምርጫ ሥርዓት ላይ መደራደር፤ (ውብሸት ሙላት)

በማያውቁት የምርጫ ሥርዓት ላይ መደራደር፤
ቅይጥ-ትይዩ፤ምን ከምን ይቀየጣል? እንዴት ይቀየጣል?

ኢሕአዴግ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ከጀመረ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ከሚደራደሩባቸው አጀንዳዎች አንዱ የምርጫ ሥርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱ ሲሻሻል ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል፡፡ ከየሚዲያዎቹ እንደሰማነው ሌሎቹ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ ውክልና የሚባለውን፣ኢሕአዴግ ደግሞ ቅይጥ-ትይዩ (Mixed-Parallel ) የምርጫ ሥርዓትን በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡

ኢሕአዴግ ይህንን የምርጫ ሥርዓት ለድርድር ሲያቀርብ ሌሎቹ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ኢሕአዴግ የዚህን የምርጫ ሥርዓት ባሕርይ፣ ጥቅምና ጉዳት አስቀድሞ እንዲያስረዳቸው ጠይቀዋል፡፡ ያስረዳቸው ወይም አያስረዳቸው ባይታወቅም ኢሕአዴግ ከ550 መቀመጫዎች 50 መቀመጫዎችን ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ቀሪ 500 ያህሉን ደግሞ አሁን ሥራ ላይ ያለውን የአንደኛ አላፊ (First-past-the-post) የምርጫ ሥርዓት እንዳለ ለመጠቀም የ10- 90 በመቶ ምጣኔ አቀረበ፡፡ አስራ አንድ ፓርቲዎች ደግሞ 50-50 በመቶ አቀረቡ፡፡ ከድርድር በኋላ ደግሞ እንደሚከተለው መቅረቡን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዜናነት አስተላልፏል፡፡

“85% አንደኛ አላፊ፤15% ተመጣጣኝ ውክልና”-ኢሕአዴግ፤

“75% አንደኛ አላፊ፤25% ተመጣጣኝ ውክልና”-መኢብን፤

“60% አንደኛ አላፊ፤40%ተመጣጣኝ ውክልና”-11 ፓርቲዎች፤

“100% አንደኛ አላፊ ወይም 100% ተመጣጣኝ ውክልና”-ኢራፓ፤

አንድ በትክክል ስሙን ያልሰማሁት ፓርቲ ደግሞ የኢሕአዴግን አቋም ደግፏል፡፡

ኢሕአዴግ ዋናው ነገር ሥርዓቱን ማሻሻሉ እንጂ ምን ያሕል አሁን እንዳለው ቀሪው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና የመደረጉ ጉዳይ እንዳልሆነ በምክንያትነት አቅረቧል፤ይልቁንም ልምድ እየተወሰደበት ወደፊት እንደሚሻሻል ተናግሯል፡፡ አስራ አንዱ ፓርቲዎች ደግሞ እንደ ኢሕአዴግ በቁጥቁጥ ሳይሆኑ ቀድሞ ከነበራቸው የ50-50 በመቶ አቋም 10 በመቶ በመቀነስ 40 በመቶን ለድረድር አቅርበዋል፡፡

እንግዲህ እነዚህ ፓርቲዎች ለድርድር የቀረበውን ጉዳይ (የምርጫ ሥርዓት) ሳያዉቁት ተደራደሩ፡፡ የሚደራደሩበት ጉዳይ ጥቅምና ጉዳቱን በሌላው ወገን ያለው ተደራዳሪ (ኢሕአዴግ) አስረዳቸው፡፡ እናም፣ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነው፣የኢትዮጵያ ሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተደራደሩ ነው፡፡ ምን ከምን እንደሚቀየጥ ሳያውቁ፣በትይዩ የሚከናወነው ምን እንደሆነ ሳይረዱ ተደራደሩ፡፡

አዲዮስ የፖለቲካ ፓርቲ!

ለነገሩ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባል በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ ችግር የለውም፡፡

Filed in: Amharic