>

በረከት ማለት ይሄ ነው! (ኤርሚያስ ለገሰ፤ የቀድሞ ሚኒስትር)

ስለ በረከት ስምኦን አቋም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። እሱም ቢጠየቅ ስለራሱ እርግጠኛ ሆኖ መግለጽ የሚችል አይመስለኝም። በህይወቴ ካጋጠሙኝ አለቃዎች ውስጥ የቴርሞሜቱሩ መለኪያ ከዜሮ መቶ፣ ከመቶ ኔጋቲቭ በደቂቃ ውስጥ ሲለዋወጥ ያየሁት በረከትና በረኸት ብቻ ነው። ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ለእኔ እና ሽመልስ ከማል ጠረጴዛ እየደበደበ ” ከነገ ጀምሮ ስራዬን እንደምለቅ ለአባይ ነግሬዋለሁ!” ብሎን ያውቃል። እኛም “አንተ ስትለቅ እኛም እንለቃለን” በማለት ብርታት ሰጥተነዋል።በተለይ አንድ ጊዜ የሆነውን እኔም ሆንኩ ሲንጋፖር ውስጥ በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ሆኖ ቀሪ እድሜውን የሚገፋው ሽመልስ ከማል የምንረሳው አይደለም።

እንዲህ ነበር የሆነው :– 
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሱማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ እንዳያንሰራራ ተደርጐ መመታቱ ተገልጾ ከሱማሊያ መውጣቱ ይፋ ተደረገ። ከዚህ በኋላም ወደ ሱማሊያ ሠራዊቱ መግባት እንደማያስፈልገው ተገለፀ። ብዙ ወራቶች ሳይገፉ በአቶ መለስ ትእዛዝ ሠራዊቱ ወደ ሱማሊያ ተመልሶ ገባ። ይሄን ትእዛዝ የሚያውቁት አባይ ፀሐዬ ፣ ጌታቸው አሰፋ እና “ፕሮፌሰር ጄኔራል!” ሳሞራ የኑስ ብቻ ነበሩ።በረከት ስምኦን አያውቅም። ፓርላማው አያውቅም። የሚኒስትሮች ምክርቤት አያውቅም።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ሱማሊያ እየገባ የሚያሳይ ቪዲዬ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች እጅ ገባ። እናም መረጃውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የመንግሥት ቃል አቀባይ ምን እንደሚል ለማወቅ ወደ አቶ በረከት ስምኦን ይደውላሉ። በረከት በልበ ሙሉነት ውስጥ ሆኖ ” አልሸባብ አከርካሪው በተሰበረበት ሁኔታ የምንገባበት አንዳችም ምክንያት የለም። የጠላት ወሬ ነው” በማለት ምላሽ ሰጠ።

በንጋታው ጠዋት ሰራዊቱ ወደ ሱማሊያ የገባበት ቪዲዬ ተያይዞ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ተሰራጨ። በእርግጥም ሠራዊቱ ወደ ሱማሊያ መግባቱ እና ከላይ የተጠቀሱት የሕውሓት ወሳኝ ሰዎች ትእዛዝ መስጠታቸው ተረጋገጠ። ይሄን የሰማው በረከት ስምኦን እሳት ጐርሶ እኔና ሽሜን በአስቸኳይ ጠራን ። ተሯሩጠን ወደ ቢሮው ስንሄድ በንዴት የፃፈውን የስራ መልቀቂያ አነበበልን። ለአባይ ስራውን እንደሚለቅ በቃል እንደነገረው ጨምሮ ገለፀልን ። በሁኔታው ብንደናገጥም ቆራጥ ውሳኔውን አድንቀን እኛም እንደምንከተለው ቃል ገባን። በተለይ ሽሜ በረከት ተናዶ ሲያየው አስር እጥፍ የሚናደድ በመሆኑ መልቀቂያውን ወደ ቢሮ እንደተመለሰ ፅፎ ጨረሰ። ከግማሽ ሰአት በኃላ ኢንተርኮሙ ጮኸ። በረከት ነበር።

” ቅድም የነገርኳችሁን ትቼዋለሁ ። እናንተም ወደ ስራችሁ በሙሉ አቅም ተመለሱ!” አለን።

ከሰአታት በኃላ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ሪፓርት ደረሰን።አይኔ አንድ ነገር ላይ ተተክሎ ቀረ ። የፈረንሳይ ሚዲያ (AP) የሰራው ዜና ነበር። ” የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሱማሊያ ተመልሶ ገባ የተባለው ውሸት መሆኑን ገለፁ” ይላል። በረከት ማለት ይሄ ነው።

Filed in: Amharic