>

የአባይ ጣና ጉዳይ፤ ኢትዮጵያውያን ሐይቃቸውን ለመታደግ መጡ የሚለው በቂ ይመስለኛል

ተሾመ ታደሰ

አማራና ኦሮሞ ይዋደዳል ከሚለው ቃል ይልቅ ኢትዮጵያውያን እንዋደዳለን የሚለው ሀገር ይገነባል | ከሰለሞን ሀይሉ በድሬቲዩብ

እንግዲህ ከአንዱ የሀገር ጥግ ወደ ሌላው ጉዞ ተጀምሯል፡፡ ጉዞው ጣናን ለመታደግ ነው፡፡ 200 የሚሆኑ ወጣቶች ከኦሮሚያ ክልል ወደ ጣና እየዘመቱ ነው፡፡

ጉዞውን ተከትሎ ብዙ ነገር ሲጻፍ እና ሲነገር እየሰማን ነው፡፡ ብዙው አንድ የጋራ ሀገር ለመፍጠር ከሚያልሙ ሰዎች የሚታሰብ ዓይነት እይታ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አወዛጋቢ ሀሳቦች እየታዩ ነው፡፡

መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ድፍን የኢትዮጵያ ምድር ሀገሩ ነው፡፡ ድፍን የኢትዮጵያ ተፈጥሮ የሙሉ ኢትዮጵያውያን ሀብት ነው፡፡ እናም መነጽራችን ይሄ ቢሆን ደግ ነበር፡፡

ብዙዎች የኦሮሞ ወጣቶች ጎጃም ገቡ የሚለውን ዜና ተአምር አድርገውት ይልቁንም በብዙ መልኩ የሚተረጎም ቅኔ ተደርጎ ጉዳዩ ተጋኗል፡፡ ግን የመነጽራችን ችግር ይመስለኛል፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን በማድረጉ ተአምር አድርገነው ልዩነቱን ወደ ገዘፈ ቀዳዳ በመቀየር በኩል የእኛ ሚና ምንድነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ትርጉም አንድና ቀላል ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሐይቃቸውን ለመታደግ ከአንዱ ጥግ ሌላው ጋር ሄዱ፡፡ በቃ ይሄ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ተደርጓል፡፡ አድዋ ተደርጓል፡፡ ማይጨው ተደርጓል፡፡ በቀይ ኮኮብ ጥሪ ተደርጓል፡፡ በእድገት በህብረት ዘመቻ ተደርጓል፡፡ በባድመም ተደርጓል፡፡

ይህንን አረም የመታደግ ዘመቻ ሌላ ትርጉም ሰጥተን ሌላ ትዝብት እንዳይከተል፡፡ አማራና ኦሮሞ ይዋደዳሉ እንደሚል ጸረ ኢትዮጵያ ማን ሊኖር ይችላል፡፡

ኢትዮጵያን የሚወድ ማለት ያለበት እኛ ኢትዮጵያውያን እንዋደዳለን የሚል ነው፡፡ ሀገር መገንባት ከሆነ ትርጉሙ ይሄ ነው፡፡ ሁላችንም ዘረኝነትን አሸንፈን ስለ ሁላችንም ፍቅር ማውራትና መናገር መቻል፡፡
እዚህ ሀገር ትንሽ ቁርሾ እና ትንሽ ደስታ ናቸው ሀገር ሲያምሱ የኖሩት፡፡ ከስሜታዊነት መውጣት አለብን፡፡ ጣና የሁላችንም ነው፡፡

ጣናን መታደግ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው፡፡ በሀገር ጉዳይ የምንጠላውን የመንግስት ቋንቋ ደግመን መጠቀም የለብንም፡፡ የብሔረሰብ ቀን በሁለቱ ክልሎች የሚከበር አስመሰልነው፡፡ ወንድሞቻችን ጣናን ለመታደግ ሆ ብለው ዘምተዋል፡፡ ድሉ ይሄ ነው፡፡ ቃሉም ይሄ ነው፡፡

Filed in: Amharic