>

ይደረጋል ሁሉም! (በ.ሥ)

ምሽቴን ማን ወሸማት፤ ኣይሉም ኣይሉም
በሬየን ማን ነዳው፤ ኣይሉም ኣይሉም
ቤቴን ማን ወረሰው፤ ኣይሉም ኣይሉም
ቀን የጎደለ ቀን፤ ይደረጋል ሁሉም
ብሎ ኣንጎራጎረ ደጃዝማች ብሩ የተባለ መስፍን ፡፡ ይህ ሰው ባንድ ወቅት ራሱ ባለስልጣን ስለነበረ የስልጣን ባህርይ በደንብ ገብቶታል፡፡ በዘመናችን ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ ግፎች ሲፈጸሙ በተመለከትኩ ቁጥር ወደ ኣእምሮየ ቀድሞ የሚመጣው ይህ ስንኝ ነው፡፡ ኣዎ፤ ቀን የጎደለ ቀን ይደረጋል ሁሉም
ኣባቶቻችን በጣም ኣቅመቢስ የሆነውን ሰው፤ ቀን የጎደለበት ብለው የሚጠሩትን ያህል፤ ገደብ የለሽ ስልጣን የጨበጠውን ሰውየ ደግሞ ባለጊዜ ብለው ሰይመውታል ፡፡

”ኣደባባይ ቆሞ፤ ኣበጀሁ ቢላችሁ
ይህን ባለጊዜ፤ ምን ትሉታላችሁ “

እንዲል የየጁው ተሸናፊ መስፍን ራስ ኣሊ፡፡ ለኔ ባለጊዜ ማለት ባለስልጣን ከሚለው የላቀ ትርጉም ይሰጠኛል ፡፡ ባለ ፈረስ፤ የፈረስ ባለቤት እንደ ሆነ ሁሉ ባለ ጊዜ የጊዜ ባለቤት ነው፡፡ ጊዜን መቆጣጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዘመናችን ኣንድ ጉልበተኛ ድንገት ኣፍሶ ይወስድህና ወህኒ ቤት ይወረውርሃል፡፡ ከእድሜህ ኣንድ ኣመት ወይም ሁለት ኣመት ይቀማሃል፡፡ ወህኒ ቤት ውስጥ ጸሀይ የምትሞቅበትን ግዜ ለክቶ ይሰጥሃል፡፡ ከተሰፈረልህ ጊዜ በላይ ከሞቅህ ይደበድብሃል፡፡ ከጠያቂዎች ጋር የምታውራበትን ሰኣት ቆንጥሮ ይሰጥሃል፡፡ በተንዛዛ ቀጠሮ እያሸ ቅስምህን ይሰብረዋል፡፡ ወደድንም ጠላንም ፤እድሜያችን ያለው በባለጊዜዎች ኪስ ውስጥ ነው፡፡

”ገደብየለሽ ስልጣን ያለገደብ ያባልጋል“ ይላል ሎርድ ኣክተን፡፡ ኣንድ ባለጊዜ ባቅመቢሱ ላይ ማድረግ የሚፈልገውን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡ ፈሪሃ እግዚኣብሄር፤ የህሊና ወቀሳ፤ የህብረተሰብ ወግና ደንብ የሚባሉት በገደብ የለሽ ስልጣን ፊት የገለባ ምርኩዝ ናቸው፡፡ ቱሱዲድየስ የተባለ የግሪክ ጸሀፊ እንዳለው“ኣንድ ጉልበተኛ ማድረግ ያለበትን ሁሉ ያደርጋል፤ኣንድ ኣቅመቢስ ደግሞ መሸከም የሚችለውን ያክል ይቀበላል”፡፡ ይሄው ነው!!

ኣገር ኣማን ብሎ ጨምቶ የተቀመጠን ዜጋ ፤ እያዳፉ ወስደው በጨለማ ክፍል ውስጥ ለብዙ ወራት ዘግተው ካሰቃዩ በኋላ ነጻ ነህ ብለው ማሰናበት ምን ይሉታል? ይህን ሁኔታ “ቀን የጎደለ ቀን ይደረጋል ሁሉም “ ከሚለው ስንኝ የተሻለ ምን ኣይነት ርእዮተ ኣለም ያብራራዋል?
ሰውን የጸሀይን ብርሃን በመከልከል መቅጣትን ሳስብ ኣንድ ነገር ትዝ ኣለኝ፡፡ ስለስብሐት ገብረእግዚኣብሄር ከተነገሩ ያልተረጋገጡ ታሪኮች ኣንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ኣንድ ቀን ስብሐት ከጓደኛው ቤት ሲጫወት ኣምሽቶ እዛው ይተኛል፡፡ በመንፈቀ ሌሊት ሌቦች ቤቱን ሰብረው ገብተው የሱንና የወዳጁን ልብስና ጫማ ዘርፈው ገለል ይላሉ፡፡ ቀድሞ የተነሣው ጓደኛው ቀስቅሶ ይሄንን ሲያረዳው ስብሐት ተጋግቶ “ ኣይዞህ !እንኳን ጸሀይንና ጨረቃን ኣልዘረፉን እንጅ ችግር የለም ” ኣለው ይባላል፡፡ እንደ ስብሐት እድለኛ ሳይሆኑ ቀርተው ጸሀይንና ጨረቃን የተዘረፉትን ዜጎችን ታሪክ ይዘክራቸው፡፡
ኣለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ የተረኩት ኣንድ ሌላ ታሪክ ላንሳ፡፡ ንጉስ በካፋ ካንድ መነኩሴ ጋር ተጣልቶ መነኩሴውን ጨለማ ቤት ውስጥ ኣስገብቶ ዘጋበት ፡፡ ከሦስት ኣመታት የጨለማ ቆይታ በኋላ መነኩሴው ከእስር ቤት ሲወጣ“ የበካፋ ጸሀይ እንዴት ነሽ!የበካፋ ጸሀይ እንዴት ነሽ!“ በማለት ኣለቀሰ ኣሉ ፡፡ በካፋ ሲሞት እነ መንግስቱ ሃይለማርያም እነ መለስ ዜናዊ ጸሀይን በፈረቃ ወርሰው የግል ንብረት ኣደረጓት፡፡ ኣሁን ይችን ስጽፍ እንኳ “የህወሃት ጸሃይ እንዴት ነሽ? እንዴት ነሽ?” የሚሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

Filed in: Amharic