>

የፍትህ ሃገሯ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ? (ዘመድኩን በቀለ)

ቀልዱስ ቀልድ ነው ።ይልቅ ጋዜጠኛ_ተመስገን_ደሳለኝን በአስቸኳይ ፍቱት ። ይኽ ልመና አይደለም ። የልጁን መብት ነው ይከበር ፤ ጠብቁለትም እየተባለ ያለው ።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አመክሮ ተከልክሎም የተፈረደበትን ሙሉ የ3 ዓመት ፍርድ ጨርሶ መውጣት የሚገባው በዛሬው ዕለት ጥቅምት 3 ነበርም ተብሏል ።

¶ይኼኛው ዜና ደግሞ የሶማሊ ኦሮሞን ግጭት ፣ የኦሮምያን የተቃውሞ ሰልፍ ፣ የኦሮሞ ወጣቶችን ወደ ጣና ሐይቅ ሔደው እንቦጭ ነቀላ የመፈጸማቸውን ዜና ለማጠየም አገዛዙ አይኑን ጨፍኖ ህገመንግሥታዊ መብትን በመጣስ ሰሞኑን በያለንበት እንነታረክበት ዘንድ የሰጠን አጀንዳ መሆኑነ ነው ።

የጋዜጠኛ ተመስገን እናት አረጋዊዋ ወይዘሮ ፋናዬ እርዳቸው ሰሞኑን ልጄ ይፈታል በማለት በደከመ አቅመቸው እንዲያው መሬቱ አልበቃ ብሏቸው ሽርጉድ ይሉ እንደነበርና የቤታቸውን ቀለም ሲያስቀቡ ፣ የሶፋ ጨርቅ ሲያስቀይሩ ፣ በአጠቃላይ ቤታቸውን ሲያስውቡ መክረማቸውን ልጃቸው ታሪኩ ደሳለኝ Tariku_Desalegn በፌስ ቡክ ገጹ ላይ እንዳስነበበን የሚታወስ ነው ። በመጪው ጥቅምት 12 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን በዓል ለማክበርና በዚያውም የልጃቸውን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መፈታት አስመልክተው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በአንድነት ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ በማሰብ ከጽዋ ማኅበርተኞቻቸው ጋር የሚጠጡትን ጽዋ በእሳቸው ቤት እንደዘከር በማድረግ የመልአኩን ጽዋ ተቀብለው እንደአቅሚቲ ድርብ በዓል ለማክበር ድግስ ቢጤም አዘጋጅተው ድርብ በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይም ነበሩ ተብሏል ።

ነገር ግን አረጋዊዋ እናት እንዳሰቡት አልሆነላቸውም ። አልተሳካምም ። ይኸውም ስለምንድነው ያልተሳካው ቢሉ ፤ ዛሬ ወንድሙን ከእስርቤት ተቀብሎ ከናፈቁት እናቱ ጋር ለማገናኘት ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ወደ ዝዋይ እስር ቤት አቅንቶ ነበር ። እናም ወንድሙ ታሪኩ ዝዋይ ደርሶ ለመላው ዓለም ህዝብ የላከው ዜና ግን የምስራች ቃል የነበረው ዜና አለነበረም ። ይልቁኑ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቅስም የሚሰብር ዜና ነው ነበር ታሪኩ ከዝዋይ የላከው ። [የዝዋይ ማረሚያ ቤት ሓላፊዎች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የእስር ጊዜውን ቢፈጽምም እኛ ግን አንፈታውም ] ብለዋል ብሎ ነው መርዶውን ለዓለም ህዝብ ያረዳው ።

በነገራችን ላይ ታሪኩ ደሳለኝ ማለት የጋዜጠኛው ታናሽ ወንድም ሲሆን [ የዘመን ድራማ ] የካሜራ ባለሙያው ነው።ታሪኩ ደሳለኝ።

የሌላውስ ቀላል ነው፤እንዲያው ግን ይሄንን ክፉ ዜና፤ የልጃቸውን መፈታት በጉጉት የሚጠብቁትና ሌቱም አልነጋ፤ ቀኑም አልመሽ እያለ ምጥ እንደያዛት ሴት በስተ እርጅና በዚያውም ላይ ደግሞ በህመም ላይ ፣ እንደገናም በድካም ላይ ሆነው የልጃቸውን ከእስር ተፈትቶ መምጣት በጉጉት እየተንቆራጠጡ ይጠብቁ የነበሩትን አረጋዊዋ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ወይዘሮ ፋናዬ ምን ይሰማቸው ይሆን ? አለማሰቡ ይሻላል ። እንኳን ከእስር ቤት ከደጅ ውሎ የሚገባ ልጇን ከቤቷ እስኪገባ የማያስችላት እናት በእውነት ምን ይሰማት ይሆን ። ይኽንንስ በእውነት ወላድ ይፍረደው ? ከእናት የተወለደ ፣ እናቱን የሚወድ ይፍረደው ።

እነ አሜሪካ እንኳ አሸባሪ የተባሉና የብዙ ዜጎችን ህይወት የቀጠፉ ፣ ንብረት ያወደሙ አሸባሪዎችን ከጓንታናሞ እየለቀቀች ባለችበት በዚህ ዘመን ፤ ብዕርና ወረቀት አዋሕዶ ገዢውን ሥርዓት ሻይ እየጠጣ የሞገተን አንድ ምስኪን ጋዜጠኛ እንዲህ ከኦሳማ ቢላደን በላይ ፈርቶ [ ከወጣ አለቀልኝ ] ብሎ በመንቦቅቦቅ ምን የሚሉት ነው ? ያውም ህግ ጥሶ ፤ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወትር የሚያመልኩትን ህገ መንግሥት በድማሚት ንዶ ስለ ፍትህ ማውራት እንዴት ይቻላል ?

እርግጥ ነው ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ገዢ ይኼኛውን የሰላማዊ ትግል ጨርሶ አያውቀውም ። እሱ የለመደው ጠብመንጃ አንስቶ ተራራ ማንቀጥቀጥ ነበር ። ምሽግ መማስ ፣ በቆረጣና ፣ በደፈጣ ውጊያ አቧራ ሲቅም ፣ በረሃ ለበረሃ ኮቾሮ እየበላ ሲንከራተት የኖረ አካል እንደተመስገን ደሳለኝ ፣ እንደ እስክንድር ነጋ ፣ እንደ አንዷለም አራጌ ፣ እንደ በቀለ ገርባ ፣ እንደ ፕሮፌሰር መመራ ጉዲና አይነቶቹን መሀል አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ማኪያቶና ቀዝቃዚ ቢራ እየተጎነጩ በአንደበታቸውና በብዕራቸው የሚሞግቱትን ዜጎች እንዴት ይቋቋማቸው ። አቶሚክ ቦንብ እንደታጠቀ ሰራዊት ባይፈራቸው ነበር የሚደንቀው ። ምክንያቱም የሰለማዊ ትግሉን የጨዋታ ህግ ሲፈጥረው ጀምሮ አያውቀውም እናነው ።

ይኽ ጋዜጠኛ እንደ ሌሎቹ ጋዜጠኞች ከሀገር የሚወጣበት ብዙ ሰፊ እድሎች ነበሩት ። ነገር ግን በፍጹም በዚያ በኩል ለመጠቀም አልፈለገም ። በአንድ ወቅት እኔ ወደ ሀረር ቅድስት ስላሴ እሱ ደግሞ ወደ ድሬደዋ ለሥራ ጉዳይ ሲሄድ አብረን በአንድ አውሮፕላን ነበር ለረጅም ሰዓት እየተወያየን የሄድነው ። በወቅቱ ተመስገንን ለምን እንደሌሎቹ ጋዜጠኞች ከሀገር ወጥቶ እንደማይሰደድ ጠይቄው እንደነበር ትዝ ይለኛል ። እሱ ግን በፍጹም በጭራሽ ስደትን አልሞክረውም ። እነ እስክንድር ነጋ የገቡበት እስር ቤት ወይም እነ ፕሮፌሰር አስራት የገቡበት መቃብር ቤት ነው የሚከቱኝ አይደል? እናም እጄን በካቴና አስረው ዘብጥያ እስኪያወርዱኝ ድረስ እጽፋለሁ ። እጽፋለሁ ዘመድኩን ነበር ያለኝ ። ” አንተ ከእነ በጋሻው ጋር የምታደርገውን ትግል ለምን አታቆምም ብልህ የምትመልስልኝን መልስ ሳትነግረኝ መገመት እችላለሁ ። ይኼማ እምነቴ ነው እንደምትለኝ አምናለሁ ። ለእኔም ጋዜጠኝነት እምነቴ ነው ። ልሰዋለት ፣ ልታሰርለት ፣ ልገደልለት ቃል ኪዳን የገባሁለት እምነቴ ነው ነበር ያለኝ ። ይኸው ይኼ ሰው እምነቱን እንደጠበቀ ህክምና ተከልክሎ ፣ ጠያቂ ተከልክሎ ፣ አመክሮ ተከልክሎ፣ በመጨረሻም በፍርድቤት ውሳኔ መሰረት በዛሬው ዕለት የሚፈታ ቢሆንም ይኽንንም ተከልክሎ ከህግ አግባብ ውጪ በወኅኒ ቤት እንዲበሰብስ ተፈርዶበታል ።

እውነት ነው ልጁ እልኸኛ ነው ። ተሜ በጋዜጣ ላይ ሃሳቡን መግለጽ የጀመረው #ፍትህ በተባለችው ጋዜጣው ነበር ። ፍትህ ጋዜጣ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ሞት አስቀድማ ከሁሉ በፊት አረጋግጣ በመጻፏ ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ኅትመት ታትሞ እስኪያልቅ ጠብቀው ። ኅትመቷ ከማተሚያ ቤት ሳትወጣ በዚያው እንድትዘጋ የተወሰነባት ናት ። ተመስገን ተስፋ አልቆረጠም በመቀጠል #አዲስ_ታይምስ ብሎ መጻፉን ቀጠለ ። እሱንም ዘጉበት አሁንም እጅ አልሰጠም #ልዕልና ብሎ መጣ እሱንም ዘጉበት ። ተሜ አሁንም እጅ አልሰጠም ፣ ተስፋም አልቆረጠም #ፋክት የሚል መጽሔት ይዞ ከተፍ አለ ። ኢህአዴግ ከዚህ በላይ ሊታገሰው አልፈለገም ። እንዲሰደድ የቦሌንም የባሌንም መንገድ ብርግድ አድርጎ ቢከፍትለትም ተሜ ወይ ንቅንቅ ብሎ በአቋሙ ጸንቶ እንደ አለት ፀንቶ አስቸገረው ። እናም ፋክት መጽሔት ከኅትመት ውጪ እንድትሆን ሲፈረድባት ባለቤቷ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደግሞ የ3 ዓመት እስር ተፈርዶበት ወደ ዝዋይ ተጋዘ ።

አሁን አገዛዙ ውጥረት ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል ። ሶማሌ የራሱን መንግሥትና ባንዲራ ህወሓት ሰጥታው ኢትዮጵያውያን ከክልሌ ይውጡ ብሎ እየገደለም ፣ እየገረፈም ከክልሉ አስወጥቷል ። እያስወጣም ነው ። ደቡብ ከኦሮሞ ጋር የመነታረኪያ አጀንዳ ተሰጥቶት ሲዳማና ኦሮሞ ደም እየተቃባ ነው ። መላው ኦሮሚያ በሰላማዊ ሰልፍ ደጅ ውሎ ማደር ከጀመረ ሰነባበተ ። ጎንደር ዓማራ ቅማንት ፣ ከትግራይ ጋር በፀገደ ፀና በጠገዴ ጠ ንትርክ ውስጥ ናቸው ። የብር የመግዛት አቅም እንዘጭ ብሏል ። ኑሮ እሳት ሆኖ ዜጎችን እየለበለበ መሆኑን እያየን ነው። መብራት የለም ። ስኳር የለም ። ዘይት የለም ። ውኃም የለም ። በዚህ ላይ ታላቁን የጣናን ሐይቅ እንቦጭ ወርሮት ሀገር እየተረባረበ ህወሓት ሆዬ ከዳር ቆሞ ይስቃል ።

እናም በዚህ እሳት ላይ ተመስገንን መፍታት በእሳቱ ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው በማለት ላለመፍታት የቆረጡ ይመስላል ። እግዚአብሔር ያሳያችሁ ያውም ሲፈታ የማይሰደድ ፣ ከሀገሩ የማይኮበልል ፣ መጻፍ መሟገት የማይሰለቸው እሳት የሚተፋ ብዕር ጨብጦ የሚጠበጥባቸውን ጀኔራል ከወኅኒ አውጥቶ ማን ሲንከለከል ይኖራል ብሎ ህውሓት ሆዬ ህገመንግሥቱ አስር ጊዜ ለምን አይደፈጠጥም ፣ ለምንስ ከፈለገ አፈር ከድሜም አይግጥም በማለት የፈለገው ይምጣ ፣ ለምን ዓለሙ ሁሉ አይንጫጫም ብሎ ተመስገንን እዚያው በዝዋይ ቋንጣ አድርጎ ጠብሶ ሊበላው በወኅኒ ከርችሞበታል ።

እንግዲህ ምን እንላለን የተመስገን እናት ሆይ ! ወገብዎን በደንብ ይታጠቁ ፣ እናቴ አዝዎት ። ጽዋውን የሚጠጡት ዝኩሩን በስሙ የሚዘክሩለት ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ጽናቱን ይስጥዎት ። ሌላ ምን ይባላል ። ምንም ።

ለአሁን አበቃሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነልኝ በቀጣይ ደግሞ በሌላ ርዕስ እመለሳለሁ ።

ይኽንም ጦማር ራሴው እኔ ዘመዴ በእጄ ጻፍኩት ። 004915217428134 የቫይበር ፣ በኢሞ ፣ በኋትስአፕ እና በቴሌግራም የሚደርሱኝን መረጃዎችና መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።

ሻሎም.! ሰላም.

Filed in: Amharic