>

የሚበጀው (ሃብታሙ አያሌው)

በርግጥ ለአቡነ ማትያስ የሚበጀው ስልጣን እለቃለሁ በማለት አባዱላ እና በረከትን መምሰል ወይም ማህበረ ቅዱሳንን ማፍረስ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ራስ እርሱ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያንን እና ምዕመኗን በሰላም በፀጋና በመንፈስ እንዲጠብቅ ቤቱን ለባለቤቱ ማስረከብ ይመስለኛል። ‘ከበደኝ አልቻልኩም” ያሉት ሸክማቸውን የሚቀበል ሁሉን ያደርግ ዘንድ የሚቻለው የድንግል ማርያም ልጅ ክርስቶስ በደጅ ቆሞ ሳለ ነውና።
የክብር ንጉስ ይገባ ዘንድ በሩ ይከፈት፤ የክብሩ ንጉስ በቂምና በጥላቻ መካከል ወደ ውስጥ አይዘልቅምና የምዕመኑ ፀሎት እና ምልጃም ከቅዱሳን መላዕክቱ ፅና ከእጣኑ ጢስ ጋር በእግዚአብሔር ፊት እንዲያርግ፤ በዚህ አጋጣሚ የተጣሰው ቀኖና ቤተክርስቲያን ይታረም። በብፁዓን አባቶች መካከል እርቀ ሰላም ይውረድ። ሁለት ሲኖዶስ መንበር አይፀናምና እርቀሰላም በማውረድ በቤተክርስቲያን ሰላም ይውረድ። ቀዳዳ እየፈለገ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ የሚያደባው የተሐድሶ ተኩላም በሩ ይዘጋበት። በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ከዳር ደርሶ ሳለ በህወሓት መንግስት እንቢተኛነት የተደናቀፈው እርቀ ሰላም ይፈፀም።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ስለ ቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም በእናንተ ዘንድ (በውጭ እና በሀገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ) መካከል እርቅ ይሁን። ይህ ሳይሆን ቢቀር ያለ ይቅርባይነት የሚያርግ መስዋዕት የሚሰማ ፀሎት እንደሌለ አስተምራችሁናልና ሁሉ ከንቱ ነው። ልጆቻችሁ ስለ እርቅ እንማፀናለን።
በትህትና !
Filed in: Amharic