>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7223

ደመራ (መምህር ምህረተ አብ)

 

ደመራ;- ደመረ ከሚለው መነሻ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መሰብሰብ ማከማቸት እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ደመራ ማለት የመሰብሰብ ወይም የመደመር ሂደት (ደመራ፤ ድመራ ) ልንለው እንችላለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ከፈፀመ በኋላ እንደ ወንጀለኛ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ ሞተ ( መስቀል የወንጀለኛ መቅጫ ነበር) ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ እንደ ተራ ነገር አውላላ ሜዳ ላይ ጣሉት ከጊዜ በኋላ ግን ወደ አይሁዳ ጆሮ አንዱ አንድ ነገር መጣ ፡፡ እንደ ቀልድ የጣሉት የክርስቶስ መስቀል ህሙማንን እየፈወሰ እውራንን እያበራ ድንቅ ታእምራትንም እያደረገ እንደሆነ ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ከከተማው አውጥተው እንደሰቀሉት ሁሉ መስቀሉንም እንዲሁ ከከተማ ውጭ አውጥተው በተራሮች መካከል ቀበሩት ቆሻሻም መጣያ አደረጉት፡፡

እግዚያብሔር ግን ነገርን የሚያከናውንበት ጊዜ አለውና ደግሞ ዘመን መጣ፡፡ በእስጢፋኖስ ሞት የተበተነው የክርስትናው ዘር ማፍራት ጀመረ በሮም ነግሰው የነበሩት መክሲሚያኖስ እና ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን እንደ ሰም እያቀለጡ እንደ ገል እያደቀቁ ከነፍሰጡሮች ማህፀን ሽል አውጥተው በሰይፋቸው እየሰነጠቁ በስቡ ጎራዲያቸውን በሚወለውሉበት በዚያ አስደንጋጭ የዘመነ ሰማዕታት የስቃይ ጊዜ ( በነገራችን ላይ ቤተክርስቲያን በዚያ ዘመን ከደረሰባት መከራ የበለጠ እስካሁን አልደረሰባትም ወደፊትም ይደርስባታል ተብሎ አይገመትም) ብዙ ክርስቲያኖች ዋሻ ውስጥ አበው ግበበምድር ይሉታል ገብተው ተውፊት ቁሳዊንና ትውፊት መንፈሳዊውን እየጠበቁ በብዙ መከራ የተስፋይቱን ቀን ሲናፍቁ ነበር፡፡
በዚያ የክርስቲያኑ ስደት በተጀመረበት ጊዜ አንዲት ሴት ከነዚህ መከራ ከወረደባቸው ስለ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉት ጋር አብራ ገፈት ቀማሽ ነበረች ስሟ እሌኒ ይባላል፡፡ በኋላ የመከራው ዘመን ሲያልፍ ንጉስ ቆንስጣን አግብታ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ወልዳለች፡፡ ንግስቲቱ እሌኒ በመከራ ውስጥ እግዚያብሔር የለያት ሴት፡፡
በንግስትነት ስትኖር ቤተመንግስቱ ስለተመቻት ክርስቶስን አልረሳችውም፡፡ ይልቁንም የጌታ ፍቅር እንደ እግር እሳት ስለሚያንገበግባት እሱን በአይነ ስጋ ባገኘውም እንኳን መስቀሉን አግኝታ ገላው ያረፈበትን አቅፋ፣ ስማ ፍቅሯን ለማውጣት መንፈስ ቅዱስ አነቃት ወደ እየሩስ አሌምም መጣች፡፡

የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበት አካባቢ ማንም አያውቅም ያገኘችው አረጋዊ ሰው ኪሪያኮስ እንኳን አካባቢውን ከመገመት አባቶቻችን ከነዚያ ተራሮች በአንዱ ነው ይላሉ ከማለት የዘለለ ሊነግራት አልቻለም፡፡ ክርስቲያን ነገር ሲከብደው የሁሉ ነገር መፍትሔ ወዳለው ጌታ ይፀልያልና ንግስት እሌኒና አረጋዊ ክሪያኮስ ሱባዔ ይዘው ወደ ፈጣሪያቸው ማመልከት ጀመሩ፡፡
በመንፈስ እንደተረዱት እንጨት ሰብስበው ደመራ ደምረው እሳት ሲያነዱ ከእሳቱ ላንቃ በላይ ተምዘግዛጊ ጢስ ወጣ ( ጢሰ ቅታሬ) እንደ ጦር ቀስት ምልክት ያለው፡፡
ጢሱም በአንድ ተራራ አናት ላይ ተተከለ፡፤ ሰው እግዚአብሔርን ማገልገል ሲያቅተው ግዕዛንና እንስሳት ያገለግሉታል ፡-የቢታንያ ዲንጋዮች ፣ የሰባ ሰገል ኮኮብ፣ የበልአም አህያ፣ የገሊላ ባህር አሁን ደግሞ የደመራው ጢስ ከአይሁድ በላይ ባለአይምሮ ሆነ ጢሱም ያረፈበት ቦታ የመስቀሉ መገኛ መሆኑን ስላወቁ ደመራውን በደመሩበት ማግስት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ ቅዱሱ የጌታ መስቀል መጋቢት 10 ቀን ተገኘ፡፡ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

Filed in: Amharic