>

የብሔር ትርጉም፤ ያረጀው የሌሊን-ስታሊን እና አዲሱ አረዳድ፤ (ውብሸት ሙላት)

የዐምሐራ ብሔርነት በእነዚህ መለኪያዎች
ክፍል አንድ

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት (በሌኒን እና በስታሊንም) መሠረት “ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ” ለመባል አምስት መሥፈርቶች መሟላት አለባቸው፡፡ እነዚህም፡-ተመሳሳይ ባህል ወይም ልምዶች ፣ መግባቢያ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና፣ የሥነ-ልቦና አንድነት እና በአንድ በተያያዘ አካባቢ መኖር ናቸው፡፡

ለነገሩ ከላይ የተዘረዘሩት መሥፈርቶች በዚህ ዘመን ተቀባይነት የላቸውም፡፡ የተለየ  ቋንቋ መኖር ግድ አይደለም፡፡ አንድ አካባቢ ላይ ሰፍረው ባይገኙም፣ የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት ባይችሉምና ባይፈልጉም እንደብሔር ዕውቅና ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በታሪክ ብሔርተኝነትን ድንበር ገድቦት ሲቆም አልታየም፡፡ራስን በራስ ለማስተዳደር የግድ በአንድ አካባቢ መኖር ወሳኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገር ለመመሥረትም እንደዚሁ፡፡

ሀገር መመሥረት የማይችልን፣ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል በአንድ በተለዬ አካባቢ መኖር ካልቻለ ብሔር ወይንም ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ አይደላችሁም ማለት ግን አሳማኝ አይመስልም፡፡ ለነገሩ ዕውቅና ማግኘት የግድ መስተዳድር ለማቋቋም ብቻ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ዕውቅና፣ በአብዝኃኛው ሥነ-ልቦናዊ ይዘት ነው ያለው፡፡ አስተዳደራዊ እርከን ከማቋቋም ውጭም ብዙ መብቶች አሉና፡፡

ሌላው የባህልና የልምዶች ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የተለየ ስም ያለው ሕዝብ፣ የኔ የሚለው የጥንት መኖሪያ ያለው፣ በአንድነት የሚተርከው አፈታሪክና ተረት፣ ትዝታና ተመሳሳይ ባህል ያለው እንዲሁም ከሕዝብ የሚመነጭ የጋራ መብትና ግዴታ ካለው ይህ ብሔር ነው የሚሉም አሉ፡፡  ይሁን እንጂ እነዚህ መለኪያዎች ብዙ ጊዜ ለጎሳና ለነገድ መለያነት ሊያገለግሉም ስለሚችሉ በመጠንና በስፋት ከፍ ላሉት ለብሔርና ለብሔረሰብ በቂ መለያዎች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም በተለይ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ባህላቸው ላይለያይ ይችላል፡፡

ለአብነት በኦሮሚያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ አማሮች ከአማራ ባህልና ልምዶች ይልቅ የኦሮሞ ባህልና ልምድ የበለጠ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ነባር ሬድ ኢንዲያንስ ከባህል አንጻር ከሌላው አሜሪካዊ የተለየ ባህል ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ጂንስ ለብሰው፣ በተመሳሳይ ቅላጼ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናግረው፣ ማክዶናልድ ዋና ምግባቸው ሆኖ ከማንነት አንጻር ግን ራሳቸውን ሌላ ብሔር/ማኅበረሰብ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በመሆኑም ባህል ቁርጥ ያለ መለያ ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን በተጨማሪነት ለመለያነት አያገለግለም ማለት አይደለም፤የተለየ ባህል ያላቸው የሉም ማለትም ደግሞ አይደለም፡፡

ሌላው የብሔር ማንነትን የሃይማኖት ተመሳሳይነት ወይንም መለያየት አይወሥነውም፤ሃይማኖትን  መለወጥም ብዙም ከብሔር ማንነት ጋር ቁርኝት የለውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ዋቀፌታን ትቶ የፕሮቴስታንት እምነት ቢከተል አንዱ የኦሮሞነት የጥንቱ መገለጫ ዋቀፌታ ቢሆንም ሃይማኖታዊ ለውጡ ለብሔሩ የሚኖረውን ታማኝነት አያሳጣውም፡፡  ቋንቋው ተቀይሮም፣ ባህሉ ተዋህዶም፣ ኢኮኖሚያዊ መገለጫዎቹም ቀርተው ብሔርና ብሔርተኝነት ሊኖር ይችላል፡፡

አራተኛው መስፈርት የጋራ ዘር ወይንም ህልውናን የተመለከተ ነው፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ብሔር ማለት የጋራ ዝርያ መጋራቱን የሚያምን በዛ ያለ ሕዝብ የያዘ ስብስብ ወይም ቡድን ነው በማለት ይተረጉሙታል፡፡ የጋራ ዝምድና አለኝ ብሎ ማሰቡ፣ በጋራ “ሆ” ብሎ እንዲነሳና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ያስችለዋልም፡፡ በጥንታዊው የአውሮፓውን የብሔር አረዳድ ብሔር ማለት “አንድ የጋራ የዘር ግንድ አለን በሚል ስህተት፤ እንዲሁም በጋራ የሚጠሏቸው ጎረቤቶች እንዳላቸው በማሰብ በእነዚህ አንድነትን የፈጠሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው” የሚል ነው፡፡

የአንድ ብሔር ተወላጆች እውነትም ይሁን ስህተት ከጋራ ዘራችን ከእንቶኔ ነው የመጣነው፤እነ እቶኔ ደግሞ ጠላቶቻችን ናቸው በማለት የጋራ ጠላት በውስጣቸው ካሰረጹ አንድ ጠንካራ ብሔር ለመሆን ይረዳል እንደማለት ነው፡፡የጋራ የዘር ግንድ ባይኖርም የጋራ ጠላትን ግን ልሂቃኖች ሊፈጥሩት ይችላሉ፡፡የጋራ ጠላት እንዳለው በማድረግ ብሔርተኝነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡

የመጨረሻው መሥፈርት ሥነ-ልቦናን የተመለከተ ነው፡፡ አንዳንዶች ብሔር ሲሉ በአብዝኃኛው የሥነ-ልቦናና የአመለካከት ጉዳይ በማድረግ ሙግታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ተጨባጭ የሆነ መለያን አይፈልግም፡፡ በምሳሌ ለማብራረት ያህል አንድ አባትና እናቱ ኦሮሞ የሆነ ልጅ አዲስ አበባ ተወልዶ አደገ ብንልና ኦሮምኛ አይችልም ብንል፤ በባህልም ረገድም ባህሉ እንደአዲስ አበቤው ቅልቅል እንጂ ቱባ የሆነውን የኦሮሞ ባህል አያውቅም እንበል፡፡ የብሔር ነገር የሥነ-ልቦናና የአመለካከት ስለሆነ ይሔ ልጅ “ኦሮሞ ነኝ” ማለቱን ወይንም መሆኑን አይተውም፡፡ በእርግጥም የብሔራቸውን ቋንቋ ሳያውቁ፣ ባህላዊ ክንዋኔዎችንም ሳይተገብሩ የብሔር ታማኝነታቸው፣ ማንነታቸው ግን ከወላጆቻቸው በደም ያገኙትን ብሔር የሆኑ እልፍ አእላፍ ግለሰቦች እናገኛለን፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት እንደአሜሪካም ባሉ ሀገራት ምንም የባህልና የቋንቋ ልዩነት ሳይኖራቸው ሂዝፓኒክ፣ ሬድ ኢንዲያንስ ወዘተ መሆናቸው ላይ ግን ፈጽሞ ላይደራደሩ ይችላሉ፡፡ የባህል ውህደት/ተመሳስሎሽም የሥነ-ልቦና ውህደትን ላያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ የብሔር ጉዳይ በዋናነት የአመለካከትና የሥነ-ልቦና አንድነት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የዐምሐራ የብሔር ጉዳይም ሲነሳ ሕገ መንግሥቱ ላይ በተገለጸው መለኪያ ይሁን በአሁኑ ወቅት የበላይነት ካገኘው መሥፈርት አንጻር ቢታይ ቅንጣት ታክል የሚጎድለው ነገር የለም፡፡

በጉዳዩ ላይ የበለጠ ለመረዳት የሚከተሉትን ጽሑፎች ማንበብ ነው፡፡

ማጣቀሻ፡-
Connor, Walker (1972) “Nation-Building or Nation-Destroying?” World Politics, Vol.24,No.3.
Connor, Walker, (2004) “The timelessness of nations” Nation and Nationalism, Vol.10.
Connor, Walker. (1984) The National Question in Marxist-Leninist Theory and Strategy, Princeton, NJ: Princeton University Press.
Connor, Walker.(1980), “Nationalism and Political Illegitimacy”, Canadian Review of Studies in Nationalism. VII (Fall 1980). Eugen. Weber, (1976) Peasants into Frenchmen: The Modernization of Rural France, 1870–1914. Stanford, Calif.
Gellner, Ernest (1987) Nationalism. London, Weidenfeld and Nicholson.
Hayes, H.(1931) The Historical Evolution of Modern Nationalism. New York: Macmillan.
Lenin, I.Viladmir The Right of Nations to Self-determination, Collected Works, Vol.20.
Smith, D. Anthony (1999), Myths and Memories of the Nation, Great Britain, Oxford University Press.

Filed in: Amharic