>

የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል! (ስዩም ተሾመ)

በሕገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓት በምትመራ ሀገር፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ ህወሓት፥ ብአዴን፥ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ጥምረት የሚመራ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ህወሓትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አድሏዊነት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ ይሄ እውነታ እንጆ አድሏዊነት አይደለም። ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የፌደራል ስርዓቱና ተቋማት፣ እንዲሁም የክልል መንግስታትና ተቋማት የሚተዳደሩበት ሕግ፥ ስርዓትና መዋቅር በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው።
የፖለቲካ ጨዋታውን ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይጫወታሉ። የጨዋታውን ሕግ በማፅደቁ ሂደት ሁሉም ተሳታፊዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ ሕጉ የተረቀቀበት ፅንሰ-ሃሳብ የህወሓት ነው። ይህ የጨዋታ ሕግ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ሲሆን የሕገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ደግሞ በህወሓት የብሔር ፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስትና ተቋማት ይህን የፖለቲካ መርህና አመለካከት ተግባራዊ ለማድርግ የተቋቋሙ ናቸው።

የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕገ መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። ነገር ግን፣ የሕገ መንግስቱ ትርጉምና ፋይዳ በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፣ ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ መሆን ለህወሓት ተገዢ ከመሆን ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

በአጠቃላይ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ከተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሓት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ምክንያቶች፤ አንደኛ፡- መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ሁለተኛ፡- ይህ የፖለቲካ መርህና አመለካከት ፍፁም ስህተት ስለሆነ፣ ሦስተኛ፡- የሥልጣን የበላይነቱን ለማስቀጠል እጅግ አደገኛ የሆነ ሸርና አሻጥር እየፈፀመ ስለሆነ። እነዚህን ችግሮች አንድ ላይ አያይዤ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የዳግማዊ ወያነ ወይም የሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የትግራይ ህዝብን የለውጥ ፍላጎት የብሔርተኝነት ስሜት በመቆስቆስ እና በራስ የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የቀድሞ የህወሓት (TPLF) መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመርና የንቅናቄ ስልት “…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one” በማለት ገልፀውታል።

ነገር ግን፣ ከህወሃት ብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ያነሰ ክብርና ዋጋ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። የትጥቅ ትግሉን ለማስጀመር በትግራይ ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ስነ-ልቦና ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ የተበዳይነትና ወገንተኝነት ስሜት ፈጥሯል። ከደርግ ጋር በተካሄደው ጦርነት የተፈጠረው ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ተቀይሯል።

የዘውግ ብሔርተኝነት እና በራስ የመወሰን መብት ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር (mobilization) ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የፖለቲካ ቡድን የተበዳይነትና ጠላትነት አመለካከት ያለው፣ ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት የሚመለከት ይሆናል። በሕወሃት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ያረፉበት ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሃት ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክልና በጦርነት ወቅት በተፈጠረ ከፍተኛ የተበዳይነት፥ ጠላትነትና ፍርሃት አመለካከት የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ በድርጅቱ መሪነትና የፖለቲካ መርህ ላይ ተመስርቶ የተዘረጋው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የሕወሃትን የስልጣን የበላይነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ነው።

ሁለተኛ እንደ ሕወሃት ያለ የፖለቲካ ቡድን ሌሎች አብላጫ ድምፅ ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይጀምሩ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም አብላጫ ድምፅ ያላቸው ማህብረሰቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ ማድረግ ከቻሉ የአነስተኛ ብሔር የስልጣን የበላይነትንና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ያስወግዱታል። ስለዚህ አብላጭ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጎሳ፥ ብሔርና ቋንቋ በመከፋፈል የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እና የተቀናጀ ንቅናቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ አለበት።

እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የቆመለትን የአንድ ወገን የስልጣን የበላይነትን ሊያሳጣው የሚችል ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ለውጥና መሻሻል፣ ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ለማስተነገድ ዝግጁ አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሃሳብና ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። በዚህ ምክንያት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ሕወሃት/ኢህአዴግ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሳውን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ጥረት አድርጓል።

በመሰረቱ ሕወሃት የስልጣን የበላይነቱ በሕገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በዚያ ረገድ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ አይደለም። በመሆኑም እያንዳንዱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ ይመለከታል። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት በማዳፈን ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ልሂቃን መንግስትን እንዲፈሩ፣ በዚህም የስርዓቱን ሕልውና ለማስቀጠል ጥረት ያደርጋል።

በእርግጥ ፍርሃት (fear) የሕወሃት መርህና መመሪያ ነው። ሆኖም ግን፣ በየትኛውም ግዜ፥ ቦታና ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ እኩልነት (equality) ነው። የሁሉም መብትና ነፃነት እስካልተከበረ ድርስ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄን ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። እንደ ሕወሃት ያሉ ጨቋኞችም የመብትና ነፃነት ጥየቄ ባነሳው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ጥያቄው ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ፣ ሕወሃት ከሚፈጥረው ሽብርና ፍርሃት ይልቅ እድሜ ልክ በተገዢነትና ጭቆና መኖር ይበልጥ ያስፈራል።

ዛሬ የሕወሃትን የሰልጣን የበላይነት የሚቃወም፣ በጭቆና ተገዢነት መኖር የሚጠየፍ ትውልድ ተፈጥሯል። ስለዚህ፣ ወይ የሕወሃት የበላይነት በለውጥና ተሃድሶ ያበቃል፣ አሊያም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሕዝባዊ አመፅና አምቢተኝነት ይፈርሳል። በመሆኑም የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል። ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚታየውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በሸርና አሻጥር ወደ ሁከትና ብጥብጥ በመውሰድ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማዳፈን የሚደረገው ጥረት ሁለተኛውን የለውጥ ጉዞ ከማፋጠን የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ የለውም።

Filed in: Amharic