>

ምን እየተካሄደ ነው? (ዮናስ ሃጎስ)

በአሁኑ ሰዓት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት ወይ የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅ አሊያም ባለሙያ ተንታኝ መሆን አይጠበቅብህም። በቃ ባለፉት 26 ዓመታት እስካሁን የመጣንበት ጎዳና መለስ ብለህ ካየህ በበቂ ሁኔታ ስላሁኑና ስለመጪው ክስተት መናገር ትችላለህ።
***
የመጣንበት ጎዳና ምን ይመስላል? እስቲ እንየው?
***
1) አባዱላ የኢሃዴግ ተወርዋሪ ኮከብ ነው። ድርጅቱን ካንድም ሶስቴ ከቅሌት አድኖታል። አሁን ለኢሃዴግ ራስ ምታት እየሆነ የመጣውን የነለማ አስተዳደርን ሰብሮ ኢሃዴግን መታደግ የሚችል ብቸኛው ሰውም እሱ ነው።
2) ሕወሐት አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ብቸኛው ማምለጫ ዘዴዋ ክራይስስ መፍጠር ነው። ይህ የብዙ አምባገነን መሪዎች መለያ ቢሆንም የሕወሐትን ለየት የሚያደርገው በምትፈጥረው ክራይስስ እንዴት ፖለቲካዊ ትርፍ እንደምታገኝ አስቀድማ ስለምታሰላስል ሁለት ጥቅም ነው የምታገኘው። አንደኛው ሰዉ በክራይስሱ ምክንያት አጀንዳውን ዞር አድርጎ ትንፋሽ ይሰጣታል። ሁለተኛ በምትፈጥረው ክራይስስ የብዙ ሐይሎችን መስመር ታስታለች።
3) ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 26 ዓመታት አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎችን በሙሉ አበጥረን ካየናቸው የሚያመሳስላቸው አንድ ብቸኛ ነገር አለ። ይኸውም ለነዚህ ግድያዎች ኃላፊነቱን እንዲወስድ ተደርጎ ፍርድ ቤት የቀረበ አንድም ሰው አለመኖሩ ነው። ይህ ግድያዎቹ ከፍተኛ በሆነው የምንግስት አካል እንደሚቀነባበሩና ድርጊቱን ፈፃሚዎቹም ጥበቃና ከለላ እንደሚደረግላቸው የሚያሳይ ነው። 2ኛ ቁጥር ላይ ስለ ሕወሐት የፃፍኩትን ካስተዋልን በዚህ ተራ ቁ 3 ላይ ‹ከፍተኛው አካል› ተብሎ የተጠቀሰው ማን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
4) የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ አንድ እርምጃ ወደፊት እየተራመደ ሁለት እርምጃ ወደኋላ የሚሄደው ለምንድን ነው? መልሱ ቀላል ነው። ተቃዋሚው ሕወሐትን ለማጥፋት የሚጠቀምበት ዘዴ እሾህን በእሾህ የሚባለው ዘዴ ስለሆነ ነው። ተቃዋሚው ይህንን መንግስት ከሚቃወምበት ጉዳዮሽ ዋንኛው የዘር ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ 90 በመቶ የሚሆነው ተቃዋሚ የተደራጀው በዘር ነው። ተቃዋሚው በዘር መደራጀቱ ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ከሕወሐት ውጭ ያሉ ‹ተላላኪ› ተብለው የሚታሰቡ ድርጅቶች ያን ያህል የተቃውሞ በትር እንዳያርፍባቸው ምክንያት ሆኗል። አንዳንድ ተቃዋሚዎችማ እነርሱን እንደ አጋር በመያዝ ኢሃዴግን መጣል ይቻላል ብለው ያምናሉ…
***
ከነዚህ እውነታዎች በመነሳት በአሁኑ ሰዓት ኦሮምያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ነገር በዚህ መልኩ ማስቀመጥ ይቻላል።
***
የነለማ አስተዳደር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። በእርግጥ እነሙክታርን ሲተኩ የተፈለገውም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ለሁለት ዓመታት ያህል ሲካሄድ የነበረውን ዓመፅ እንዲያበርዱ ነበር። አሁን ድምፁ የሌለውና ለአንድ ሰሞን ግን የጆሮ ታምቡራችንን ሊበጥሰው የነበረው ‹የኦሮሚያ ኢኮኖሚክ ሪቮልዩሽን› የዚህ እቅድ አንዱ ዓላማ ነበረ። (በነገራችን ላይ የአማራም ኢኮኖሚክ ሪቮልዩሽን› ታስቦ በቀናት ውስጥ ወሬው ሁሉ ደብዛው የጠፋው እንደ ኦሮሚያው ለሆነ ዓላማ ታቅዶ ሳይሆን በብዓዴን ‹እኔስ ለምን ይቅርብኝ› ፍላጎት ስለሆነ ነው።
የተፈለገው ውጤት ቢገኝም ቅሉ እነ ለማ ግን በዛ ማቆም የፈለጉ አይመስልም። ስለዚህ ዓመፅ ለማብረድ ተብሎ የተጀመረውን ‹ማባበያ› እነርሱ የምር አድርገውት ቀጠሉበት። ይህ ደግሞ ዓመፅ አብርዱ ብሎ ለላካቸው አካል የሚዋጥ አልሆነም። ተዉ እባካችሁ ቀዝቅዙ ቢባሉም ቅሉ የሚቀዘቅዙ አልሆኑም። ስለዚህ ላኪው አካል እነርሱን የሚያዳክምበት ሌላ ዘዴ መቀየስ ነበረበት። የመጀመርያው ዘዴ ሁሌም ቢሆን ድርጅቱን ከውድቀት በማዳን በኩል ወደር የሌለውን አባዱላን ወደዚያው መላክ ነው። ነገር ግን አባዱላ የፓርላማው አፈ ጉባዔ ሆኖ ሳለ ከመሬት ተነስተው ወደ ኦሮሚያ ሊልኩት አይችሉም። በዛ መልኩ ቢሄድ አሁን ከለማ ጋር ፍቅር የያዘው ሕዝብ በፍፁም ሊቀበለው አይችልም። ያለው አማራጭ አባዱላም የነለማን ዘዴ መከተል ብቻ ነው። በዕቅዱ መሰረትም ድራማቲክ በሆነ መልኩ ከአፈ ጉባዔነቱ ለመነሳት መወሰኑን ተናገረ። ምክንያቱን በይደር ያቆየው ላኪው አካል የሕዝቡን ትርታ ለመለካት ስለፈለገ ነበረ። እቅዱ ከተፈለገው በላይ መሳካቱ የታወቀው በኦሮሚያ ተቃዋሚውም ሆነ ደጋፊው ባንድ ድምፅ አባዱላን ‹ጀግና› ብለው ማንቆሎጳጰስ በመጀመራቸው ነው። ከናንተ ከመጣ አይቀር… በሚል ሰውዬው ለሁለተኛ ጊዜ ኢንተርቪው ላይ ቀርበው «የድርጅቴ ክብር ተነክቷልና ከድርጅቴ ጋር ሆኜ እታገላለሁ…» አሉና አረፉት። በሌላ ቋንቋ «እየመጣሁ ነው!» ማለታቸው ነው።
ሆኖም አባዱላ ወደ ኦሮሚያና ኦህዴድ ከመመለሳቸው በፊት መሰራት የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህ ነገሮች ዋንኛው የነለማ ቡድንን በክራይስስ ማዋከብ ነው። በተለይ የኦሮሚያ ፖሊስ ሰልፈኛ መበተኑን አቁሞ ማጀብ መጀመሩና ከንቲባዎችና አስተዳደሮች ‹ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ትችላላችሁ!› ብለው ፈቃድ መስጠታቸው ቡድኑ ቶሎ መመታት እንዳለበት የሚያመላክት ነው። ቡድኑን ለመምታት ሕወሐት አሁንም የተጠቀመችው ዘዴ የራሳቸውን የነለማን ዘዴ መከተል ነው።
ለዚያም ነው ሰሞኑን ኦህዴድም ሆነ ሚኒሶታ የማያውቃቸው ሰልፎች የበዙት። እነዚህ ሰልፈኞች በጣም ነውጠኛ እና የሚጠይቁትን እንኳን በቅጡ አስተካክለው የማያውቁ ናቸው። ባንዴ የኦሮሚያን የትራንስፖርት ሁኔታ ቀጥ ሊያደርጒት ችለዋል። መኪኖች አቃጥለዋል። ንብረት አውድመዋል። ሕዝብ ለሕዝብ ሊያጋጭ በሚችል ሁኔታ ከደቡብ የመጡ ሰዎችን ባልተገባ ሁኔታ አጎሳቁለዋል። ዛሬ እንደምንሰማው ደግሞ በኢሊባቡር የትግራይና አማራ ተወላጆችን እየለዩ ገድለዋል።
***
ቀጣዩ ነገር ያው የታወቀ ነው። የነለማ ቡድን እየተንገዳገደ ነው። ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም የሚባል ነገር ጠፍቷል። አምራቾች ምርቶቻቸውን ለሌላው የኢትዮጵያ ክፍል መላክ ባለመቻላቸው ኢኮኖሚው እየተናጋ ነው። ከሌሎች ክልሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል መጓዝ አስቸጋሪ ሆኗል። በተለይ የአማራና የትግራይ ክልል መታወቅያ ይዞ መገኘት ራስን አደጋ ላይ መጣል መሆኑን በግልፅ እየታየ ነው። ባጠቃላይኦሮሚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ናት።
*
ምን ተሻለ ታድያ?
*
1) የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ለመግባት የሚችልበት ሁኔታዎች ተፈጠሩ ማለት ነው። ምናልባት አባዱላ የዚህ ችግር መሲህ ሆኖ ወደ ክልሉ በቅርቡ ማምራቱ አይቀርም። ላኪው አካል እሱ ወደዛ ሲደርስ የጀግና አቀባበል እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጨዋታ ተጫውቷል። እሱ እዛ ከደረሰ በኋላ ክልሉን ያረጋጋል። መሬት ለሚፈልገው መሬት ገንዘብ ለሚፈልገው ገንዘብ እየሰጠ ሁሉንም አፋቸውን ያዘጋል። ከዚያ ምንም እንዳልተፈጠረ ኦሮሚያ ኑሮዋን ትቀጥላለች።
2) ወይንም በመሐል እነለማ ክንዳቸውን እያፈረጠሙ ከሄዱና ሕዝቡን የበለጠ መቆጣጠር የሚችሉበት ደረጃ ላይ በሆነ ተዓምር ከደረሱ (አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ለማድረግ የሆነ ተዓምር ያስፈልጋቸዋል) እነሌንጮን በድርድር ሁለተኛው የኦሮሚያ ተቃዋሚ አድርገው ማስገባትና በሚቀጥለው ምርጫ (ያው እነለማ የፈለገ ቢወደዱ በምርጫ ሰዉ ኢሃዴግን ከመምረጥ ተቃዋሚን መምረጥ ስለሚቀለው) እነ ሌንጮ አሸንፈው ሁለተኛው የሕወሐት ፈረስ ሆነው ጉዞው ሊቀጥል ይችላል።
***
In the meantime… የነ ፕሮፌሰር መረራን እና አቶ በቀለ ገርባን ጉዳይ ብትረሱት ይሻላችኋል። አሁን ኦሮሚያ የሕወሐትና የኦሕዴድ የትግል ሜዳ ሆናለች። ስለዚህ ሁለቱን መሪዎች መፍታት ማለት አሁን ያለውን የኦሮሚያን የተወሳሰበ ችግር የበለጠ ማወሳሰብ ማለት ነውና በፍፁም አይታሰብም።
***
በኢሊባቡ በዘራቸው ምክንያት ነፍሳቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ፈጣሪ ምሕረቱን ያውርድላቸው! ተቃዋሚዎችንም ወያኔን ከሚቃወሙበት የዘር ልክፍተኝነት ራሳቸውን ያርቁ ዘንድ ልቦናቸውን ያብራልን!!

Filed in: Amharic