>

የኢህአዴግ​ ለዛ-ቢስ ቃላቶች:- ጥገኝነት፥ ጠባብነትና አክራሪነት (ስዩም ተሾመ)

ክፍል-1

ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ቅጥ ከመደጋገማቸው የተነሳ ለዛ-ቢስ የሆኑ ቃላት አሉ። ቃላቱ በዜና እወጃ፣ በባለስልጣናት መግለጫ፣ በግለሰቦች አስተያየት፣ በፖለቲካ ክርክር፣ በስልጠና መድረክ፣…ወዘተ ከመደጋገማቸው የተነሳ ለዛ-ቢስ እና ትርጉም-አልባ ወደ መሆን ተቃራበዋል። እነዚህ ቃላት በዋናነት የኢህአዴግ መንግስት “የሩብ ምዕተ ዓመታት ‘ፈተናዎች’ እና ‘ስኬቶች’” በማለት በተደጋጋሚ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውላቸው ናቸው።

ለምሳሌ፣ በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስልጠና በተዘጋጀ ሰነድ ላይየ፤ “የሩብ ምዕተ ዓመታት የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ እየታዩ ያሉ ፈተናዎችንና መፍትሄዎቻቸው” በሚል ንዑስ-ርዕስ የሚከተሉትን ችግሮች ይዘረዝራል፡- “ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የትምክህትና ጠባብነት አደጋዎች እንዲሁም ሃይማኖትን ሽፋን የሚያደርገው አክራሪነት ፈተናዎች አሁንም ቅርፃቸውን ቀይረው ወይም በሌላ ተተክተው ስላሉ ፈተናዎቹን ለማለፍ የተከተልናቸውን ስልቶች ይበልጥ አጠናክረን ያገራችንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማደናቀፍ ወደ የማይቻልበት ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ በመሆኑ…” የከፍተኛ ትምህርት ማህብረሰብ ሥልጠና ለ2009 ትምህርት ዘመን ዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፥ መስከረም 2009፥ ገፅ-7 

በተመሣሣይ፣ በ2006 ዓ.ም በመስከረም ወር ላይ ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰጠው ስልጠና ተዘጋጅቶ የነበረው ሰነድ ደግሞ፤ “የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ” በሚል የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፦

“…ትምክህትና ጠባብነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት እና የእነዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነው ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ (ኪራይ ሰብሳቢነት) በመፍታት የተያያዝነውን የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ አጠናክረን ልንቀጥልበት እንደሚገባ…” የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ፥ ሐምሌ 2006 ዓ.ም፥ ገፅ-34

ከላይ እንደተጠቀሰው በ2006 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም የተዘጋጁት ሁለት ሰነዶች በሀገሪቱ እየታዩ ላሉት ችግሮች መንስዔዎች እና መፍትሄዎች አንድና ተመሳሳይ ናቸው። የኢህአዴግ መንግስት አመት በወጣና በገባ ቁጥር ተመሣሣይ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ የሙጥኝ ማለቱ ባለበት እየረገጠ ስለመሆኑ ያሳያል። ነገር ግን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየረና እየጨመረ መጥቷል።

በአጠቃላይ፣ ከሁለት አመት በፊት ሆነ ከሁለት አስርት አመታት በፊት የኢህአዴግ መንግስት ፈተናዎች ተብለው የሚጠቀሱት “ጥገኝነት፣ ትምክህትና ጠባብነት” ናቸው። እነዚህ ቃላት ያለቅጥ ለፖለቲካ ፍጆታ በመዋላቸው ምክንያት ለዛ-ቢስ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የቃላቱን መሰረታዊ ትርጉም አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመለከታለን።

ጥገኝነት፥ ጠባብነትና አክራሪነት

የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ባዘጋጀው የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ የቃላቱን ፍቺና ከነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመልከት። በመጀመሪያ “ጥገኛ” (ጥገኝነት) የሚለውን ቃል ስንመለከት፣ “በሌላው አካል ወይም ድርጅት ጥላ ስር የሚንቀሳቀስ” የሚል ፍቺ አለው። በተለይ ከአስር ዓመታት በፊት ራሳቸውን ያልቻሉ፣ በውጪ ኃይሎች እርዳታና ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸው እርግጥ ነው። ዛሬ ላይ በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ ማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም፣ የበጎ-አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ እና ከ1997 ዓ.ም በኋላ ያለው ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ከመንግስት እውቅና ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት እንዳይኖሩ አድርጓል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳው የሻዕቢያ መንግስት፣ ግንቦት7 እና የኦሮሞ ነፃ-አውጪ ግንባር (ኦነግ) ወደ ሀገር ውስጥ “ተላላኪዎችን” ከማስገባት ባለፈ የተደረጀና በእነሱ እርዳታና ድጋፍ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል የመፍጠር አቅም የላቸውም። አሁን በሀገሪቱ ለተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት የሻዕቢያ መንግስትን፣ ግንቦት7ና ኦነግን ተጠያቂ ማድረግ “የኢህአዴግ መንግስት ከእነዚህ ኃይሎች የባሰ አቅመ-ቢስ ሆኗል” ብሎ በራስ ላይ ከመመስከር ያለፈ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። በአጠቃላይ፣ “ጥገኛ ኃይሎች…” የሚባለው በመንግስት ድክመት ምክንያት ለተፈጠረ ችግር ሌሎችን ተጠያቂ (externalize) ለማድረግ ነው።

“ጠባብ ብሔርተኛ” (ጠባብነት) – “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። በእርግጥ ከ20 ዓመታት በፊት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን የማይቀበሉና በኃይል የመገንጠል ጥያቄ የሚያቀርቡ ኃይሎች ነበሩ። ዛሬ ላይ ግን፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ራስን-በራስ የማስተዳደር መብታችን ይከበር የሚሉ እንደ ቅማንት፥ ኮንሶና ወልቃይት ማህብረሰቦችን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተረፈ፣ የመገንጠል ጥያቄ በማቅረብ ወይም ፅንፍ የወጣ የብሔርተኝነት አቋም ይዞ ከፍተኛ ግጭትና አለመረጋጋት ሊፈጥር የሚችል የተደራጀ ኃይል የለም ማለት ይቻላል።

“ትምክህት” (ትምክህተኛ) – “ከመጠን በላይ በራስ መመካት፥ መተማመን፣ ራስን ከፍ አድርጎ የሚያይ” ማለት ነው። ከ10 ዓመት በፊት በብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚቃወሙ ኃይሎች ነበሩ። ከብሔር ማንነት ይልቅ በብሔራዊ አንድነት ላይ ለተመሰረተ አህዳዊ ሥርዓት ቅድሚያ የሚሰጡ ብዙ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደነበሩም እርግጥ ነው።

በመሰረቱ፣ ጠባብነትና ትምክህተኝነት የጥገኝነት አስተሳሰብ (አመለካከት) ውጤቶች አይደሉም። ጥገኛ የፖለቲካ ኃይል ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አይችልም። “ጠባብ ብሔርተኛ” ከሌሎች ብሔሮች ይልቅ የራሱን ብሔር ወይም ጎሳ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም ነው። “ትምክህተኛ” ደግሞ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሞክር ነው። ሁለቱም ለራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ እንጂ የውጪ ኃይሎች አጀንዳ የሚያስፈፅሙ አካላት አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ፣ አሁን በኢትዮጲያ ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር ለጥገኛ ኃይሎች የሚመች ሁኔታ የለም። ከዚያ ይልቅ፣ በጠባብነት እና ትምክህተኝነት ውስጥ የሚንፀባረቀው የጥገኝነት አስተሳሰብ ሳይሆን አግባብ የሆነ የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ ነው።

“ትምክህተኛ” የሚለው እሳቤ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በባህላቸውና በታሪካቸው ላይ ያላቸውን የራስ መተማመን ስሜት የሚሸረሽር ነው። በዚህ መልኩ የሚደረገው ተፅዕኖ በአማራ ልሂቃን ላይ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ይፈጥራል። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው በአማራነቱ ብቻ “ትምክህተኛ” እየተባለ ታሪኩና ማንነቱ እንደ ጥፋት ሲቆጠር በውስጡ የብሔርተኝነት ስሜት ያቆጠቁጣል።

በተመሣሣይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው እሳቤ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ያለውን ድርሻ የሚያንኳስስ፤ በሀገሪቱ አንድነት ላይ ያለውን የምሶሶነት ሚና ወደ አንድ ግንጣይ ቅርጫፍነት የሚያሳንስ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚገባውን መጠየቁ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ “በጠባብነት” ሲፈረጅ በኃይል ሚዛኑን ውስጥ የሚገባውን ድርሻ ለመያዝ በራሱ መንቀሳቀስ ይጀምራል።

በአጠቃላይ፣ ኦሮሞን “ጠባብ ብሔርተኛ” በሚል በሀገሪቱ አንድነት ውስጥ የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከብሔርተኝነት ወደ አንድነት እየቀየረ መጥቷል። በተመሣሣይ፣ አማራን “የትምክህተኛ አንድነት” በሚል እንደ ብሔር የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከአንድነት ወደ ብሔርተኝነት እየቀየረ መጥቷል። የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ በዚህ የሽግግር ሂደት መሰረት ከሁለት ተቃራኒ ጫፎች ወደ መሃል በመምጣት ያልተጠበቀ ጥምረት ተፈጥሯል። ይህ አንደ ቀድሞው በሁለት ተቃራኒ ፅንፈኞች መካከል የተፈጠረ ጥምረት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁለቱም ሕዝቦች በማንነታቸውና በሆኑት ልክ የሚገባቸውን ጥቅምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴው የተፈጠረ የጋራ ጥምረት ነው። በመሆኑም የኦሮሞና አማራ ጥምረት በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ጥምረት ነው።

Filed in: Amharic