>

በአገር ጉዳይ ድርድር የለም! (ሃብታሙ አያሌው)

አገር ከሌለ ህዝብ የለም! ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊነት ይለምልም የምንለው። ኢትዮጵያዊነት ከሌለ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ልትኖር አትችልም። ትበታተናለች። ትበታተናለች ማለት ግን ሌሎች ራሳቸውን የቻሉ (independent) ትናንሽ አገራት ይወጧታል ማለት አይደለም። ሲፈርስ ኮላተራል ዳሜጅ የሚባል ነገር አለው። አዲስ እግር እተክላለሁ የሚለው ተገንጣይም ከሌሎች ተገንጣይ ጎረቤቶቹ ጋር ለትውልዶች የሚዘልቅ የጦርነት ቁርቁዝ ውስጥ ይገባል። በተገነጠለው መንደር ውስጥ ብቻ የተለያየ የጎሳና የእምነት ማንነት ያላቸው ሰዎች ይጫረሳሉ። ህይወት መራራ ትሆናለች። ባለጉልበት ብቻ ራሱን የሚከላከልባት ሁኔታ ይፈጠራል። እያንዳንዱ ሳይቀድመኝ ልቅደም በሚል ፈሊጥ ጎረቤቱን ሲጥ እያደረገ ያደራል። ፖለቲከኞቹ ድንጋጤው ስላማይወጣላቸው የሚይዝ የሚጨብጡትን ያጣሉና አገርን (አዲሷን መንደራቸውን) ማረጋጋት አይቻላቸውም። እነሱም ዘንድ ለስልጣን በሚደረግ ሹክቻ ደም መፋሰስ እና አንገት መቃላት የለት ተለት ኑሮ ይሆናል።

ለ3ሺ ምናምን ዓመት የተገመደ social fabric በጣጥሰህ አዲስ አገርና ማንነት እገነባለሁ ስትል የምታጭደው ይህንን ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ላይ የደረሰችው፣ አገር መገንባት የሚያስከትለውን ወጪና መስዋእትነት በየጊዜው እየገበረች ነው። ደርግ የገነባውን ድልድይ አፍርሶ በወያኔ ኢንጅነር እንዳዲስ እንደመስራት ቀላል አይደለም። መጪው ትውልድ ያላንዳች ደም መፋሰስ፣ ህይወቱን በእውቀት እያበለጸገ ሌሎች እንደሚኖሩት የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር፣ አገሩን አበልጽጎ ወገኑን ከርሀብና ከእርዛት እንዲታደግ፣ በቅድሚያ የዛሬው ትውልድ ያለአንዳች ድርድር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ሲችል ብቻ ነው!! በዚህ አገርና የጋራ ማንነት ማዕቀፍ ስር እያንዳንዱ ዜጋ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ደረጃ መብቱን የሚያስከብርበት፣ ፍትህን የሚሰፍንበት፣ እኩልነትን የሚረጋገጥበት ወዘተ ስርዓት በድርድር በፉክክር በሀሳብ ፍጭት ወዘተ መፍጠር ይችላል። ይህን ተቀበሉ፣ ይህን አትቀበሉ ያለ የለም። አይኖርም። ሊኖርም አይችልም። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከማይቀበል ሰው ጋር ግን በነዚህ ነጥቦች ላይ መደራደር ማለት ከነ ድርቡሽ፣ ኦቶማን፣ ጣልያን ወዘተ ጋር በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንደመደራደር ማለት ነው። ባጭሩ፣ ባእድ ናቸው። ከባዕድ ጋር በአገርና ህዝብ ሉአላዊ ጉዳይ ላይ ድርድር የለም። ኖሮም አያውቅም።

Filed in: Amharic