>

የትግራይ ህዝብና ህወሓት (በኔ እይታ) [ሃብታሙ አያሌው]

……ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የህወሓትን ጥልቅ የዘውገኝነት ሴራ በተገቢ መጠን ያልተረዱ ፖለቲከኞች ደግሞ ስህተት በስህተት ይታረም ይመስል የትግራይ ተወላጅ ሁሉ የህወሓት ጆሮ ጠቢ ነው፣ ትግርኛ የተናገረ ሁሉ ባለሥልጣን ነው፣ ማለትን እንደ ትግል ስልት በመቁጠራቸውና ሰተት ብለው ወደ ህወሓት ወጥመድ በመግባታቸው ለጥላቻ ፖለቲካ ከባድ መሠረት ተጣለ፡፡

እነ መለስ በዚያ ወቅት በተከተሉት የተሳሳተ የፖለቲካ ስልት የተተከለው የፖለቲካ ነቀርሳም ዛሬ ድረስ እያመረቀዘ በኢትዮጵያ ታሪክ ከበጎም ከመጥፎውም ምዕራፍ የራሱ ድርሻ የነበረውን የትግራይን ሕዝብ እንደው በደፈናው ሁሉንም በህወሓት ስልቻ
እያስገቡ መፈረጅ የተለመደ ሆኖ ለመቀጠሉ መግፍዔ ሆነ፡፡
በቁጥር ቀላል ያልሆነ የትግራይ ገበሬ እንደሌላው የአገራችን ክፍል ሁሉ ትላንትም አፈር ገፍቶ ለፍቶ የሚያድር ድሃ፣ ዛሬም በተመሳሳይ ድህነት የሚማቅቅ ስለመሆኑ የሚጠራጠር ካለ በመረጠው አቅጣጫ ከመቀሌ የሙስና ሰፈር አሥር ኪሎ ሜትር ወደ ገጠሩ በመዝለቅ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ትላንት በደርግ፣ ዛሬ ደግሞ በህወሓት ኢህአዴግ ብዙሃኑን የትግራይ ገበሬ ራብ ሲፈታው የህወሓት አመራር ልጆች በአውሮፓ፤ በአሜሪካና በቻይና በዊስኪ እየተራጩ በሶሻል ሚድያ የእዩልን ጥሪ ሲያቀርቡ ታዝበናል፡፡

ተፈጥሮ ፊቷን አዙራ አፈር ነሥታ የድንጋይ ኮረት የሸለመችውን አብዛኛውን የትግራይ መሬት የሚታገለው ድሃ ገበሬ መርጦ ስለተወለደበት እንዳልሆነ ግን መግባባት ላይ ሊደረስበት ይገባል፡፡ መሪዎቹ ነን ባሉት የደደቢት በረሃ ተቧዳኞች የፖለቲካ እብደት ለበርካታ ዓመታት በጦር አውድማነት የመከነ ምድር የሚገፋውን በርካታ የትግራይ ገበሬ በጥቂት የህወሓት ሀብታሞች ሚዛን የሚያስቀምጥ ፖለቲከኛስ እንደምን ፖለቲካ ያውቃል ሊባል ይችላል፡፡ ይህንን ስል በመሐል አገር በትግራይ ስም በትግራይ ሲሆን በአድዋ ስም አድዋ ሲደርስ ደግሞ በመለስና በአቦይ ስብሃት ቤተሰቦች ስም እየማለ በመቀሌ፣ በአድዋና በአዲግራት ትኩረት ሰጥቶ የአገሪቱን ሀብት እያከማቸ እንደ ሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የቀድሞው ሚንስትር ድኤታ የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ‹‹የመለስ ልቃቂት›› የተሰኘ መጽሐፍ ማንበብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic