>

አማርኛ ቋንቋ እንዴት ተወለደ? እንዴትስ አደገ? (ጥበቡ በለጠ)

ይህን ፅሁፍ እንዳዘጋጅ የገፋፋኝ አንድ ጉዳይ አለ። ሰሞኑን አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ በሆነ አጋጣሚ ተገናኘን። ወጣቱ አማርኛ ቋንቋን አይችልም። አይናገርም አይጽፍበትም። ግራ ገባኝ። አብሮት ወዳለው ጓደኛው ዞር አልኩና የት ተወልዶ እንዳደገ ጠየኩት። ነገረኝ። እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ግን ዩኒቨርሲቲ እስከሚገባ ድረስ አማርኛ ቋንቋን አልተማረም። ጉዳዩ ከነከነኝ። ጥፋቱ የማን ነው? የልጁ ነው? የወላጆቹ ነው? የመንግስት ነው? ወይስ የፈጣሪ እያልኩ ቆዘምኩኝ። አንድ ሃሣብ ግን መጣልኝ።

ኢትዮጵያን እየመሯት ያሉት አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ለሕዝባቸው ንግግር የሚያደርጉት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ፓርላማው አዋጆች፣ ደንቦችና ረቂቆችን የሚያየውና የሚወያይበት እንዲሁም ውሳኔ የሚያስተላልፍበት ቋንቋ አማርኛ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም በፓርላማም ሆነ በልዩ ልዩ ኢትዮጵዊ በአላት ላይ ለሕዝባቸው ንግግር ያደርጉ የነበሩት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን 17 አመት ሲመሩ ለሕዝባቸው በአማርኛ ቋንቋ ነው የሚናገሩት። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለሕዝባቸው የሚናገሩት በአማርኛ ቋንቋ ነበር። ሊግ ኦፍ ኔሽን፣ ጄኔቫ ላይ ያሠሙት ታሪካዊ ንግግርም ሣይቀር በአማርኛ ቋንቋ ነው። አጤ ምኒልክም ለሕዝባቸው የሚናገሩት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ታላቁን የአድዋ ጦርነትም ያወጁት በአማርኛ ቋንቋ ነበር። የአድዋን ድልም ያበሰሩት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ከእርሣቸው ቀደም ያሉት አፄ ዮሐንስ እና አፄ ቴዎድሮስም ከሕዝባቸው ጋር በአማርኛ ቋንቋ ነበር የሚነጋገሩት። እናም አማርኛ የመንግሥት ቋንቋ ነው። እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው መሪዎች አማርኛ ቋንቋን ባይናገሩ ኖሮ ኢትዮጵያን ሊመሩ አይችሉም። ስለዚህ ሁላችንም አማርኛን ቋንቋ እንድናውቅ ግድ ይለናል።

የሐገሬ መሪ የሚናገረውን ቋንቋ፣ የሐገሬ ፓርላማ የሚወያይበትን ቋንቋ፣ አዋጅ የሚነገርበትን ቋንቋ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማረው ይገባል። ሊናገረው ይገባል።

ድሮ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና የሒሳብ ትምህርቶች ላይ የወደቀ ወይም F ያመጣ የማትሪክ ተፈታኝ ዩኒቨርሲቲ መግባት አይችልም ነበር። እነዚህ ትምህርቶችን ማለፍ ግዴታ (Compulsory)  ነበር። እነዚህ ሦስት ትምህርቶች ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የመጀመሪያ አመት ተማሪ ሲሆን ይማራቸው ነበር። አማርኛ ቋንቋ ከዚህ ማዕረግ ውስጥ ከወጣ 30 አመታት አለፉ። የመሪያችንን ቋንቋ፣  የፓርላማውን ቋንቋ ብዙ ትኩረት አልሠጠነውም።

በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የአፍሪካ ሕብረት ቋንቋ ምን ይሁን የሚል ጥያቄ በምሁራን ዘንድ ተነስቶ ነበር። ያነሡት ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም። ከቅኝ ግዛት የተላቀቁት የሌሎች አፍሪካ ሐገራት ምሁራን ናቸው። እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ፖርቹጋልኛ የአፍሪካ ቋንቋዎች አይደሉም፤ የቅኝ ገዢዎቻችን ቋንቋዎች ናቸው። ስለዚህ አፍሪካዊ የሆነ ቋንቋ ያስፈልገናል ተባባሉ። አፍሪካዊ ፊደል ያለው የፅሁፍ ቋንቋ የሆነው ብዙ ታሪክ ያለው አማርኛ ቋንቋ በዋናነት ታጭቶ ነበር። ምክንያቱን በውል ባለተረዳሁበት እና መረጃም ያጣሁለት ነገር ቢኖር ይህ እጩነት እንዴት ገቢራዊ እንዳልሆነ ነው። አማርኛ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የልሣን  ቋንቋ እንዲሆን መታሠቡ የቋንቋውን ግዙፍነት ያሳያል። ይህን ታሪክ ያገኘሁት የዛሬ አራት አመት የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ አመቱን ሲያከብር የሕብረቱን መጽሔት ካዘጋጁት መካከል የቡድን መሪ ስለነበርኩኝ ሰነዶችን በማገላብጥበት ወቅት የአማርኛን እጩነት አነበብኩኝ።

ለነገሩ በአሜሪካም ውስጥ ዋሽንግተን እና አንዳንድ ከተሞቸ አማርኛ በአሜሪካ  ከሚነገሩ ቋንቋች ምድብ ውስጥ ገብቶ የአሜሪካ መንግሥት እውቅና ሠጥቶታል። ፍ/ቤት እና ሌሎች አገልግሎት ስፍራዎች ላይ አማርኛ በመንግሥት ደረጃ ፈቃድ አግኝቷል።

የቅርቡን እንተወውና ወደ ሩቁ ዘመን እንሂድ። ለመሆኑ አማርኛ ቋንቋ እንዴት ተፈጠረ፣ እንዴትስ አደገ፣ ተስፋፋ የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ እናንሳ።

እርግጥ ነው አንድን ቋንቋ በዚህ ዘመን ተፈጠረ ብሎ መናገር አይቻልም። አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ቋንቋው አገልግሎት ላይ ይውልበት የነበረውን ዘመን መጠቆም ይቻል ይሆናል።

አንዳንድ ፀሐፊያን ሲገልፁ፣ የአክሱም ስርወ መንግስት ከሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ እየተዳከመ መጣ። በተለይ በቀይ ባህር ዙሪያ ላይ ሰፊ የሆነ የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ስለነበር እንደ ቀደመው ዘመን ገናነቱ ሊቀጥል አልቻለም። ከውስጥም ግጭቶች እያየሉ መጡ። በኋላም እየተዳከመ መጥቶ ስልጣን ወደ ሮሃ ላስታ አካባቢ መጣ። የአማርኛ ቋንቋንም መስፋፋትን ከዚሁ ከዘመነ ዛጉዌ ጀምረው የሚቆጥሩ አሉ። በተለይ በንጉስ ላሊበላ ዘመነ መንግስት ጀመረ የሚሉ አሉ።

ሌሎች ደግሞ አማርኛ የተስፋፋው ስልጣን ወደ ሸዋ ሲመጣ በአፄ ይኩኖ አምላክ /1245-1268/ ዘመነ መንግስት ነው ይላሉ። አማርኛን ሸዋዎች ናቸው የጀመሩት ይላሉ። ሌሎች ደግሞ፣ አማርኛ ወሎ ውስጥ አማራ ሳይንት ከተባለች ቦታ የፈለቀ ነው ይላሉ። ግን የድሮው ታሪክ ፀሐፊ አለቃ ታዬ ይህን አይቀበሉትም። አለቃ ታዬ በ1920 “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ የሚከተለውን ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡-

“ባፄ ይኩኖ አምላክ ጊዜ የአማርና ቋንቋ ተጀመረ ማለት ፈፅሞ ጨዋታ እና ተረታ ተረት ነገር ነው። ባፄ ይኩኖ አምላክ ጊዜስ አማርኛ ፈፅሞ የሠለጠነ ያማረ የተወደደ ጉሮሮ የማያንቅ፣ ለንግግር የማያውክ ሆኖ ስለተገኝ የቤተ-መንግስት ቋንቋ እንጂ ንግግሩስ አስቀድሞ ከዚህ በፊት ብዙ ዘመን የነበረ ነው። አፄ ይኩኖ አምላክ የነበሩትና የነገሡት አሁን በቅርቡ በ1253 ዓ.ም ነው። ከአፄ ይኩኖ አምላክ መጀመሪያ መንግስት እስከ አሁን እስከ ዘመናችን እስከ 1913 ዓ.ም 660 አመት ነው። አማርኛ ቋንቋ ከዚህ ዘመን ብቻ ተነገረ ማለት እንደ ተረት ያለ የጨዋታ ታሪክ ነው። ከዚህ አስቀድሞ ከ5ሺ022 ዓመተ አለም 6ሺ 434 አመተ አለም ከአፄ ይኩኖ አምላክ በፊት ከሺ 640 ዓመት የሚበልጥ አማርኛ ቋንቋ እንደነበር በፊተኛው ክብረ ነገስት ተፅፏል። ከዚያ ዘመን ውስጥ ከነገሡት አያሌ የነገስታት ስም ባማርኛ ቋንቋ ነበር። ይህም ወረደ ነጋሽ፣ ጉም፣ አስጐምጉም፣ ለትም፣ ተላተም፣ መራ ተክለሃይማኖት፣ መባላቸው ይገለጣልና ይታያል። በፊት አማርኛ ቋንቋ ተሌለ ይህ ሁሉ ስም ከምን መጣ? ይህ ሁሉ በግዕዝ በትግርኛ የሌለ ያማርኛ  ስም ነው። ነጋሽ፣ ጐሽ፣ የአረብ ፊደል የአማርኛ ቃል ነው እንጂ በግዕዝ “ሸ” “ጀ” “ጨ” የሚል ቃል አንድ እንኳ አይገኝም።”

ታሪክ ፀሐፊያችን አለቃ ታዬ ከላይ በሠፈረው ፅሁፋቸው አማርኛ ቋንቋ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተፈጠረ ሣይሆን ገና ድሮ ጥንት በአክሡም ዘመነ መንግሥት እንደነበር የራሣቸውን መከራከሪያ ነጥቦች ጠቅሠው ይሟገታሉ። ነገር ግን የእርሣቸውም አፃፃፍ ቢሆን ትክክለኛውን ዘመን ይህ ነው ብሎ ማሣየት አይችልም። ግን በዘመነ አክሡም ስርዓት ውስጥ አማርኛ ቋንቋ ነበር ነው የሚሉን።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ በጥንት ዘመን የተፃፈው በግዕዝ ቋንቋ ነው። ጥንታዊት ኢትዮጵያን የምናውቀው የግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ተጠቅልላ ነው። አማርኛ የፅሁፍ ቋንቋ አልነበረም ማለት ነው። የሚፃፈው በግዕዝ ነው። ግን አማርኛን ልሣነ ንጉስ፤ የንጉስ አንደበት መናገሪያ እያሉትም የሚጠሩት አሉ። ሰለዚህ አማርኛ የንግግር ብቻ ነበር ብሎ መገመት ይቻላል።

አማርኛ የፅሁፍ ቋንቋ ሆኖ ብቅ ያለው መጀመሪያ ላይ በአፄ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ከ1297-1327 ለንጉሡ በተገጠመ ግጥም እንደሆነ ጥናቶች ያሣያሉ። ይህ ማለት የዛሬ 789 አመት ነው። ከዚያም ለሁተለኛ ጊዜ በተገኘ የፅሁፍ ማስረጃ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈው በአፄ ይስሃቅ ዘመን መንግስት በተፃፈ ግጥም ነው። ሦስተኛው ደግሞ በአፄ ዘርአያዕቆብ ዘመን መንግስት ከ1399-1414 ዓ.ም  በተፃፈ ፅሁፍ ነው። እንዲሁም ለአፄ ገላውዲዮስ/አፅናፍ ሰገድ 1540-1559/ የተገጠመው ግጥም ተገኝቷል። ግጥሙ ንጉሡ ከግራኝ አህመድ ጋር ያደረጉቱን ጦርነት እና ያገኙትን ድል የሚያወሣ ነው።

አማርኛ በየ ስርዓተ መንግስቱ እየጐለበተ መጣ። በተለይ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አባ ጐርጐሪዮስ የሚባሉ አባት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከቤተ-አምሐራ ይሠደዱ እና ወደ አውሮፓ ይሔዳሉ። እዚያም ሂዮብ ሉዶልፍ የተባለ የቋንቋ ተመራማሪ ጋር ይገናኛሉ። አባ ጐርጐሪዮስ የአማርኛ ቋንቋን ሥርአት ባጠቃላይ ስዋሰውን ለሂዮብ ሉዶልፍ ያስረዱታል። አሱም አባ ጐርጐሪዮስን እንደ መረጃ አቀባይ (informant) ቆጥሮ የአማርኛ ቋንቋ ሰዋሠው መዝገበ ቃላት እ.ኤ.አ በ1698 ዓ.ም አሣትሞ አስወጥቷል። ከዚህ ዘመን ጀምሮ የአውሮፓ ሊቃውንት በአማርኛ ቋንቋ እና በኢትዮጵያ ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጀመሩ በማለት በአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ የቋንቋና የሥነ-ጽሑፍ ሊቅ የነበሩት መምህራችን ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ጽፈዋል።

ስለ አማርኛ ቋንቋ መስፋፋት ምክንያት የሆኑ ነጥቦችን ስንጠቅስ አንድ ታላቅ ጀርመናዊ እፊታችን ድቅን ይላል። ይህ ሠው ዮሐን ፖትከን ይባላል። የኮሎኝ ሠው ነው። ይህ ሰው በቫቲካን በቅዱስ እስጢፋኖስ ከሚገኙ መነኮሣት የዳዊት የግዕዝ ግልባጭ አግኝቶ በህትመት እንዲወጣ አድርጓል ይባላል። ይህም የሆነው በ1513 ዓ.ም ነው። ጀርመናዊው ጉተንበርግ የመጀመሪውን የሕትመት መሣሪያ እንደሰራ ከታተሙ የአለማችን መፃሐፍት አንዱ ይህ ኢትዮጵያዊ መጽሐፍ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን መፃሕፍት በአውሮፓ ማሣተም የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1513 ዓ.ም በዮሐን ፖትከን አማካይነት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ የታሪክ ፀሐፊ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ሕትመት ታሪክ ባዘጋጁት ግሩም መጽሃፋቸው ውስጥ ሌላ ጀርመናዊን ይጠቅሣሉ። ይህ ሰው ፒተር ሃይሊንግ ይባላል። ሙያው ሕክምና ነው። ግን ከፍተኛ የቋንቋ ችሎታ ያለው ሠው ነበር። ጐንደር ላይ ገናና መሪ ከነበሩት ከአፄ ፋሲል/1632-1667/ ጋር ጥሩ ጓደኝነት ይፈጥራል። በወቅቱ ሐይማኖትን ለማስፋፋት ይፈልግ የነበረው ይኸው ጀርመናዊ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዮሐንስ ወንጌልን እ.ኤ.አ በ1647 ዓ.ም ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማሣተም በብዛት ማሠራጨቱ ተጽፏል።

ለአማርኛ ቋንቋ መስፋፋት አስተዋጽኦ ካደረጉ ሠዎች መካከል ኢዘንበርግ የተባለው ሚሲዮናዊ ተጠቃሽ ነው። ይህ ሰው እ.ኤ.አ በ1841 ዓ.ም የጂኦግራፊ መጽሐፍ አሣትሟል። አማርኛው ግን ያው የፈረንጅ አማርኛ ነበር። ይህ ሰው ትግራይ አድዋ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱም በትግርኛ ቋንቋም አሣትሟል። እ.ኤ.አ በ1835 ዓ.ም ደብተራ ማቲዮስ የተባለ ኢትዮጵያዊ ቀጥሮ ሐዲስ ኪዳንን ወደ ትግርኛ ቋንቋ መተርጐሙን ዶ/ር አምሣሉ አክሊሉ አጭር የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በተሠኘው የጥናትና ምርምር መጽሐፋቸው ላይ ገልፀዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን በኢትዮጵያ ቋንቋ የመተርጐምና የማሠራጨት ስራ ተስፋፍቶ ነበር። በ1870 የሉቃስ ወንጌል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሟል። ከሦስት አመት በኃላ መዝሙረ ዳዊት እና ኦሪት ዘፍጥረት ቀጥሎም ኦሪት ዘፀአት እ.ኤ.አ. በ1877 በኦሮምኛ ታትሟል።

ይኸው ኢዘንበርግ የተባለው ሚሲዮናዊ ከጂኦግራፊ መፅሐፍ ሌላ የአማርኛ ንባብ ማስተማሪያ መፅሐፍ “የትምህርት መጀመሪያ” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም፣ “የአለም ታሪክ መጽሐፍ” እ.ኤ.አ በ1842 ደርሶ አሳተመ።

ከዚያም ኢትዮጵያዊ መፃሕፍት በአውሮፓ ውስጥ ይታተሙ የነበሩት በብዛት ጀርመን እና ስዊዝ ውስጥ ነበር። በተለይ በስዊዝ አገር በቅዱስ ክሪቮና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማተሚያ ቤት ተቋቁሞ ስለነበር ከስዊዝ እስከ ኢትዮጵያ መፃሕፍት ይጓጓዙ ነበር። በሰው፣ በእንስሳት፣ በባህር ላይ እየተጓጓዙ በአማርኛ ቋንቋ ለማደግ ሁሉም ተረባርቧል። አማርኛ ቋንቋ የሁሉም ነው።

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ በ1863 ዓ.ም ምፅዋ ውስጥ መቋቋሙን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ይገልጻሉ። ያቋቋሙት የላዛሪስት ቄስ የነበሩት ቢያንኪየሪ የሚባሉ ሰው እንደሆኑ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ አጭር የኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክ በተሰኘው ያልታተመ ስራቸው በሆነው መፅሐፍ ገልፀዋል።

ማተሚያ ቤት በከረን ውስጥም በ1879 ዓ.ም ተቋቋመ። እንዲህ እያለ እየተስፋፋ መጣ። እውቀትም ተስፋፋ። በአማርኛ ቋንቋ መፃፍ፣ መናገር፣ መማር፣ ማስተማር እየጎለበተ መጣ። አማርኛም ኢትዮጵያን ጠቀመ። አሳደገ። ዕውቀት አስፋፋ። የዓለምን እውቀት ወደ ኢትዮጵያ አመጣ። ባለውለተኛ ቋንቋ ሆነ።

ለአማርኛ ቋንቋ እድገት ሁሉም ማሰነ። ጊዜውን፣ ዕውቀቱን አበረከተ። አማርኛ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ፈረንጆቹ ሳይቀሩ ለአማርኛ ቋንቋ እድገት ማስነዋል። ታዲያ ይህን ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ ዩኒቨርስቲ ደርሶ አለመናገር፣ አለመስማት ለምን ተፈጠረ? አማርኛ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማረው የሚገባ ቋንቋ መሆኑን ብዙም ማስረዳት አያስፈልገውም።

ወደፊት ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እዚህ እስከኛው ዘመን ድረስ አማርኛን ቋንቋ መሠረቱን ያቆሙትን እና ያስፋፉትን ሊቃውንት ለማስታወስ እሞክራለሁ።

መላው መፅሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ ቋንቋ ለመትርጐም ተነሣስቶ ከብዙ አመታት ድካም በኃላ ሐሣቡን እግቡ ያደረሠው የጐጃም ተወላጅ የሆነው መነኩሴ አባ አብርሃም ነው። አብርሃም በግብፅ አድርጐ ኢየሩሳሌም ለመሣለም ሂዶ ነበር። ከዚያም የትምህርት ሠው ስለነበር ወደ ሶርያ አርሜኒያ ፋርስ እና ወደ ሕንድ አገር ሔዶ እየተዘዋወረ ከጐበኘ በኃላ ወደ አገሩ ተመለሠ። አገሩ ለረጅም ጊዜ ከቆየ በኋላ እድሜው ከሃምሳ በላይ ሲሆን እንደገና ወደ ግብፅ ሔደ። እግብፅ ከደረሠ በኋላ በጠና ይታመምና የፈረንሣይ ረዳት ቆንሲል የነበረው አሰለን ረድቶት ያድነዋል። ከዚህ በኋላ አሰለን ኢትዮጵያዊውን መነኩሴ በቅርብ ሲያውቀው ብዙ ቋንቋዎችን ያውቃል። ፋርስኛ፣ ኢጣልያኒኛ፣ ግሪክኛና ሌሎችም ቋንቋዎች የሚያውቅ ሠው መሆኑን ይረዳል። ከዚህ የተነሣ ፈረንሣዊው አሰለን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ እንዲተረጉም ጠይቆት ከተስማሙ በኋላ በሣምንት ሁለት ሁለት ቀን ማለትም ማክሰኞ እና ቅዳሜ እየተገናኙ አስር አመት ሙሉ ከሠሩ በኋላ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ አለቀ። በትርጉሙ ላይ የአሰለን ድርሻ አንዳንድ ከበድ ያሉ ቃላት ሲያጋጥሙ ከኢብራይስጡ፣ ከሱርስትና ከሳባው ሊቃውንት ትርጉም እያመሣከረ አብርሃምን መርዳት ነበር። የትርጉም ስራ እ.ኤ.አ በ1818 ዓ.ም ካለቀ በኋላ አባ አብርሃም ለዕረፍት ወደ እየሩሳሌም ሂዶ ሳለ ወዲያው በአገሩ ውሰጥ ወረርሽኝ ገብቶ ስለነበረ በዚሁ በሽታ ተለክፎ እዚያው ሞቶ ተቀበረ።

ወደ አማርኛ የተተረጐመው መላው መጽሐፍ ቅዱስ በእጅ ጽሁፍ 9539 ገጽ እንደነበረው ሲታወቅ በዚያው በተርጓሚው በአብርሃም የአማረ ብዕር የተፃፈ ነበር። ይላሉ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ግሩም አድርገው ባዘጋጁት መጽሀፋቸው። አሰለን Church mission society  እና ለ Bible society  የአብርሃምን ረቂቅ ቢያስረክባቸው ወጭ ያደረገውን 1250 ፓውንድ ጠይቆ አስረክቧቸዋል።

ይህ የአብርሃም ትርጉም በእንግሊዝ አገር በሚገኙ የቋንቋ አዋቂዎች ከተመረመረ በኃላ መላ አርባዕቱ ወንጌል እ.ኤ.አ በ1824 ዓ.ም በአማርኛ ታትሞ ወጥቷል። ሐዲስ ኪዳንን እ.ኤ.አ በ1829 ዓ.ም ታትሞ ሲወጣ መላው መጽሐፍ ቅዱስ እ.ኤ.አ በ1840 ዓ.ም በአማርኛ ታትሞ ወጥቷል።

ይህ የአባ አብርሃም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ አቡሩሚ በሚባል ስም ይታወቅ ነበር። አቡሩሚ ግብፆች አባ አብርሃምን ይጠሩበት የነበረ ስም ነው። ይህ ሠው ለአማርኛ ሥነ-ፅሁፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ በምንም ቃላት ማወደሻ ሊገለፅለት አይችልም።

የእሡን መጽሐፍ ቅዱስ አውሮፓ ውስጥ እያሣተመ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ተጀመረ። በአመቱ ማለትም በ1841 ዓ.ም ክራኘፍ የተባለ ሚሲዮናዊ 1000 ልሳነ ክልኤ (ባለ ሁለት ቋንቋ) የአረብኛ እና የአማርኛ መፃህፍት ቅዱሣትን ለሸዋው ንጉስ ለንጉሥ ሳህለሥላሴ ሰጥቷል። እንዲህ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እያደጉ መጡ።

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የታወቀው ሚሲዮናዊ ማርቲን ፍላድ እ.ኤ.አ በ1856 ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 300 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዲስ ኪዳን እና ልዩ ልዩ የሃይማኖት ጽሁፎችን ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል።

አማርኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ መገለጫ ከሆነ ከ150 አመታት በላይ ሆኗል። በአፄ ቴዎድሮሰ ዘመነ መንግሥት የንጉሡ ደብዳቤ መላላኪያ ሆኖ የመጣ ቋንቋ ነው። ከዚያ በፊት ደግሞ በቤተ መንግሥት ውስጥ ያሉ ሠዎች ብቻ የሚነጋገሩበት ቋንቋ ነው።

አማርኛ ቋንቋ የሴም ቋንቋዎቸ ውስጥ የሚመደብ ነው። የግዕዝ ቤተሠብ ነው።

ዘመድ ነው። አንዳንድ አጥኚዎች ግዕዝና አማርኛ የሩቅ ዘመዶች ናቸው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የእህትና የወንድም ልጅ ናቸው ይላሉ። ደፈር ያሉት ደግሞ አማርኛ እናትና አባቱ ግዕዝ ነው ይላሉ። ደፈር ያሉት ደግሞ አማርኛ አባቱ ግዕዝ ነው ይላሉ። ምንም ተባለ ምንም አማርኛ ቋንቋ በርካታ ነገሮቹ ከግዕዝ ጋር ይዛመዳል። ብዙ ቃላትን ከግዕዝ ተውሷል። በሰዋሠዋዊ መዋቅር (Grammatical Structure) የተለያዩ ቢሆኑም የአማርኛ ውልደት ከግዕዝ ማሕፀን ውስጥ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።

ለዚህ ምክንያት የሚሆነን ንጉሥ አምደፅዮን በተጓዘባቸው ጦርነቶች ድል ካደረገ በኃላ በግጥም መልክ የተፃፈው አማርኛ የቋንቋውን መወለድና ልደቱን ያሣየናል። ቋንቋው በአማርኛ ይፃፍ እንጂ ቃላቱ ከግዕዝ ጋር ከፍተኛ ዝምድና ያላቸው ነበሩ።

ለምሣሌ

ሐርበኛ ዓምደ ጽዮን

መላላሽ የወሠን

ወኸ እንደመሰን

መላላሽ የወሰን

እያለ ይቀጥላል። የአማርኛ ቋንቋ መሠረት የተጣለበት ዘመን ነው ተብሎ የአምደ ጽዮን ስርዓት ይጠቀሣል። ሌሎች አጥኚዎች ደግሞ የአማርኛ ዕድሜ ከዚያም ይልቃል ነው የሚሉት።

አማርኛ ቋንቋ እንዲህ ተወለደና አደገ። የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ የመንግሥት እና የሕዝብ ቋንቋ ሆነ። አማርኛ በከፍተኛ ደረጃ እመርታ አሣየ። የትምህርት ቋንቋም ሆኖ የኢትዮጵያን አያሌ ሊቃውንት አፍርቷል።

በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ጐንደር ከተማ ውስጥ የሐይማኖት መስበኪያም ሆኖ እንደመጣ አንዳንድ ፀሐፊያን ይገልፃሉ። አማርኛ ቋንቋ እንዲህ ራሡን አደራጅቶ የሚሊዮኖች ልሣን ሊሆን የበቃበት ምክንያት ብዙ ቢሆንም በዘመኑ የነበሩት የቋንቋ ልሂቃን (elites) አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም። ቋንቋው የራሡ የሆነ ሥርዓተ ድህፈት(Orthography) ያለውና ከፍተኛ የሆነ የሰዋሠው  (Grammar) እና የሥነ-ልሣን (Linguistics) ጥናትና ምርምር እየተደረገበት ዛሬ በአለም ላይ አድገዋል ተብለው ከሚጠሩት ቋንቋዎች መካከል አንዱ ሆኗል።

የአማርኛ ቋንቋ እድገት ምስጢር

አማርኛ ቋንቋ ስርዓቱ ክፍት ነው። ቃላትን ከተለያዩ ቦታዎች እና ቋንቋዎች እየተቀበለ ራሡን አወፈረ። አደነደነ። አሣደገ። አማርኛ ከትግርኛ ይዋሣል። ከግዕዝ ይዋሣል። ከኦሮምኛ ይዋሣል። ከጣሊያን፣ ከፈረንሣይ፣ ከእንግሊዝ፣ ከአረብ፣ ከሂብሩ ወዘተ ወዘተ ይዋሣል። ተውሶ የራሡ ያደርጋል። በራሡ የቋንቋ ስርዓት ውስጥ ይከታል።

– ቴሌቪዥን

– መኪና

– ሱሪ

– ኮት

– ሻሂ

– ጉዲፈቻ

– አባወራ

ሌሎች በርካታ ቃላትን ከሌሎች እየተዋሠ እየወሠደ ሕዝባዊ ቋንቋ ሆኗል።

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሲናገር አማርኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋንቋ ነው ይላል። ይህንን እንዲል ያስገደደው ቋንቋው ከሁሉም ብሔረሰቦች እየተዋሠ ያደገ በመሆኑ የጋራ ቋንቋ ነው ይለዋል።

የኘላኔቷ ተአምረኛ ፀሐፌ ተውኔት የሆነው የሼክስፒር ስራዎች በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡ በተለይ ሎሬት ፀጋዬ የተረጐማቸው እንደነ ሃምሌት የመሣሠሉት ቴአትሮች የአማርኛ ቋንቋን የመግለፅ ከፍተኛ አቅም ያሣየበት ነው። አማርኛ ቋንቋ የማይሸከመው የምድራችን ሃሣብና ገለፃ እንደሌለ ፀጋዬ ገ/መድህን ሃምሌትን ተርጉሞበት አሣይቷል።

አማርኛ የራሡ ፊደል የለውም

አማርኛ ቋንቋ ብልጥ ነው። ፊደል ባይኖረውም ፊደልን የተዋሠው ከግዕዝ ነው። ብዙ ሠዎች አማርኛ የራሡ ፊደል ያለው ይመስላቸዋል። ነገር ግን አብዛኛዎቹን ፊደሎች የተዋሰው ከሀገሩ ልጅ ከግዕዝ ቋንቋ ነው። የተወሠኑ ፊደሎችን ብቻ ለራሡ ድምፅ ጨመረ። የተቀሩት የግዕዝ ቋንቋ ፊደሎች ናቸው። በተውሶ የዳበረ ቋንቋ ነው።

ለነገሩ ትግርኛም፣ አደርኛም፣ ጉራግኛም ፊደሎቻቸውን የተዋሡት ከግዕዝ ነው። ሌላ ሀገር ሆና ዛሬ የተገነጠለችው ኤርትራ ሣትቀር የቋንቋዋ ፊደል የግዕዝ ነው። እነዚህ ቋንቋዎች የተዋሡት ከጐረቤታቸው፣ ከቅርባቸው ነው። ሩቅ አልሄዱም። በፊደል ሕግ ሩቅ መሔድ ብዙ አያዋጣም። አንዳንድ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የላቲን ፊደልን በመጠቀማቸው የተነሣ ዛሬ ተጐጅዎች ሆነዋል።

ተጐጂ የሆኑበት ምክንያት የላቲን ፊደሎች በውስጣችው አናባቢ (Vowel) የላቸውም። በላቲን ተነባቢው (Consonant) ሲፃፍ አናባቢው አብሮ ነው የሚፃፈው። ስለዚህ የላቲን ፊደል የተጠቀሙ የሃገራችን ቋንቋዎች አንድ ነገር ለመፃፍ ሲፈልጉ በጣም ረጅም ይሆንባቸዋል። ለምሣሌ

በአማርኛ          በላቲን

አበበ               Aababa

አንዱ ቃል በእጥፍ ይጨምራል። ስለዚህ ፍቅር እሰከመቃብርን ወደ ላቲን ወደሚጠቀሙ የሃገራችን ቋንቋዎቸ ብንተረጉመው ብዙ ቅጽ መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል። የግዕዝ ፊደሎች በውስጣቸው አናባቢውን (Vowel) ሰለሚይዙ አፃፃፋቸው ስብሰብ ይላል። ቅለትም አለው።

አማርኛ ቋንቋ የሴም ቋንቋ ነው ቢባልም ከሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተዋሰ ያደገ ነው። እናም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ስለሆነ ቋንቋውን ማወቅ ግድ ይለናል።

ምንጭ:- ሰንደቅ

Filed in: Amharic