>

አሮጌ ወይን በአዲስ አቁማዳ (ያሬድ ጥበቡ)

በአንድ ወቅት እንደ አንጋፋ ልጄ ያህል እቆጥረው የነበረው የኔው ጃዋር መሃመድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሮሞ ምልክት አድርገው የመረጡትን የዋርካ ምስል በተለያዩ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ላይ እያስሳለ ለተከታዮቹ እያሰራጨ ይገኛል ። በተለይ በበጎች፣ ፍየሎች፣ ላሞችና ወይፈኖች ፀጉር ላይ በተደጋጋሚ የዋርካው ምስል ያለባቸውን ስእሎች ይለጥፋል ። ከሱ ተቀብለው የሚያባዙትም የኦሮሞ ወጣቶች ቁጥር የትዬለሌ ነው ። ዓላማውም ግልፅ ነው ። ዋቃ ወይም አላህ የኦሮሚያ መንግስት ለማቆም ደርሳችኋል፣ በርቱ ትግሉን የበለጠ አቀጣጥሉ፣ የመጨረሻው ክብረወሰን ላይ ለመድረሳችሁ ምልክት ይሆናችሁ ዘንድ የበግ ግልገሎችና ጥጃዎች እንኳ ሳይቀሩ የባንዲራችሁን ማህተም ይዘው መወለድ ጀምረዋል የሚል ነው ። ይህ መቼም የለየለት እብደት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ቢሆንም፣ ከብልህ አእምሮ ተጠንቶ የቀረበ ስልት መሆኑን ግን መርሳት የለብንም ። ፍርሃቴ በዚህ የጃዋር ስልት ያበደ ብሄርተኛ በህፃናት ደረት ወይም ጀርባ ላይ ይህንኑ የዋርካ ምስል በጋለ ማጭድ ተኩሶ የዋቃን ምስክርነት ሊያሳየን እንዳይሞክር ነው። ጃዋር እነዚህን የዋርካ ምስሎች ተፈጥሮአዊ አድርጎ ለማቅረብ ለምን ፈለገ ብለን ግን መጠየቅ ይኖርብናል።

አንድ የገዢ ልሂቅ ወይም ኤሊት የሚናገረውና የሚሰጠው ቀጭን እዝ ያለምንም ጥያቄ ተቀባይነት እንዲኖረው፣ በአለም ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠጉበት ሽፋን ሐይማኖትን ወይም የህዝቡን ባህልና ትውፊት መሸሸጊያ በማድረግ ነው ። እነዚህ ደካማ ወይም ጠቃሚ ሆነው ሳይገኙ ደግሞ ብሄርተኛ ርእዮተዓለምን በሐይማኖት ቀኖና ደረጃ ከፍ በማድረግ ያንን የጠየቀ ወይንም የተቃወመን ሁሉ በመኮነን ፍፁም የበላይነት ለመያዝ ይሞከራል ። በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ እስከ ቅርብ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያችንም የነገስታት ቅባትነት (divine intervention) ይሰበክ የነበረው፣ በጉልበት ወይም በደም ሥልጣን ላይ የወጡ ነገስታትን ህዝቡ ፈጣሪው የላከለት መሪዎቹ መሆናቸውን ተቀብሎ ተንበርክኮ እንዲኖር ፣ ቢከፋው እንኳ ነፍጥ ከማንሳት ይልቅ ለፈጣሪው እያለቀሰ ምህላ እንዲያቀርብ የሚያስገድድ ባህል በጭቆና አኑሮናል ። ቤተክርስቲያንም አንጋሽና አወዳሽ ሆና ሲሶ መንግስት በመሆን ከገዢዎቹ ጋር ስታስገብር ኖራለች።የየካቲት አብዮት የገረሰሰው ይህን አስከፊ ሥርአት ነበር።

ስንት የተገበረለት የኢትዮጵያ የነፃነትና እኩልነት ትግል ዛሬ ሥልጣን ላይ በወጡም ሆነ ለሥልጣን በሚታገሉ የክልል ብሄርተኞች ተጠልፎ አክ እንትፍ ብለን ወደመጣነው የጨቀየ አስተሳሰብ ሊመልሱን፣ በዚያውም ወደማያባራ የርስበርስ ጦርነት ሊማግዱን አሰፍስፈዋል ። የጃዋር የእንስሳት ፀጉር ላይ ምስል ዘመቻ የህዝቡን ኋላቀርና የቀቢፀ ተስፋ ስሜት በመኮርኮርና በማነሳሳት፣ ይሄው ፈጣሪ መጪው ጊዜ የናንተ ነው የነፃይቱ ኦሮሚያ ቀን ቀርቧል እያለን ነው ብሎ ለማነሳሳት የሚጠቀምበት መሆኑ ግልፅ ነው ።

ትልቁ ችግር ይህ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተደጋጋሚ የሠራ አሁንም ሊሠራ የሚችል ስልት ነው ። ሥልጣንና ሐይማኖት ፣ ሥልጣንና የህዝቡ ባህላዊ እምነቶች ሲቆራኙ፣ ህዝቡ ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዢ የመሆን አደጋው እጅግ የከፋ ነው ። ጃዋር የፖለቲካ ሳይንስ ጠቢብ በመሆኑ ይህን ዕውነታ ደርሶበታል ። እየተጠቀመበትም ነው ። ምን ይሻላል?

በእኛ ትውልድ ዘመን ቢሆን አሁን ጃዋር የሚያደርገው አይነት ብልጥነት የማይታሰብ ነበር ። በተለይ ለግራው ሃይል ። ይህን መስመር የተላለፈ ወያኔ ነበር ። ለምሳሌ በየቀበሌው ወጣቶችን ለሠራዊታቸው ሲመለምሉ እምቢተኛ የሆኑትን ወጣቶች ቀሚስ ያስለብሷቸው ነበር ሲባል ሰምቻለሁ ። አላየሁም ። በእድሜ እኩዮቻቸው እንደ ሴት ብሎም እንደፈሪ እንዳይታዩ “አቀብለኝ ካላሽኔን፣ እንደ አባቴ መኩሪያዬን” እያለ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ወጣቱ እንዲግተለተል የአእምሮ ጫና አድርጎበት ነበር ። ኢህአፓ ግን ይህን ማድረግ አይቻለውም ነበር ። ፍርሃትን ከቀሚስነትና ሴትነት ጋር ከማያያዙ አስቀድሞ ራሱን ማጥፋት ነበረበት ።

ከየካቲት አብዮት ወዲህ ባሉትም አመታት ቢሆን ከደርጉ ጀምሮ ሥልጣን ላይ መውጣት የቻሉት ሀይሎች በባህልና ትውፊት የቆየን ሰሜት መኮርኮር የቻሉት ናቸው ። አሁንም የጃዋር የነፃነት ምስሎች ሀይል አላቸው ። የህዝቡን የነፃነት ተስፋ ከፈጣሪ ምልክታ ጋር በማቆራኘት ለመጨረሻው ፍልሚያ ያዘጋጀዋል ። ወያኔ ይህን አይነት የረቀቀ ግፊት መቋቋም ይችል የነበረው፣ የኢትዮጵያን ብሄርተኝነት በጠላትነት ፈርጆ ለ25 ዓመታት ባይቀጠቅጥ ነበር ። ሆኖም ጠባብ የሥልጣን ፍላጎቱ የኦሮሞና የኢትዮጵያን ብሄርተኝነቶች ተፎካካሪና ተገዳዳሪ አድርጎ በማቅረብ እርሱ የመሃል ዳኝ ሚና መጫወትን መረጠ ። ያ ጨዋታ አሁን ከደረስንበት ጭው ያለ የገደል አፋፍ አድርሶናል ። ሆኖም የግድ መውደቅ የለብንም ። የገደሉን አስከፊነት አይተን ወደኋላ መመለስ እንችላለን ። ትልቁ ሃላፊነት ወያኔ ላይ ወድቋል ። ትልቁ ሃላፊነት የትግራይ የቢዝነስ፣ ሚሊተሪና ደህንነት ኤሊት ላይ ወድቋል ። የኢትዮጵያን ብሄርተኝነት ጥንት ነበረው ብለው ከሚያምኑት አግላይነት፣ ጠባብነትና ድክመት አላቀው፣ ድሮ በነበረው መልካም ጎኖቹ ላይ ሁሉንም ያካተተና ያቀፈ ገፅታ አላብሰውት እንደ አዲስ በባለቤትነት ሊቆሙለት ይገባል ። አለበለዚያ ዛሬ ከጃዋር የሚማሩት የአማራ፣ የሱማሌ፣ የአፋር ወዘተ ብሄርተኞች በህዝቡ ውስጥ ተቀብረው የኖሩ ኋላቀር አስተሳሰቦችንና ሰሜቶችን በመኮርኮር ወደ እርስበርስ እልቂት ልንወርድ እንችላለን ። ይህ ከመሆኑ በፊት አሰባሳቢና ሁሉንም ያካተተ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ እንወያይበት ። የዩሱፍ ያሲን “አሰባሳቢ ማንነት በአንድ ሃገር ልጅነት” መፅሃፍ መነሻ መወያያችን ሊሆን የሚችል ይመስለኛል። አይዞን! እንዲህ በቀላሉማ እጅ አንሰጥም።

Filed in: Amharic